በየአመቱ እየጨመረ የመጣው የተጫዋቾች የፊርማ ክፍያ (ክፍል 2 – የመፍትሄ ሀሳቦች)

በክፍል አንድ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች የፊርማ ክፍያ ባለፉት 16 አመታት ምን ያህል እድገት እንዳሳየና በሃገሪቱ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ምን ያህል እንዳሻቀበ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ በክፍል ሁለት ደግሞ ክለቦች የሚያወጡትን ወጪ ለመቆጣጠር ወይም የሚያወጡትን ወጪ የሚመጣጠን አገልግሎት ከተጫዋቾች እንዲያገኙ ሊጠቅሙ የሚችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማንሳት እንሞክራለን፡፡

 

የፋይናንስ ስፖርታዊ ጨዋነት ደንብ አስፈላጊነት

በ2013 በአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የፀደቀው የፋይናንስ ስፖርታዊ ጨዋነት ደንብ ክለቦች ለተጫዋቾች ዝውውርና ደሞዝ የሚያወጡት አጠቃላይ ወጪ ከገቢያቸው ጋር በንፅፅር ምን መሆን እንዳለበትና በህጉ ከተጠቀሰው ገንዘብ በላይ ኪሳራ ያስመዘገበ ክለብ እንደየደረጃው ቅጣት እንዲጣልበት የሚያስድድ ህግ ነው፡፡ ዘንድሮ የተሸሻለውን ህግ ተግባራዊ መሆን የሚቃወሙት እንዳሉ ሆነው የእግርኳሱን ጤናማነት ይጠብቃል ፣ በግድየለሽ ከበርቴዎች ምክንያት እግርኳሱን ከአደጋ ይታደጋል ተብሎለታል፡፡ በክለቦች መካከል ያለውን የፉክክር ሚዛን ከመፋለስ ያድነዋልም ተብሏል፡፡

ይህ ህግ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የምናይበትን ጊዜ የምናልምበት ትክክለኛው ቀን ደርሷል፡፡ ክለቦች ከትርፍ ይልቅ ኪሳራ ተኮር በመሆናቸው የተጫዋቾች ደሞዝ ክፍያ እና ጥቅማጥቅም የበጀታቸውን ምን ያህል መቶኛ መያዝ እንዳለበት የሚያስገድድ ህግ በፍጥነት ተቀርፆ ተግባራዊ መደረግ ይጠበቅበታል፡፡ አመታዊ ኪሳራቸው ምንያህል መሆን እንደሚገባው በጥናት ላይ ተመስርቶ ደንብ ማስቀመጥ ይኖርታል፡፡ ይህንን በማይፈፅሙ ክለቦች ላይም ከነጥብ ቅነሳ እና የገንዘብ ቅጣት እስከ ውድድር ማገድ ድረስ የሚያደርስ ከባድ ቅጣት ቀስ በቀስ ሊጥልባቸው ይገባል፡፡

ይህ ደንብ ተግባራዊ ቢደረግ ትኩረቱን የሚያደርገው በደሞዝ እና የዝውውር ገንዘብ ላይ በመሆኑ ለልማት ስራዎች (ለአካዳሚ ፣ ለስታድየም ፣ ለልምምድ ቦታ ግንባታ እና ለመሳሰሉት) የሚያወጡት ወጪ እዚህ ውስጥ አይደመርም፡፡

ክለቦች በሚልዮን የሚቆጠር በጀታቸውን በተጫዋቾች ደሞዝ ከመጨረስ ተቆጥበው ወጣት ተጫዋቾችን ወደማሳደግ ፣ ክለብን ክለብ የሚያሰኝ የውስጥ የልማት ስራ እንዲሰሩ ብሎም ወጪያቸውን በኮሜርሻል ገቢዎች በማካካስ ወደ ትርፋማነት ለመምጣት እንዲተጉ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ አመታዊ ገቢያቸውን ባሳደጉ ቁጥር ለተጫዋቾች ደሞዝ የመክፈል አቅማቸው ስለሚምርና ህጉም ስለሚደግፋቸው ገቢ ለመሰብሰብ ሊተጉ ይችላሉ፡፡

እግርኳሳችን በአጠቃላይ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ እንደሚታየው ሁሉ በብልሹ አሰራር እና ድብብቆሽ የተሳሰረ በመሆኑ ደንቡ ቢወጣም ተግባራዊ ለማድረግ ተራራ የመውጣት ያህል ከባድ እንዳይሆን መከታተልና ደንቡን ለማስፈፀም ኮስታራ መሆንን ይጠይቃል፡፡

 

ፌዴሬሽኑ በታዳጊ ስልጠና ላይ ስራዎችን መስራት

ፌዴሬሽኑ በሃገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የታዳጊዎች ስልጠና ስርአት ሊያበጅ ይገባል፡፡ በርካታ የማሰልጠኛ ማእከላት ቢኖሩ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች በብዛት ይገኛሉ፡፡ በዚህም ክለቦች በርካታ አማራጮች የሚያገኙ በመሆኑ ለፊርማ የሚያወጡት ከፍተኛ ወጪ ሊቀንስላቸው ይችላል፡፡ በጀርመን እንዳለው አይነት የተሳካ የታዳጊዎች ስልጠና መዋቅር ክለቦችን ምንያህል ሊጠቅም እንደሚችል በአሁኑ ሰአት በሃገሪቱ ያለው የተትረፈረፈ ተሰጥኦ እና የክለቦች ትርፋማነትን ተያያዥነት ማጤን ያስፈልጋል፡፡

 

ክለቦች እና ከሌሎች ክለቦች ጋር ያላቸውን ያለመተማመን ስሜት መተው ይኖርባቸዋል

በኢትዮጵያ ክለቦች እርስ በእርስ የሚገናኙት በአመታዊ የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ አልያም በጨዋታዎች ወቅት ብቻ ነው፡፡ ክለቦቻችን እርስ በእርስ አለመተማመናችው እግርኳሳችንን ወደኋላ ጎትቶታል፡፡ ተጫዋቾች የኮንትራት ጊዜያቸው ሳያበቃ ከክለቦች ጋር ተነጋግረው ሲያመጡ የታየበባቸው ጊዜያት ጥቂት ናቸው፡፡ ተጫዋች እና ክለብ ብቻ በሚገናኝበት እግርኳሳችን ውስጥ ክለቦች ከክለቦች የሚያደርጉት ግንኙነት ሊሻሻል ይገባል፡፡ ትብብራቸውም የዝውውር ገበያውን የሚያንዛዙና ዋጋ የሚያንሩ አሰራሮች እንዲሁም ግለሰቦችን ለማወቅና እግርኳሱን ወደ ጤናማ መንገድ እንዲመራ ሊያደርግ ይችላል፡፡

 

የረጅም ጊዜ ኮንትራት መፈራረም

ይህ ሁለቱንም አካላት (ተጫዋቹንም ሆነ ክለቡን) ሊጠቅም የሚችል አሰራር ነው፡፡ ክለቦች ለ2 አመታት 1.5 ሚልዮን ብር አንድ ተጫዋች ላይ ከሚያፈሱ ለ4 አመታት 3 ሚልዮን ብር ቢያፈሱ የተሻለ ይሆናል፡፡ አንድ ተጫዋች በማንኛውም መስፈርት በ2 አመት የኮንትራት ጊዜ ውስጥ የሚፈለግበትን ግልጋሎት ሊያበረክት አይችልም፡፡ ክለቡን እስኪላመድ ፣ ከአሰልጣኙ አጨዋወት ጋር እስኪዋሃድ ፣ ከደጋፊዎች የሚመጣውን ጫና እስኪቋቋም 2 አመታት በዋዛ ያልፋሉ፡፡ በአንድ ቡድን ውስጥ ከ7 እስ 10 የሚጠጉ አዳዲስ ፈራሚዎች ሲሆኑ ደግሞ አስቡት፡፡ አንድን አዲስ ተጫዋች በክለቡ ውስጥ የሚያላምደው ነባር ተጫዋች ሳይኖር እንዴት ብቃቱን አውጥቶ ሊጠቀም ይችላል? ክለቦች እንደቀኖና የያዙትን ልማድ ትተው ለተጫዋቹ ቢያንስ የ4 አመት ኮንትራት ሊሰጡ ግድ ይላል፡፡ ረጅም ጊዜ በክለቡ እንደሚቆዩ ያረጋገጡ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን የረጅም ጊዜ እቅድ ሊኖረውና በየአመቱ እየተዋሃደ የሚሄድ ቡድን ሊገነባ ይችላል፡፡

ከረጅም ጊዜ ኮንትራት ጥቅሞች መካከል፡-

ተጫዋቹ ለረጅም ጊዜ ክለቡን ይጠቅማል፡፡

ብቃቱን አጎልብተው ኮንትራቱ ሳያልቅ አትርፈው ሊሸጡት ይችላሉ

በክለቡ ውስጥ የተረጋጋ የተጫዋች ስብስብ እንዲኖር ያደርጋል

በአቋም መውረድ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ክለቡ ተጫዋቹን የማይፈልገው ከሆነ ለሌሎች ክለቦች በውሰት በመስጠትና የተወሰነ ደሞዙን ለመክፈል በመስማማት የደሞዝ ወጪውን መቀነስ ይችላል፡፡ ካልሆነም በመሸጥ የደሞዙን ወጪ ከማትረፋቸውም በላይ በዝውውሩ ገንዘብ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ተጫዋቹ የረጅም አመት ኮንትራት ቢፈርም ቢያንስ የኮንትራት ዘመኑ እስከሚያልቅ ድረስ ደሞዙ ሳይቋረጥበት የመጫወት ዋስትና ያገኛል፡፡ ክለቡ ባይፈልገው እንኳን ቀሪ የኮንትራት ዘመኑን በካሳ መልክ እንዲከፈለው ማድረግ ይችላል፡፡

በየ2 አመቱ ከክለብ ክለብ ሲዟዟር ወይም ኮንትራት ሲያድስ ገንዘቡን ሊካፈሉት የሚችሉ 3ኛ ወገን አካላትን በማስወገድ ትክክለኛውን የገንዘብ መጠን እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡

በየ2 አመቱ ከክለብ ክለብ በሚያደርገው ዝውውር ብቃቱ ላይ ከሚደርሰው ችግር (አለመረጋጋት ፣ ከቡድን ጋር አለመዋሃድ ፣ ጫና አለመቋቋም) ተላቆ የወደፊት እግርኳስ ህይወቱን ለማስተካከልና ደረጃውን ለማሻሻል ይረዳዋል፡፡

አሁን በወጣው ህግ መሰረት ገንዘቡ የሚከፈለው በየወሩ ተቆራርጦ በመሆኑ ተጫዋቹ የወር ደሞዝተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ተጫዋቹ ምርጥ ብቃቱን አሳይቶ ኮንትራቱ ሳያልቅ ክለቡ ቢሸጠው እንኳን ከአዲሱ ክለቡ ጋር በደሞዙ ዙርያ ተደራድሮ ከቀድሞው የተሻለ ተከፋይ የመሆን እድል ስለሚኖረው ለበለጠ ስኬት ይነሳሳል፡፡

አሁን ባለው ግሽበት ምክንያት የተጫዋቹን የወደፊት ተጠቃሚነቱን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ቢሆንም ተጫዋቹ እና ክለቡ ኮንትራት በሚፈራረሙበት ወቅት ቅድመ ሁኔታዎች ሊያስቀምጡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በውድድር አመቱ ምንያህል ጨዋታ ቢያደርግ ፣ በውድድር አመቱ ምን ያህል ግብ ቢያስቆጥር/ባይቆጠርበት ፣ ቡድኑ ዋንጫዎችን ካሸነፈ ቦነስ እንደሚኖረው በኮንትራቱ ላይ በማስቀመጥ ለተጫዋቹ አሳማኝ የሆነ ኮንትራት ቢቀርብለት የረጅም አመት ኮንትራት ሊፈርም ይችላል፡፡ ለተጫዋቹ ዋስትና ለክለቡም በተለይም ወጣት ተጫዋቾች ላይ ትርፍ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡

ክለቦች ይህንን አሰራር የሚጀምሩበትና ሃገሪቱን እግርኳስ ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚያመጡበት ሰአት አሁን ይመስላል፡፡ ተጫዋች ሲያስፈርሙ እቅዶች ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አንጋፋ ተጫዋች ከሆነ የአጭር ጊዜ ኮንትራት ፣ ወጣት ተጫዋች ሲሆን ደግሞ ከፍ ያለ ኮንትራት በመስጠት የተረጋጋ የተጫዋቾች ስብስብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ክለቦች እና ተጫዋቹ ኮንትራት ሲያልቅ ብቻ ሳይሆን ገና እኩሌታ ጋር ሳይደርስ ጀምሮ ለቀጣይ አመታት አብረው ስለሚሰሩበት ሁኔታ ሊወያዩ ይገባል፡፡

የኤሌክትሪክ ስራ አስኪጅ የነበሩት አቶ አርአያ ተስፋይ በ1995 ክረምት ኤሌክትሪክ 13 ተጫዋቾቹን ሲያጣ የተናገሩትን እናስታውሳችሁ ‹‹ እኛ ተጫዋቾቻችንን ለ2 አመት ቢበዛ ለ3 አመት እናስፈርማለን፡፡ በመሃል (ኮንትራታቸው ሳያልቅ) የኮንትራት ማራዘምያ ለማድረግ በፕሮፌሽናል መዋቅር አለመደራጀታችን እንቅፋት ፈጥሮብናል፡፡ በሌሎች ሃገራት ላይ እንዳለው ተጫዋቹ ኮንትራቱ ሳያልቅ ለማራዘም ጥያቄ አቅርበንለት ፍቃደኛ ሳይሆን ቢቀር ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ያው አመቱ ሲጠናቀቅ ይለቃል፡፡ በሌሎች ሃገራት ተጫዋቹ አልፈርምም ቢላቸው እንኳን ውሉ ሳይጠናቀቅ ለሽያጭ ያቀርቡታል፡፡ ›› ብለው ነበር፡፡

 

ፌዴሽኑ ኮስታራ ሊሆን ይገባል

ፌዴሬሽኑ ህጎችን በጥንቃቄ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ሊያወጣ ይገባል፡፡ ቅሬታ እንዳይነሳም ሁሉንም ክለቦች ሊያወያይ ይገባል፡፡ አንድ ጊዜ ከፀደቀ በኋላ ደግሞ ተግባራዊ ለማድረግ ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ክለቦች ተጫዋቾችን የሚያስፈርሙበትን መንገድም ሊመረምር ይገባል፡፡

 

ክለቦች ወደራሳቸው መመልከት ይኖርባቸዋል

ተጫዋች ከአሰልጣኙ አልያም ከክለቡ ሃላፊዎች ጋር ባለው ግንኙነት ብቻ ለአንድ ክለብ በከፍተኛ ዋጋ የሚፈርምበት ወቅት ሊያበቃ ይገባል፡፡ ክለቦች ከሚበጅቱት ከፍተኛ ገንዘብ ጥቂቷን ለመልማዮች ፣ ለመረጃ ተንታኞች (data analysts) አልያም የዝውውር ጉዳይ ለሚመለከተው ኃላፊ ሊመድቡለት ይገባል፡፡ የዝውውር ጉዳይን ለስራ አስፈፃሚው ፣ ለዝውውር ጉዳይ ኃላፊ ፣ ለቴክኒክ ዳይሬክተር አልያም ለአሰልጣኙ ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነት በመስጠት በተጠያቂነት እንዲሰሩ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ለአንድ ተጫዋች የወጣው ግንዘብ ምክንያታዊነቱን ሃላፊነት ከተሰጠው ግለሰብ ማብራርያ ሊጠይቁ ይገባል፡፡ የመጣው ተጫዋች ለምን እንደመጣ ፣ ምን ያህል ጊዜ እደሚያገለግል ፣ ቡድኑን ምንያህል እንደሚያሻሽል ፣ የጉዳት ሪኮርዱን ፣ ያለፉ የውድድር ዘመን አቋሞቹን ፣ ምን ያህል ኢንተርናሽናል ጨዋታ እንዳደረገ ፣ እድሜውን ፣ ልምዱን ከግምት አስገብተው ይገባዋል የሚባለውን ገንዘብ እና የኮንትራት ጊዜ ሊሰጡት ይገባል፡፡ የክለቦች ባለቤት የሆኑ ድርጅቶችም ለክለቡ የሚመድቡት የአመት ወጪ ምን ያህል መሬት ላይ እንደወረደ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የሚታይ ለውጥ ሳናስተውል ግሽበት ብቻ ስንቆጥር መዝለቃችን አይቀሬ ነው፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *