​ሪፖርት | የሲዳማ እና ኤሌክትሪክ ጨዋታ በደጋፊዎች ተቃውሞ ታጅቦ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት የይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ በአሰልቺ እንቅስቃሴ እና በደጋፊ ተቃውሞ ታጅቦ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። 

ሲዳማዎች በ14ኛው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ መከላከያን ከገጠሙበት ስብስብ በአመሀ በለጠ ምትክ ወንድሜነህ አይናለምን ፣ በዮሴፍ ዮሀንስ ምትክ ፈቱዲን ጀማልን ሲጠቀሙ አበበ ጥላሁን ከተለመደ ቦታው ይልቅ በአማካይነት ተሰልፏል። ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ፋሲል ከገጠሙበት ስብስብ በዮሀንስ በዛብህ ፣ ተክሉ ተስፋዬ እና ኄኖክ ካሳሁን ምትክ ሱሌይማና አቡ ፣ ኃይሌ እሸቱ እና ጫላ ድሪባን በመጀመርያ አሰላለፍ በማካተት ወደ ሜዳ ሲገቡ ጫላ ድሪባ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ተሰልፏል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ሳቢ ያልሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያየንበት ፣ በተደጋጋሚ በሚሰማ ፊሽካ የሚቆራረጥበት እና የግብ እድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። እስከ 20ኛው ደቂቃ የግብ ሙከራ ያልተስተናገደበት ሲሆን በ21ኛው ደቂቃ ሲሴ ሀሰን ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት እና በ35ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ትርታዬ ደመቀ ከማዕዘን ምት አሻግሯት ጋናዊው ተከላካይ ማይክል አናን በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጭ የወጣችበት ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴን ያስተዋልንበት ሲሆን ጎሎችም ተስተናግደውበታል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ትርታዬ ደመቀ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ተቆጣጥሮ የግብ ጠባቂው ሱለይማና አቡን እና የተከላካዮቹን መዘናጋትን በመጠቀም ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኃላ አቻ ለመሆን ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ቀይ ለባሾቹ በጫላ ድሪባና ግርማ በቀለ አማካኝነት በተከታታይ ሁለት ጊዜ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በግንባር ገጭተው ወደ ውጭ ወጥቶባቸዋል። 55ኛ ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ፣ በ59ኛው ደቂቃ ካሉሻ አልሀሰን እንዲሁም በ69ኛው ደቀቃ ኃይሌ እሸቱ ለክለቦቻቸው ያገኙትን አጋጣሚዎች አምክነዋል።

በተወሰነ መልኩ በባለሜዳው ሲዳማ ቡና የግብ ክልል አጋድለው መጫወት የቻሉት ኤሌክትሪኮች ተክሉ ተስፋዬን በኃይሌ እሸቱ ፣ ተከላካዩ ሲሴ ሀሰንን በምንያህል ይመር ቀይረው በማስገባት ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 79ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲዬ ለብሪ ከማዕዘን ምት ያሻማትን ኳስ ካሉሻ አልሀሰን በሚገባ ተቆጣጥሮ በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ተክሉ ተስፋዬ አቀብሎት ተክሉ ወደ ግብነት በቀየረወ ግብ አቻ መሆን ችለዋል። ኤሌክትሪኮች ከአቻነት ጎሉ በኋላም የበላይነታቸው ቢቀጥልም ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከ1 ሰአት በላይ የፈጀ ተቃውሞን የይርጋለም ስቴዲየም አስተናግዷል። አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አና አፀያፊ ስድቦች የተሰነዘሩ ሲሆን ተጫዋቾቹን ጨምሮ አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህን አናስወጣም በማለት ደጋፊዎች ሲቃወሙ ተመልክተናል። ሶከር ኢትዮጵያም ጉዳዩን ለማጣራት ባደረግችሁ ጥረት አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ ከአማካዩ ዮሴፍ ዮሀንስ ጋር የፈጠሩት ሰጣ ገባ እንደሆነ እና ተጫዋቹ ከባዬ ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ አሰልጣኙ ከጨዋታ ውጭ ማድረጋቸው ለተቃውሞው ምክንያት እንደሆነ ሰምተናል። የክለቡ ስራ አስኪያጅ መንግስቱ ሳሳሞ በሰጡን አስተያየት ነገ አስቸኳይ ስብሰባ የሚያደርጉ እና ውሳኔ ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና

“በጨዋታው ተጋጣሚያችን ይዞት በመጣው አጨዋወት ምክንያት ወርደን ታይተናል። አስደሳችም አልነበረም። ከመጀመሪያው አጋማሽ ሁለተኛው ጥሩ ነበር። ጥሩ በመሆናችንም ግብ አስቆጥረናል።

” እኔ ጫና ውስጥ አልገባም። ደጋፊው ዛሬ የሰደበኝ አንድ ተጫዋቾች በፈጠረው ነው። እንደማንኛውም ተጫዋች በዲሲፕሊን እርምጃ ተወስዶበታል። ለኔም ካልታዘዘ ምን ያደርግልኛል። ይህ ትልቅ ክለብ ነው። እሱ አንድ ተጫዋች ነው። ክለቡ ግን እርምጃ መውሰድ አለበት። ካለበለዚያ ከባድ ነው ፤ ደጋፊውም አንድ ተጫዋች በፈጠረው አጉል ድርጊት መታለል የለባቸውም። እኔን ግን ሊጎዳኝ ካሰበም ተሳስቷል፡፡

አሸናፊ በቀለ – ኤሌክትሪክ

“እንደ እንቅስቃሴያችን ማሸነፍ ነበረብን። በመጀመሪያ አጋማሽ የደጋፊውን ጫና ለማቀዝቀዝ አስበን ነበር የተጫወትነው። ደረጃችን ስጋት ውስጥ መሆናችንን ይገልፃል። ከባድ ፈተና ቢጠብቀንም ጨዋታዎቹ አላለቁም። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *