አሰልጣኝ ብርሃኔ ገ/እግዚአብሔር ከወልዋሎ የተለያየሁበት መንገድ ተገቢ አይደለም በሚል ለፌዴሬሽኑ የቅሬታ ደብዳቤያቸውን አስገቡ።
አሰልጣኝ ብርሃኔ ወልዋሎን ከከፍተኛ ሊግ አንስቶ በማሰልጠን ቡድኑ ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ከማስቻላቸው ባሻገር በፕሪምየር ሊጉ እስከ አምስተኛው ሳምንት ድረስ መልካም የሚባል ጅማሮ ማድረግ ቢችሉም በተደጋጋሚ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ የክለቡ አመራሮችም ሆኖ ደጋፊዎች ተቃውሞ አስነስቶባቸው ከወልዋሎ አሰልጣኝነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል።
አሰልጣኝ ብርሃኔ ትላንት ለፌዴሬሽኑ ባስገቡት ደብዳቤ እስከ ሰኔ 30 2010 ድረስ ቡድኑን ለማሰልጠን ቢፈርሙም ክለቡ ከውላቸው ውጭ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ከጥር 15 ጀምሮ ማሰናበቱ ተገቢ እንዳልሆነ ገልፀዋል። አሰልጣኙ ማስተካከያ እንዲደረግ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ምላሽ በማጣታቸው ” ፌዴሬሽኑ በውሌ መሰረት መብቴን እንዲያስከብርልኝ ” በማለት የቅሬታ ደብዳቤያቸውን ማስገባታቸውን ገልፀዋል።
የወልዋሎ ክለብ አመራሮች አሰልጣኙ ባቀረቡት ቅሬታ ዙርያ ምላሽ እንዲሰጡን ደጋግመን ብንጠይቅም መልስ የሚሰጠን አካል ባለማግኘታችን በዚህ ዜና ላይ አካተን ማቅረብ አልቻልንም።