በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተለያየው ዳዊት እስጢፋኖስ ወደ ሀዋሳ ከነማ ሊያመራ እንደሚችል ከወደ ሀዋሳ ያገኘነው ዜና ያመለክታል፡፡ ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ከስምምነት ለመድረስ ሳይቃረብ እንዳልቀረም ተነግሯል፡፡ ነገር ግን የሀዋሳ ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ስለ ዝውውሩ የሚያውቁት ጉዳይ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ በዳዊት ዙርያ ምንም መረጃ የለኝም፡፡ መረጃ በሌለኝ ጉይ ዙርያ አስተያየት ልሰጥ አልችልም፡፡ ›› ብለዋል፡፡
ከሱዳን ከተመለሰ ወዲህ ክለብ አልባ ሆኖ የቆየው አበባው ቡታቆ ወደ ዳሽን ቢራ ሊያመራ ይችላል ተብሏል፡፡ የግራ መስመር ተከላካዩ ወደ አዳማ ከነማ ለማምራት ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም የጎንደሩ ክለብ ከፍ ያለ ገንዘብ በማቅረቡ ወደ ዳሽን ሊያመራ ይችላል ተብሏል፡፡ እንደ ሀዋሳ ከነማ ሁሉ ዳሽንም ከተጫዋቹ ጋር ግንኙነት አድርጓል መባሉን አስተባብሏል፡፡
የተጫዋቾች ፊርማ በድሬዳዋ ደርቷል፡፡ ፌዴሬሽኑ ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተጫዋች እንዳያስፈርሙ ቢከለክልም ክለቦች በተጫዋቾች ማረፍያ ሆቴሎች በመገኘት በርካታ ተጫዋ ለማስፈረም በቃል ደረጃ እየተስማሙ እንደሆነ ታውቋል፡፡ አብዛኛዎቹ የፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞች በስፍራው የሚገኙ ሲሆን ተጫዋቾችን በማግባባት ስራ እንደተጠመዱ እየተነገረ ነው፡፡ አንዳንድ ክለቦችም ከወዲሁ እስከ 4 ተጫዋቾች ለማስፈረም እደተስማሙም ተወርቷል፡፡
አዳማ ከነማ ቶጓዊ ግብ ጠባቂ አስፈርሟል፡፡ ናይጄርያዊው ግብ ጠባቂ ፌቮ ኢማኑኤልን ወደ ንግድ ባንክ የሸኙት አዳማዎች በቀጣዩ የውድድር ዘመን ግባቸውን ከቶጎ ያስመጡት ጃኮብ ባሊ ይጠብቅላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዳማ ከነማ አንጋፋው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬንም የግሉ አድርጓል፡፡