አርባምንጭ ከነማ መለሰ ሸመናን ጊዜያዊ አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል

 

አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህን ያጣው አርባምንጭ ከነማ አሰልጣኝ መለሰ ሸመናን የክለቡ ጊዜያዊ አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡ ከክለቡ የሚወጡት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አሰልጣኝ መለሰ የተሸሙት በጊዜያዊነት ሲሆን ክለቡ ቋሚ አሰልጣኝ ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቷል፡፡ አሰልጣኝ መለሰ ሸመና በብዙወች የሚታወቁት በ1995 አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅን እየመሩ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለመሳም በተቃረቡበት ወቅት ነው፡፡ ክለቡ አሰልጣኙን በጊዜያዊነት ቢቀጥርም ከብሄራዊ ሊግ ተጫዋቾችን እንዲመለከቱ ወደ ድሬዳዋ እንዳላካቸው የታወቀ ሲሆን ወደ ስፍራው ያመሩትም የክለቡ ኮሚቴ አባላት ናቸው ተብሏል፡፡

በተያያዘ ዜና እስካሁን ምንም ተጫዋች ያላስፈረመው አርባምንጭ ከነማ የ4 ተጫዋቾቹን ኮንትራት አድሷል፡፡ ክለቡ ውል ካደሰላቸው መካከል አምበሉ ታገል አበበ ይገኝበታል፡፡ የመስር ተከላካዩ ለ2 አመታት 650ሺህ ብር ሊከፈለው መስማማቱ ተነግሯል፡፡ ታሪኩ ጀጎሌ እንደ ታገል ሁሉ በ2 አመታት ውስጥ 650ሺህ ብር ሊከፈለው ተስማምቶ ውሉን አድሷል፡፡ አማካዮቹ ወንድሜነህ በክሪ እና ተመስገን ዱባ ደግሞ እያንዳንዳቸው በ2 አመት ውስጥ 500ሺህ ብር ሊከፈላቸው ተስማምተው ውላቸውን አድሰዋል፡፡

አርባምንጭ ከነማ ለከርሞ በነባር ተጫዋቾች ለመቅረብ እንዳሰበ ሲገለፅ ክለቡን በለቀቁት ተጫዋቾች ምትክ ከብሄራዊ ሊጉ የተመለከታቸውን ተጫዋቾች እንደሚያስፈርም ይጠበቃል፡፡

ያጋሩ