በክረምቱ መቐለ ከተማን የተቀላቀለው የ32 ዓመቱ ጋናዊ አማካይ ሚካኤል አኩፎ ቡድኑ የውጪ ዜጎችን ቁጥር የማመጣጠን ሰለባ በመሆን ተቀናሽ ተጫዋች ሆኗል።
ከዚህ ቀደም በሀገሩ ክለቦች ኣሻንቲ ኮቶኮ እና ኸርትስ ኦፍ ኦክ እንዲሁም በሊቢያው ክለብ ኣ.አል አንሳር የተጫወተው አማካይ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመጣ በኃላ በጉዳት ምክንያት እንደሚፈለገው ክለቡን እያገለገለ አይገኝም። ከመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ጨዋታዎች በኃላም በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሲካተት አልተስተዋለም።
መቐለ ከተማ በጥር የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሰይድ አብዱልዱሩ እና ፊሰን ኑኑ የተባሉ ሁለት ጋናዊያንን ማስፈረሙን ተከትሎ በሁለተኛው ዙር በስብስቡ የሚገኙ የውጪ ዜጎች ቁጥር 6 ስለሚሆን አንድ የውጪ ተጨዋች የመቀነስ ግዴታ ውስጥ ገብቷል። በዚህም ምክንያት ብዙም አገልግሎት እየሰጠ የማይገኘው አኩፎን ለመቀነስ ተገዷል። ቡድኑ ምናልባትም ካለበት የተጫዋች እጥረት አንፃር በአንደኛ ዙር ተስተካካይ ጨዋታ አኩፎን ሊጠበምበት እንደሚችልም ተሰምቷል።
የዮሀንስ ሳህሌው ቡድን ባለፈው ሳምንት 5 ተጫዋቾችን የቀነሰ ሲሆን በአመቱ መጀመርያ ሌላው ጋናዊ አደም ማሲላቺን ማሰናበቱ የሚታወስ ነው።