የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የተላለፈበት ቅጣት ውሳኔ ተገቢ አይደለም በሚል ለፌዴሬሽኑ ይግባኝ ብሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከነማ ጋር ባደረገው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ በተፈጠረው ሁከት ሁለቱም ክለቦች ጥፋተኛ ሆነው አግኝቻቸዋለው በማለት የዲሲፒሊን ኮሚቴው ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ላይ ከበድ ያለ የቅጣት ውሳኔ ወስኗል ። ቅጣቱ ዝርዝር ነገሮች ቢኖሩበትም በዋናነት ቡድኑ በሜዳው የሚያደርገውን አንድ ጨዋታ በዝግ እንዲያደርግ እና የ180 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ነው የተወሰነበት።
ውሳኔውን ተከትሎ አንድ ጨዋታ በሜዳው ሲጫወት በዝግ እንዲሆን የተላለፈው ውሳኔ በየትኛው ጨዋታ ላይ እንደሆነ ፌዴሬሽኑ በግልፅ አላስቀመጠም ። ይህ በመሆኑም ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይ በየትኛው ጨዋታ ላይ ቅጣቱ ተግባራዊ እንደሚሆንበት ማወቅ የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል። ይህንን ሀሳብ በመያዝ ሶከር ኢትዮጵያ የክለቡን አመራር በማናገር አጭር ምላሽ አግኝታለች። በምላሹም ክለቡ በውሳኔው ዙርያ ውይይት አድረጎ ዛሬ ለፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይግባኝ እንዳቀረበ ተነግሮናል ።
ክለቡ ይግባኝ የጠየቀ በመሆኑ በቀጣይ ኮሚቴው የሚያስተላልፈው ውሳኔ የሚጠበቅ ቢሆንም በ12ኛ ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ከነገ በስትያ ከደደቢት ጋር የሚያደርገውን ወሳኝ ጨዋታ በዝግ እንደማያደረግ መገመት ተችሏል ።