​መከላከያ ከ መቐለ ከተማ | ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመርያ ዙር ተስተካካይ ጨዋታዎች ከሐሙስ ጀምሮ እየተደረጉ ሲሆን ዛሬ ደግሞ መከላከያ መቐለ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ከ10፡00 ሰዐት ጀምሮ ይካሄዳል። በዚህ ጨዋታ ላይ የሚነሱ ነጥቦችን እንደሚከተለው አዘጋጅተናቸዋል። 

የ12ኛ ሳምንት መርሀ ግብር የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዛሬ ሲደረግ ለእንግዶቹ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታቸው ሲሆን መከላከያዎች ደግሞ ከዚህ በኃላ ከወልድያ ጋር ሌላ ተስተካካይ ጨዋታ ይጠብቃቸዋል። በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው መከላከያ ባሳለፍነው ሳምንት መግቢያ ላይ በሰፊ የጎል ልዩነት በደደቢት የደረሰበት ሽንፈትን የአመቱ አምስተኛ ሽንፈቱ ሆኖ ሲመዘገብ አሁንም ቡድኑ በርካታ ደካማ ጎኖች እንዳሉት አሳይቶ ያለፈ ነበር። በተቃራኒ መንገድ ላይ የሚገኘው መቐለ ከተማ ደግሞ ሜዳው ላይ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ ነጥብ ቢጋራም ከዚያ አስቀድሞ ያስመዘገባቸው ሶስት ተከታታይ ድሎች በደረጃ ሰንጠረዡ አስተማማኝ ቦታ ላይ እንዲቀመጥ አድርገውታል። የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍም ቡድኑ የመጀመሪያውን ዙር ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ሊያጠናቅቅ የሚችልበትን ዕድል የሚፈጥርለት ሲሆን ለመከላከያዎችም ቢሆን ከወራጅ ቀጠና በመውጣት እስከ 12ኛ ደረጃ ከፍ የሚሉበት በመሆኑ ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።  

መከላከያ ከአዲሱ ተስፋዬ እና ቴውድሮስ በቀለ በተጨማሪ አማኑኤል ተሾመንም በጉዳት ምክንያት የማይጠቀም ሲሆን አሌክስ ተሰማን ከጉዳት መልስ በሚያገኘው መቐለ ከተማ በኩል ግን የተሰማ ሌላ ጉዳት ዜና የለም።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ጨዋታው ግብ የማስቆጠር ከፍተኛ ችግር ያለበትን ቡድን ከጠንካራ የመከላከል አቅም ባለቤት ከሆነ ቡድን ጋር የሚያገናኝ ነው። እስካሁን በሊጉ አምስት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው መከላከያ በዚህ መስፈርት የመጨረሻ ደረጃን ይዟል። መቐለ ከተማ ደግሞ አምስት ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት ክለብ ሆኖ ተቀምጧል። ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎችም በአስሩ መረቡን ሳያስደፍር ለመውጣት ችሏል። በዚህ ረገድ ጨዋታው ለመከላከያ ፈተኛ እንደሚሆን መናገር ይቻላል። አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ በተደጋጋሚ የሚናገሩት የቡድናቸው የአጨራረስ ድክመት ብቻም ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የቦታ አጠባባቅ ችግር የሚታይበት የቡድኑ የአማካይ ክፍል ለዚህ ደካማ የግብ ማስቆጠር ሪከርድ እንደ ምክንያትነት ሊነሳ ይገባዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ ወደ ግብ ደርሶ እና ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን ፈጥሮም ፍጥነት በሌለው ውሳኔ አሰጣጥ ምክንያት የግብ ሙከራ የማያደርግባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። 

በዛሬው ጨዋታም መከላከያ እነዚህን ችግሮቹን አርሞ ወደ ሜዳ መግባት ይጠበቅበታል። ሆኖም ነገሮች ቀላል ይሆኑለታል ተብሎ አይጠበቅም። እንግዶቹ መቐለዎች የአማካይ ክፍላቸው  ለተከላካይ መስመራቸው የሚሰጠው ሽፋን መሰል የማጥቃት ድክመት ላለበት ቡድን በቀላሉ ክፍተትን የሚሰጥ አይደለም። በደደቢቱ  ጨዋታ መከላከያ በማጥቃት ሂደት ላይ ሳለ የሚኖረው የተዛባ ቅርፅ ወደ መከላከል የሚያደርገውን ሽግግር ከባድ ሲያደርግበት እና ለመልሶ ማጥቃት ሲያጋልጠውም አስተውለናል። ይህ ደግሞ መቐለ ከተማዎች የያዟቸው ፈጣን የመስመር አማካዮች በመሰል አጋጣሚዎች የፊት አጥቂያቸውን በቅብብሎች ለማግኘት የሚያስችል አቅም ያላቸው በመሆኑ እንግዶቹ ኳስ ቀምተው ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል የሚገቡባቸውን አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር ወሳኝ ያደርጋቸዋል። ከፊታቸው የተደራጀ መከላከል የሚገጥማቸው የጦሩ የአማካይ እና የፊት መስመር ተሰላፊዎችም ፍጥነት ያላቸው እና ያልተዛነፉ የኳስ ቅብብሎችን በማድረግ አስከፍተው ዕድሎችን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *