​ፋና ወጊው መሳይ ደጉ በእስራኤል ታሪክ ሰርቷል

በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የብሩክ ደጉን ያህል የደመቀ ታሪክ ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች የለም። አሁን ደግሞ የብሩክ ታናሽ ወንድም የሆነው መሳይ ደጉ በእስራኤሊ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ እጅግ ወጣቱ እና የመጀመርያው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ በመሆን ታሪክ መስራት ችሏል። የጄሩሳሌም ፖስቱ አሎን ሲናይ ስለ ወጣቱ አሰልጣኝ የእግርኳስ ህይወት ያሰፈረውን ጽሁፍ በዚህ መልኩ ወደ አማርኛ መልሰነዋል።


መሳይ 32ኛ አመቱን የደፈነው ከ6 ቀናት በፊት ነበር። የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ሀፖኤል አሽኬሎን ከሚመራው መሳይ ደጉ በእድሜ የሚያንስ አሰልጣኝ በእስራኤል ትልቁ ሊግ ታይቶ አይታወቅም። ትውልደ ኢትዮጵያዊ (ቤተ-እስራኤል/ፈላሻ) ሆኖ በዚህ ደረጃ አሰልጣኝ ሆኖ ስንመለከትም የመጀመርያው ነው። ምሉዕ ባልሆነው የእውነታ አለም ላይ ተመስርተን የመሳይን የስኬት ታሪክ ማሳነስ ትልቅ ስህተት ላይ ይጥለናል። የመሳይ ስኬት ለመንገር የሚያጓጓ ብቻ አይደለም ፤ በቤተ-እስራኤላዊያን ህይወት ላይ ትልቅ አዎንታዊ ተፅእኖ የሚፈጥርም ጭምር ነው። ገና በአሰልጣኝነት ህይወቱ መጀመርያ ላይ ቢገኝም ፋና ወጊ ነው። ገና ከወዲሁም መነሻውን እና የቆዳ ቀለሙን ለሚጋሩ ሁሉ ተፅእኖ ፈጣሪ ሆኗል። 

መሳይ የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ ፌብሪወሪ 15 ቀን 1986 ነበር። በ1990 በኦፕሬሽን ሰለሞን አማካኝነት ቤተ-እስራኤላዊያንን ወደ እስራኤል የማጓጓዝ ሒደት አካል በመሆን ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ እሰራኤል ያመራው መሳይ በእስራኤል ዝቅተኛ ዲቪዝዮኖች ከመጫወት ጎን ለጎን የባት-ያም መንገዶችን ንፅህና በመቆጣጠር ነው ህይወቱን የመራው። ስራውን የሚያከናውንባቸው የባት ያም መንገዶች ጭር ሲሉም ፈረቃው እስኪያበቃ ቁጭ ብሎ ሰአት ከመቁጠር ይልቅ የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላን የልምምድ ፕሮግራሞች በተንቀሳቃሽ ስልኩ በመመልከትና ማስታወሻ በመያዝ የማሰልጠን ክህሎትን ለማዳበር ጥሯል።

መሳይ የታላቅ ወንድሙ ብሩክ ስኬታማ ተጫዋችነት ዱካ የመከተል ህልሙን ሲያሳድድ ኖሯል። የቀድሞው የማካቢ ሀይፋ ኮከብ ከፈረንጆች ሚሌንየም የመጀመርያ አመታት ጀምሮ በእስራኤል ዝነኛው ተጫዋች ነበር። በ2004/05 የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ታላላቆቹ ባየርን ሙኒክ እና ጁቬንቱስ ላይ ጨምሮ 5 ጎሎች በስሙ የቻለው ብሩክ ከቤተ-እስራኤላዊያን ተጫዋቾች ምርጡ ነው። ብሩክ ለብዙ ቤተ-እስራኤላዊያን ተጫዋቾች ፈር የቀደደ ድንቅ ተጫዋች ቢሆንም ወንድሙ ግን እምብዛም የሚጠቀስ የተጫዋችነት ዘመን አላሳለፈም። በዝቅተኛ የእስራኤል የሊግ እርከኖች በአማካይ ስፍራ ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ በ2013 በቁርጭምጭሚት ጉዳት ምክንያት ከእግርኳስ ተጫዋችነት ሲገለል እድሜው 27 ብቻ ነበር።

እምብዛም የሚጠቀስ ታሪክ የሌለው የተጫዋችነት ህይወቱን ከደመደመ በኋላ በእግርኳስ ውስጥ መቆየትን በመፈለጉ የአፖኤል ወጣት ቡድንን በአሰልጣኝነት ተቀላቀለ። በሒደትም ራሱን ወደ አሰልጣኝነት በጥልቀት በማስገባት በ2016 የሀፖኤል ከፊር ሳባ አሰልጣኝ ሻሮን ሚመር ረዳት ሆኖ ስራ ጀመረ። ከሁለት ወራት በኋላ በውጤት ቀውስ የታመሰው ክለቡ ሻሮን ሚመርን ከኃላፊነት አንስቶ መሳይን እንዲቀጥል ሲያደርግ የመሳይ ህልም በፍጥነት እውን ሆነ።  ያልተረጋጋው ከፊር ሳባ ክለብ በውድድር አመቱ መጨረሻ ወደ ብሔራዊ ሊጉ የወረደ ሲሆን በወጪ ቅነሳ ላይ ያተኮሩት የክለቡ ባለቤት ስታቭ ሻቻም መሳይን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርገው በ2017 ክረምት ሾሙት። ይህ የሆነው ክለቡ በአስተማማኝ የፋይናንስ መሰረት ላይ የማይገኝ በመሆኑ መሳይ የሰራተኞች አገልግሎት ቢሮ በመሄድ የስራ አጥነት መብት እና ጥቅሞች እንዲከበሩለት በጠየቀ ማግስት ነበር። መሳይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በክለቡ ዙርያ ያሉ ሰዎችም የከፈር ሳባ እጣፈንታን የሚያውቅ አልነበረም።

መሳይ በከፈር ሳባ የዋና አሰልጣኝነት ስራውን ሲጀመር የተመደበለትን 1.5 ሚልየን ሸቀል (የእስራኤል የመገበያያ ገንዘብ) በማብቃቃት ቡድኑን መገንባት ነበረበት። ያም ሆኖ በችግር ላይ የነበረው ክለብ ድንቅ አጀማመር እንዲያደርግ ረዳው። ከመጀመርያዎቹ 9 ጨዋታዎች አንድ አቻ ብቻ በመለያየት ማግኘት ከሚገባው 27 ነጥብ 25ቱን መሰብሰብ ቻለ። ግቦች ለማስቆጠር የማይቸገር እና አዝናኝ እግርኳስ የሚጫወት ቡድን በመገንባቱም ሙገሳዎች ይጎርፉለት ጀመር። ሆኖም ከዛ በኋላ በተደረጉ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ማስተናገዱ ከክለቡ ጋር እህል ውሀው እንዲለያይ አደረገው።

አዲሱ የክለቡ ባለቤት ኢትዛክ ሸም መሳይን ለማሰናበት የወሰዱት እርምጃ በብዙ የእስራኤል እግርኳስ ተከታታዮች ዘንድ ያልተጠበቀ እና አስደንጋጭ ነበር። ቡድኑ ወደ እስራኤል ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ባለፈበት እና በሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ በጥሩ አቋም ላይ የነበረ ከመሆኑ አንፃር የሸም ውሳኔ አወዛጋቢ ነው። መሳይ ከከፋር ሳባ የተሰናበተው የክለቡ ባለቤት የልጅ ልጅ የሆነው ቶም ሼላች እንዲሰለፍ የቀረበለትን ትዕዛዝ እንደማይቀበል በመናገሩ መሆኑን ይገልፃል። የክለቡ ባለቤት ሸም ደግሞ ” የትኛውም ተጫዋች ከቡድኑ በላይ አይደለም። አሰልጣኝም ከባለቤቱ በላይ ሊሆን አይችልም። እሱ የተባረረው ለእኔ እና ለክለቡ ታማኝ ስላልነበረ ነው ” የሚል የማስተባበያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

መሳይ ይህን የመወቃቀስ ጨዋታ ለማቆም ሲጠር ቆይቷል። እንደውም የክፋር ሳባ የቁልቁለት ጉዞ ከመሳይ መልቀቅ በኋላ በግልፅ የሚታይ እንደመሆኑ ሸም በውሳኔያቸው የሚፀፀቱ ይመስላሉ። ቡድኑ ከመሳይ በኋላ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች 2 ነጥቦችን ብቻ ሰብስቦ ወደ ፕሪምየር ሊግ የመመለሱ ጉዳይ ያበቃለት መስሏል።
ከከፋር ሳባ ከለቀቀ በኋላ መሳይ ያለ ስራ አልተቀመጠም። ባለፈው ሳምንት በገዛ ፈቃዳቸው ከለቀቁት ዩቫል ናይም ጋር የተለያየው ሀፖኤል አሽከሎን ቀጣዩ የመሳይ ማረፍያ ሆኗል። አወዛጋቢው የከፋር ሳባ ባለቤት ውሳኔም ወጣቱን አሰልጣኝ ከናሽናል ሊግ ክለብ ወደ ፕሪምየር ሊግ ክለብ አሰልጣኝነት በፍጥነት አሳድጎታል። በአዲሱ ክለቡ የመጀመርያ ጨዋታውን ባለፈው ሳምንት እሁድ ያደረገው መሳይ ውጤቱ በሚመኘው መልኩ አልሆነለትም ፤ ካለፉት 18 ጨዋታዎች አንድ ብቻ ያሸነፈው አሽከሎንን እየመራ በገባበት የመጀመርያ ጨዋታ በአይረኒ ኪርያት ሸሞና 1-0 ተረትቷል። 

ክለቡ ሊጠናቀቅ ሶስት ጨዋታ በቀረው ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ደረጃ ከሚገኘው አሽዶድ በ4 ነጥቦች ርቆ በሊጉ የመቆየት ጭላንጭል ተስፋን ይዟል። ሆኖም መሳይ ተስፋ እንደማይቆርጡ ይናገራል። ” ህይወት በሊጉ ፈታኝ ነው። ነገር ግን በናሽናል ሊጉ ተመሳሳይ ፈተናን ከፋር ሳባ ጋር አሳልፌያለሁ። በቡድኑ ባልተማመን መጀመርያውኑም አልመጣም ነበር” ሲል ተስፋውን ገልጿል።

አሽከሎንን ከመውረድ ማትረፍ ከእርሱ አቅም በላይ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከመጣበት መንገድ እና ከቆዳ ቀለሙ አንፃር በአጭር የአሰልጣኝነት ህይወቱ ተስፋ የሚጣልበት እንደሆነ አሳይቷል። ከብዙ የህይወት ውጣ ውረዶች በኋላም መሳይ ወደፊት ለሚጋፈጣቸው ፈተናዎች በቀላሉ እጅ የሚሰጥ አይመስልም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *