በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎውን እያደረገ የሚገኘው ወላይታ ድቻ የዛንዚባሩ ክለብ ዚማሞቶን ገጥሞ የመጀመሪያውን ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ከ10 ቀናት በፊት በማድረግ 1-1 ተለያይቶ መምጣቱ ይታወሳል፡፡ ዛሬ 10:00 ሰአት ላይ የመልስ ጨዋታውን አድርጎም 1-0 በማሸነፍ በድምር ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡፡
ምንም እንኳን ስቴዲየሙን መሙላት ባይችሉም የሀዋሳ ከተማ ፣ የሲዳማ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ደጋፊዎች በየክለቦቻቸው መለያ ድቻን ለመደገፍ በስቴዲየሙ የተገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ እና የክለቡ አስተዳዳሪዎች ተገኝተው ከተጫዋቾቹ ጋር ከተዋወቁ በኃላ ጨዋታው በጁቡቲያዊው የመሀል ዳኛ ሱለይማን አህመድ መሪነት ተጀምሯል።
በሁለት አይነት የአየር ፀባይ የታጀበው ጨዋታ በሙሉ ክፍለ ጊዜው ዚማሞቶዎች ግብ ለማስቆጠር ከወላይታ ድቻ በተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያሳዩበት ሲሆን በአንፃሩ ባለሜዳው ወላይታ ድቻ በሚያገኛቸው አጋጣሚወች በጃኮ አራፋት ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት ሂደትን የተገበረበት ነበር። በመጀመሪያወቹ አስር ደቂቃዎች እንግዳው ቡድን ዚማሞቶ የተሻለ የግብ አጋጣሚን መፍጠር ችሏል። በ7ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ኒያንጂ ኡታማን ከቀኝ የድቻ የግብ አቅጣጫ ያሻገረውን ኳስ በዛንዚባሩ ጨዋታ ለዚማሞቶ ግብ ያስቆጠረው ሀኪም ካሚስ አሊ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ የግራ ቋሚ ብረት መልሶበታል። እንግዶቹ አሁንም ቶሎ ቶሎ ከሁለቱም ኮሪደሮች በተደጋጋሚ የሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች ለወላይታ ድቻ የመስመር ተከላካዮች ፈተና መሆናቸው አልቀረም። ወላይታ ድቻዎች ብቅ ጥልቅ የሚል የማጥቃት ሙከራን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በተለይ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ በዛብህ መለዮ እንደተጠበቀው አለመሆን አጥቂው ጃኮ አራፋት ወደ መሀል እየተሳበ ወደእነ ሀይማኖት ወርቁ ቀርቦ እንዲጫወት ምክንያት ሆኗል። 13ኛው ደቂቃ ላይ አሙር አሊ ከግራ አቅጣጫ በአግባቡ ያሻገራትን ኳስ ኒያንጂ ኡታማን ከወንደሰን ገረመው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ወደ ውጭ ኳሷን ሰዷታል።
ወላይታ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት 15ኛው ደቂቃ ላይ በፈጠሩት አጋጣሚ ደግሞ ዘላለም እያሱ የሰጠውን ኳስ ጃኮ አራፋት በግንባሩ አግኝቷት ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ውጭ የወጣችበት የጦና ንቦቹ የመጀመሪያ የግብ አጋጣሚ ነበረች። በሂደት የግብ እድልን ለመፍጠር እና የዚማሞቶን የማጥቃት ሀይል በመረዳት የአጨዋወት ሲስተማቸውን ቀየር ያደረጉት ድቻዎች በኩል 16ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም እያሱ በግሩም ሁኔታ በአየር ላይ ያቀበለውን ኳስ በዛብህ መለዩ ቢያገኛትም በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ የዚማሞቶው ግብ ጠባቂ ናስር ሚሪሾ መልሶበታል። አሁንም ወላይታ ድቻዎች ለማጥቃት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ወጥ የሆኑ ኳሶችን ለመቀባበል ሲቸገሩ ተስተውሏል። በዚህም በ18ኛው ደቂቃ ዳግም በቀለ ከግብ ጠባቂው ጋር የተገናኘችን ኳስ ቢያገኝም ናስር ሚሪሾ ቀድሞ ደርሶ አስጥሎታል። ቀጥሎም ተጠቃሽ ለግብ የቀረበ ሙከራን ከቅጣት ምት በያሬድ ብርሀኑ አማካኝነት በ25 ኛው የተገኘ ሲሆን ሀይማኖት ወርቁ በግንባሩ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ናስር ሚሪሾ እንደምንም አውጥቶበታል፡፡
በ27ኛው ደቂቃ ግን በዛብህ መለዮ በረጅሙ ወደ ዚማሞቶ የግብ ክልል የላካትን ኳስ ተከላካዩ የሱፍ ረመዳን በሳጥን ውስጥ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ቶጎዋዊው ኢንተርናሽናል ጃኮ አራፋት አስቆጥሮ ወላይታ ድቻን መሪ ማድረግ ቻለ። ከግቡ መቆጠር በኃላ አሁንም በአንድ አጋጣሚ ጃኮ አራፋት ሁለተኛ የግብ ማግባት አጋጣሚን ቢያገኝም ሳይጠቀምበት የመጀመሪያው አጋማሽ በወላይታ ድቻ 1 ለ 0 የሆነ ውጤት ተገባዷል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች ያገኙትን ግብ አስጠብቆ ለመውጣት እና በመልሶ ማጥቃት በመጫወት ዚማሞቶወች በአንፃሩ አጥቅቶ በመጫወት ግብ አስቆጥሮ ለመውጣት ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱ ሲሆን በተለይ የመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ያሳደሩት ከፍተኛ ጫና ለወላይታ ዲቻ የተከላካይ መስመር ፈተና ሆኗል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የገቡት ድቻዎች ባደረጉት ሙከራ 47ኛው ደቂቃ ላይ በበዛብህ መለዮ ወደ ግብ በቀጥታ ወደ ሳጥን ገብቶ የሞከራትን ኳስ ጥሩ ሆኖ ያመሸው የዚማሞቶው ግብ ጠባቂ ናስር ሚሪሾ መልሶበታል። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የወላይታ ድቻው አጥቂ ዳግም በቀለ የሚያገኛቸውን ተደጋጋሚ ኳሶች በአግባቡ መጠቀም ያለመቻሉ የኃላ ኃላ ወላይታ ድቻን ዋጋ ለማስከፈል የተቃረቡ ነበሩ። ለዚህ ማሳያ 51ኛ ደቂቃ ላይ የዚማሞቶ ተከላካዮችን ሰህተት ተጠቀሞ ዳግሞ በቀለ ያገኛትን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ሳይችል የቀረበት እጅግ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበር። 71ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሀይማኖት ወርቁ በተከላካዮች መሀል አሳልፎ የሰጠውን ኳስ በዛብህ መለዮ ሳይደርስባት ቀርቷል።
ወላይታ ዲቻዎች በጥብቅ በተከላከሉበት እና ደጋፊው ከስቴዲየም ለቆ በወጣበት የመጨረሻወቹ አስር ደቂቃዎች ዚማሞቶወት በፍፁም የማጥቃት ሀይላቸው ተጠቅመው የድቻን የተከላካይ መስመር ለመስበር ጥረት ያደረጉበት ነበር። በተለይ አጥቂው ሀኪም ካሚስ አሊ በግሉ ከፊት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እና የሱፍ ረመዳን ከተከላካይ ስፍራ በመነሳት አቻ ሆኖ ለመውጣት የሳየው ከፍተኛ ጥረት ትኩረትን ይስብ ነበር። ሆኖም ወላይታ ድቻዎች ባስቆጠሩት አንድ ግብ በማሸነፍ በደርሶ መልስ ድምር ውጤት 2 ለ 1 ድል በማድረግ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል ፡፡ ወላይታ ድቻ ቀጣይ ሁለተኛ ማጣሪያውን ከግብፁ ሀያል ክለብ ዛማሌክ ጋር የሚያደርግ ይሆናል፡፡