ቡድኑ በጊዜያዊነት ተበትኖ የነበረውና ከጥር 13 በኋላ ያለፉትን 3 ተከታታይ ጨዋታዎች ማድረግ ያልቻለው ወልዲያ አርብ ከወላይታ ድቻ በሚያደርገው ጨዋታ ወደ ውድድር ይመለሳል። ክለቡ ከወቅታዊ ችግር ጋር ተያይዞ በጊዛዊነት ከተበተነ በኃላ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ወደ መደበኛ ልምምድ መመለሱ የሚታወስ ነው።
በ15ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እሁድ ሊደረግ የነበረውና በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገረው የወላይታ ድቻ እና ወልዲያ ጨዋታ አርብ የካቲት 9 ሶዶ ላይ የሚደረግ ሲሆን ወልዲያም ጨዋታውን እንደሚያደርግ አረጋግጧል። ቡድኑ አዲስ አበባ ዛሬ የገባ ሲሆን ነገ ጨዋታውን ወደሚያደርግበት ወላይታ ሶዶ ከተማ የሚያቀና መሆኑ ታውቋል።
ከቡድኑ ጋር ተያይዞ ያለው መረጃ ወደ ወልዲያ ከሄደው የቡድን ስብስብ ውስጥ ካልነበሩት ተጫዋቾች መካከል ኤደም ኮድዞ ፣ ምንያህል ተሾመ እና አማረ በቀለ ከቡድኑ ጋር ሲቀላቀሉ ታደለ ምህረቴ (ወደ አሜሪካ በመሄዱ) ፣ ፍፁም ገ/ማርያም እና ያሬድ ብርሃኑ እስካሁን ቡድኑን ያልተቀላቀሉ ተጨዋቾች ናቸው።
በሌላ ዜና አማረ በቀለ ክለቡ ከኢትዮዽያ ቡና ጋር በአዲስ አበባ በተጫወተበት ወቅት የዕለቱ ዳኛ ማኑሄ ወ/ፃድቅን ለመደብደብ በመቃጣት የዳኛውን አንገት ይዟል በሚል ስምንት ወር መቀጣቱ ይታወቃል። ሆኖም ይቅርታ በመጠየቁ ቅጣቱ ሊነሳለት እንደሚችል ሰምተናል።
ከ11 ጨዋታ 11 ነጥብ ሰብስቦ በ15ኛ ደረጃ የተቀመጠው ወልዲያ ከደደቢት ፣ መከላከያ እና ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ወደ ፊት በሚገለፅ መርሀግብር እንደሚያከናውን ታውቋል።