​የአሰልጣኞች አስተያየት፡ ወላይታ ድቻ 1-0 ዚማሞቶ

በቶታል ካፍ ኮንፌድሬሽንስ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ወላይታ ድቻ ሀዋሳ ላይ ዚማሞቶን አስተናግዶ በቶጎዋዊ አራፋት ጃኮ ግብ ታግዞ በአጠቃላይ ውጤት 2-1 በማሸነፍ ወደ አንደኛው ዙር ማለፍ ችሏል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖችን አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

“ከእረፍት በኋላ ቡድኔ እኔ ካሰብኩት ውጪ ነው የተንቀሳቀሰው” የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሃ

ስለጨዋታው

ከእረፍት በፊት የነበረው ጨዋታ እጅግ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ኳስን ተቆጣጥረን ወደፊት ለመሄድ ያደረግነው ጥረት ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበር፡፡ ከእረፍት በኃላ ተነጋግረን ገብተን ነበር ፤ ነገር ግን መቀዛቀዝ ይታያል፡፡ እንደሚመስለኝ ከሆነ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት የደጋፊውንም ሁኔታ ስላዩ ውጤቱን ላለማጣት ባደረጉት ጥረት መሃል ላይ ክፍተት ነበረብን፡፡ ውጤት ለማስጠበቅ በማሰብ ተጫዋቾቻችን ወደኃላ አፈገፈጉ ፡፡ እረፍት ላይ ብዙ ነገር ተነጋግረናል፡፡ አሁንም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር እንዳለብን ማመን አለባችሁ የሚለው ነገር ለመናገር ጥረት አድርገናል፡፡  አንድ ግብ አስተማማኝ አይደለም፡፡

ማሸነፋችን እድሎችን ሊያሰኘን ይችላል፡፡ ሆኖም ያሸነፍነው በእድል አይደለም ፤ ተጫውተን ነው ያሸነፍነው፡፡ እነሱ (ዚማሞቶ) አንድ ኢላማውን የጠበቀ የሞከሩት የለም፡፡ እኛ ወደ እነሱ የግብ ክልል በሚፈለገው መጠን አለመሄዳችን እንጂ ከእረፍት በፊት ኳሱን ተቆጣጥረን በሚገባ ተጫውተናል፡፡ ከእረፍት በኃላ ውጤት ለማስጠበቅ በሚል ይመስለኛል እኔ ካልኩት ውጪ ነው የተንቀሳቀሱት፡፡

ስለ አረፋት ጃኮ እርዳታ ማጣት

እኔ የምከተለው አሰላለፍ 4-3-3 ነው፡፡ ተጫዋቾቹ የአቅም ጉዳይ ይመስለኛል ወደኃላ ይሳባሉ፡፡ ከለመዱት ነገር ለማውጣት ነው እኔ ትግሌ፡፡ ምንግዜም ለጃኮ ኳስ ሲሰጥ ሁለቱ ተመላላሾች ኳስ እንዳለበት ቦታ ቢያንስ ሁለት እና ሶስት ተጫዋቾች ቀርበውት እንዲያግዙት እና ተጨማሪ ግቦችን እንድናስቆጥር ነበር ፍላጎታችን፡፡

ስለቀጣይ የማጣሪያ ዙር 

ብዙ ክፍተቶች አሉብን፡፡ ባለን ክፍት ቦታ ለመተካት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተጎዱ ወደ አራት ተጫዋቾች አሉን፡፡ እነሱ አገግመው ሲመለሱ ክፍተቶቻችን ይሞላሉ፡፡ ማንም ይምጣ ማንም ከማንም ጋር ብንገናኝም አቅማችን በፈቀደ መልኩ ለመጫወት ክፍተቶችን ደፍነን እና ሰርተን እንመጣለን፡፡ አሁን ካያችሁት ጨዋታ የተሻለ ነገር ለማሳየት ሰርተን እንመጣለን፡፡

“ሁለተኛው አጋማሽ ተስፋ አስቆራጭ ነበር” የዚማሞቶ አሰልጣኝ አብደልጋኒ ምሶማ

ስለጨዋታው

ጨዋታውን አሸንፈዋል፡፡ አንድም የጠራ የግብ እድል በሙሉ 90 ደቂቃ ማግኘት አልቻሉም ነበር፡፡ በፍፁም ቅጣት ምት ነው ያስቆጠሩት፡፡ የእኔ ቡድን ያለቀላቸውን እድሎች አምክኗል፡፡ ዛሬ እድለኛ አልነበርንም፡፡ ድክመታችን ኳስ ቁጥጥር እና በቴክኒክ ላይ ነበር፡፡ ይህንን ነው ለማረም ጥረት የምናደረገው፡፡

ከሳምንት በፊት የተለየ ነበር ፤ አሁን እንዴት እንደሚጫወቱ ስላወቅን የተሻለ ለመንቀሳቀስ ችለናል፡፡ በቴክኒኩ ጥሩ ናቸው። ግን በታክቲክ ረገድ ወላይታ ድቻ ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡

ሜዳው ብዙ ሊሰራበት እና ጥገና ሊደረግበት ያስፈልጋል፡፡ ተጫዋቾች እዚህ ሜዳ ላይ ኳስን እየገፉ መሄድ አይችሉም፡፡ ቅብብሎች እየነጠሩ ይበላሹ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የግብ እድሎችን በመፍጠር በኩል መዳከም

በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ልንጫወት አልቻልንም፡፡ የግብ እድሎችንም ለመፍጠር አልቻልንም፡፡ ተጫዋቾቼ ተዳክመው ነበር፡፡ ከተዳከምክ እና የተለየ ተስጥኦ ከሌለህ ተስፋ ትቆርጣለህ፡፡ ቴክኒኩ አልነበረንም ስለዚህም ሁለተኛው አጋማሽ ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡

ስለፍፁም ቅጣት ምቱ

ለእኔ ተገቢ አልነበረም፡፡ አቅዶበት አልነበርም በእጁ የነካው፡፡ ህጉ የሚለው ታስቦበት በእጁ የነካ ቢሆን ኖሮ ተገቢ ይሆን ነበር፡፡ እኔ እንደማስበው ሆን ብሎ አልነካም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *