ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መቐለ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዛሬ መቐለ ላይ በሚደረግ አንድ ጨዋታ የሚጀመር ይሆናል። ይህንኑ ጨዋታ በዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

የዚህ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ ዳኝነት ሲደረግ ሁለት የተነቃቃ መንፈስ ውስጥ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኝ ይሆናል። ሳምንት ከሜዳው ውጪ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ማሸነፉን ተከትሎ ወደ ሁለተኛ ደረጃ መምጣት የቻለው መቐለ ከተማ ከፋሲል ከተማ ጋር ያለግብ ከተለያየበት ጨዋታ ውጪ በድሬደዋ ከተማ ፣ ወልድያ እና ሲዳማ ቡና ላይ ያሳካቸው ድሎች አሁን ለሚገኝበት መልካም አቋም ምስክሮች ናቸው። ያለፉት ሁለት ሳምንታት ለኢትዮጵያ ቡናም መልካም ውጤቶችን ይዘው የመጡ ነበሩ። ከስምንተኛው ሳምንት በኃላ ከድል ርቀው የሰነበቱት ቡናማዎቹ በነዚሁ ጊዜያት ድሬደዋ ከተማን እና ፋሲል ከተማን በተከታታይ ማሸነፍ ችለዋል። ይህ ጥሩ የሆነ የቡድኖቹ ወቅታዊ አቋምም የጨዋታውን ዋጋ ከፍ የሚያደርገው ሲሆን በሊጉ ፉክክር ለሚኖራቸው ቦታም ወሳኝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። መቐለ ከተማ ጨዋታውን የሚያሸንፍ ከሆነ ሊጉን የመምራት ዕድል የሚያገኝ ሲህምን በአንፃሩ ድል ለእንግዶቹ የሚሆን ከሆነ ኢትዮጵያ ቡናዎች ነጥባቸውን 21 አድርሰው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና አዳማ ከተማ ጋር የሚስተካከሉበት ዕድል ይኖራል።

በባለሜዳዎቹ መቐለዎች በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን አለማየው ሙለታን በረዥም ጊዜ ጉዳት እንዳጣ የሚታወቀው ኢትዮጵያ ቡና አክሊሉ አያናው እና አስቻለው ግርማም ሙሉ ለሙሉ ለጨዋታ ዝግጁ ያልሆኑ ተጨዋቾቹ ናቸው።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ሁለቱ ተፋላሚዎች ግብ የማስቆጠር ችግር የነበረባቸው ቢሆንም በቅርብ ሳምንታት በዚህ ችግራቸው ላይ ያሳዩት መሻሻል ለውጤታቸው ማማር ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። በዚህ ረገድ እስካሁን አስር ግቦችን ብቻ ማስቆጠር የቻለው መቐለ ስድስቱን ያገኘው በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ነው። ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ወደ ድል በተመለሰባቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። በዚህ ለውጥ ውስጥ አስተዋጿቸው ከፍ ብሎ የታዩት ሳሙኤል ሳኑሚ ፣ ጋይሳ አፖንግ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል ዛሬ ከጎል ፊት የሚኖራቸው ስኬት አንዱ የጨዋታው ተጠባቂ ነጥብ ነው።

ከዚህ  ውጪ ከመሀል ሜዳው ወደ መቐለ ከተማ አጋማሽ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ድረስ ባለው ቦታ ላይ የሚኖረው የቡድኖቹ ፍልሚያ ለጨዋታው በጣም ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። እዚህ ቦታ ላይ በአማካይ እና የአጥቂ መስመር ተሳላፊዎቻቸው በርካታ ቅብብሎችን የሚያደርጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀላሉ ክፍተት ከማይሰጠው የመቐለ ከተማ የመከላከል ቅርፅ ጋር የሚገናኙ ይሆናል። በተለይ በኤልያስ ማሞ ወደ ነፃ ሚና የሚጠጋ እንቅስቃሴ ላይ መሰረት የሚያደርገው የኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት ሂደት የተጋጣሚውን ከወገብ በታች ያሉ ተሰላፊዎች ቦታ ማሳት እና ከመከላከል ወረዳቸው በመሳብ ክፍተቶችን የማግኘት አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። በፍቃዱ ደነቀ የሚመራው እና በአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቹ በቂ ሽፋን የሚሰጠው የመቐለዎች የኃላ መስመርም የተጋጣሚ አማካዮች በመስመሮች መሀከል ክፍተቶችን እንዳያገኙ በማድረጉ በኩል ከእስከዛሬው ከፍ ያለ ፈተና ከኢትዮጵያ ቡና እንደሚገጥመው ይጠበቃል።በሌላ ጎን ደግሞ በኳስ ፍሰቱ ላይ የመስመር ተከላካዮቹን ለማሳተፍ ሲሞክር ኳስ በሚነጠቅበት ቅፅበት በቦታው ተጨዋቾች እና በመሀል ተከላካዮቹ መሀል የሚፈጥረው ክፍተት ለመልሶ መጠቃት ሲያጋልጠው የሚታየው ኢትዮጵያ ቡና ለእንደነ አማኑኤል ገ/ሚካኤል አይነት ከመስመር በመነሳት አጥብበው ወደ ውስጥ ለሚገቡ አጥቂዎች ምቹ የሆነ ደካማ ጎን አለው። በፋሲል ጨዋታ ላይ ቡድኑን ከ 4-3-3 ወደ 4-2-3-1 እንዲመጣ በማድረግ ይህን ችግር ያቃለሉት አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ በዛሬውም ጨዋታ የመቐለዎች መልሶ ማጥቃት ከብዶ ከመጣ ተመሳሳይ መንገድን መከተላቸው የሚቀር አይመስልም። ያ የማይሆን ከሆነ ግን ባለሜዳዎቹ ከሚሰነዝሩት ፈጣን ጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ብዙም የማይቸገሩ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *