ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት ሁለት ወሳኝ ፍጥጫዎች ነገ ይካሄዳሉ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ላለፉት 2 ሳምንታት በባህርዳር ከተማ አስተናጋጅነት ሲካሄድ ቆይቶ ነገ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚቀላቀሉ 2 ቡድኖችን ማንነት ይለያል፡፡

በ8 ሰአት ወልዲያ ከነማ ከ ወልቂጤ ከነማ ጋር ይጫወታሉ፡፡ በአሰልጣኝ ንጉሱ ደስታ የሚሰለጥለነው ወልዲያ ከነማ ከምድብ አራት ሁሉንም ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቆ ምድቡን በ2ኛነት በማጠናቀቅ ወደ ሩብ ፍፃሜው ሲያልፍ በሩብ ፍፃሜው ጠንካራው ድሬዳዋ ከነማን 1-0 አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተቀላቅለዋል፡፡

በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ ‹‹ ድሬ ›› የሚመራው ወልቂጤ ከነማ እንደተጋጣሚው ወልዲያ ሁሉ ምድቡን በሁለተኝነት አጠናቆ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለ ሲሆን የአስተኛጋጅ ከተማዋን ክለብ ባህርዳር ከነማን በመለያ ምት አሸንፎ ለወሳኙ ዙር አልፏል፡፡

ሁለቱም ከዚህ በፊት በፕሪሚየር ሊግ ተወዳድረው የማያውቁ በመሆናቸውና የሚገኙበትን ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ በመወከል ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት ባላቸው ፍላጎት ምክንያት ጨዋታው ድንቅ ፉክክር ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በ10 ሰአት አዳማ ከነማ ከ ሱሉልታ ከነማ ጋር ፍልሚያቸውን ያደርጋሉ፡፡ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚሰለጥነው አዳማ ከነማ ከወረደበት ሊግ ለመመለስ ከፍተኛ ግምት አግኝቷል፡፡ በረከት አዲሱ ፣ ይታገሱ እንዳለ እና አብዱልከሪም አባፎጊን ጨምሮ ለበርካታ አመታት በትልቅ ደረጃ መጫወት ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተዋቀረው አዳማ ከነማ ብዙም ሳይገመት ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀለው ሱሉልታ ከነማን ማሸነፍ ሊከብደው ይችላል፡፡ ታደሰ ጥላሁን የገነቡት የዘንድሮው ሱሉልታ ከነማ የተደራጀ እና ለተጋጣሚ ብዙም ክፍተት የማይሰጥ ቡድን በመሆኑ ሱሉልታ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ፕሪሚየር ሊጉን ለመቀላቀል ከፍተኛ ትግል ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የትኩረት ነጥቦች

-ከአራቱ ክለቦች የፕሪሚየር ሊግ ልምድ ያለው ከ1994-2005 በሊጉ የቆየው አዳማ ከነማ ብቻ ነው፡፡

-ወልዲያ ከነማ ካሸነፈ ከኮንቦልቻ ከነማ እና ጥቁር አባይ ቀጥሎ በ16 አመታት ታሪክ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለ 3ኛው የወሎ ቡድን ይሆናል፡፡ አማራ ክልልን በመወከል ደግሞ 6ኛው ክለብ ይሆናል፡፡

-ወልቂጤ ጨዋታውን ካሸነፈ ከአዲሱ ሚሌንየም ወዲህ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለ 4ኛው የደቡብ ክለብ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ደቡብን በመወከል ደግሞ 7ኛ ክለብ ይሆናል፡፡

-እስካሁን ሐረር ሲቲ እና ኢትዮጵያ መድንን ጨምሮ ከምድብ እና ከሩብ ፍፃሜው የወደቁት 14 ክለቦች በግማሽ ፍፃሜው ከሚወድቁት ሁለት ክለቦች ጋር ተደምረው ለቀጣይ አመት በአዲስ ሊግ (ከፍተኛ ብሄራዊ ሊግ) ይጫወታሉ፡፡ ከፕሪሚየር ሊግ ቀጥሎ የነበረው ብሄራዊ ሊግ ደግሞ አንድ ደረጃ ወርዶ እንደከዚህ ቀደሙ በዞኖች ተከፋፍሎ አሸናፊዎች ወደ ከፍተኛ ብሄራዊ ሊግ ያመራሉ፡፡

ያጋሩ