ኢትዮጵያ ቡና የ5 ተጫዋቾቹን ኮንትራት አራዘመ

4 ተጫዋቾች የለቀቁበት ኢትዮጵያ ቡና የ5 ተጫዋቾቹን ኮንትራት ማራዘሙን አስታውቋል፡፡ ተጫዋቹ ተከላካዩ ቶክ ጄምስ ፣ አማካዮቹ ዮናስ ገረመው እና ጋቶች ፓኖም እንዲሁም አጥቂዎቹ አብዱራህማን ሙባረክ እና ኤፍሬም ዘካርያስ ናቸው፡፡

ቶክ ጄምስ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ሲሆን በ2005 ዋናውን ቡድን ከተቀላቀለ ወዲህ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በቋሚ ተሰላፊነት አገልግሏል፡፡ በፌዴሬሽኑ ደንብ መሰረት ተጫዋቾች ባደጉበት ክለብ ቢያንስ ለ3 የውድድር ዘመናት መጫወት እንዳለባቸው በመጥቀሱ ቶክ ቀጣዩን የውድድር ዘመንም በአደገኞቹ ቤት ይቆያል፡፡ ሌሎቹ ከወጣት ቡድኑ ያደጉት ጋቶች ፓኖም እና አብዱራህማን ሙባረክም እንደ ቶክ ሁሉ በፌዴሬሽኑ ደንብ መሰረት ቀጣዩንየውድድር ዘመን ለኢትዮጵያ ቡና በመጫወት ይቀጥላሉ፡፡

ዘንድሮ በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ጥቂት የመሰለፍ እድሎችን ያገኘው ኤፍሬም ዘካርያስ ለ2 ተጨማሪ አመታት ኮንትራቱ ተራዝሞለታል፡፡ ከ2004 ጀምሮ ያለፉትን 3 የውድድር ዘመናት በቡና የቆየው ኤፍሬም ለፊርማ 450ሺህ ብር ተከፍሎታል፡፡

ዮናስ ገረመው ሌላው የኮንትራት ማራዘምያ ኮንትራት የፈረመ ተጫዋች ነው፡፡ አማካዩ ከ2005 ጀምሮ ለ2 የውድድር ዘመናት በክለቡ የቆየ ሲሆን በአዲሱ ኮንትራቱ መሰረት ቀጣዮቹን 2 የውድድር ዘመናት በአደገኞቹ ቤት ይቆያል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ከአምስቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የሆኑትን ዳዊት እስጢፋኖስ እና መስኡድ መሃመድን ኮንትራት ለማራዘም በድርድር ላይ ይገኛል፡፡

ቡና እስካሁን ስንታለም ተሸገር ፣ ፋሲካ አስፋው ፣ ሰለሞን ገብረመድህን እና ኤፍሬም አሻሞን ለቆ የአዲስ አበባ ከነማው ሚካኤል በየነን አስፈርሟል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹን ምንተስኖት አዳነ እና አንዳርጋቸው እንዲሁም የሙገሩን በኃይሉ ግርማን ለማስፈረም በእንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡

ያጋሩ