በአለም እግር ኳስ ላይ ካሉ ውድድሮች ቀዳሚ ደረጃ ላይ የሚቀመጠው የአለም ዋንጫ ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል። በሰኔ ወር ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ከሚገኘው የአለም ዋንጫ ቀደም ብሎ በፊፋ እና የለስላሳ መጠጦች አምራች ድርጅት በሆነው በኮካ ኮላ አማካኝነት ዋንጫዋ ከመስከረም ወር መጀመሪያ ጀምሮ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ጉዞ እያደረገች መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ረፋድ 5 ሰዓት አዲስ አበባ ገብታለች።
በ1974 በምዕራብ ጀርመን አስተናጋጅነት በተከናወነው 10ኛው የአለም ዋንጫ ውድድር ላይ በጣሊያናዊው ዲዛይነር ሲልቪዮ ጋዛኒካ ተቀርጻ ለአሸናፊዎች መበርከት የጀመረችው ዋንጫ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት በ6 አህጉራት በሚገኙ 51 ሃገራት እና 91 ከተሞች ጉዞዋም ለማድረግ መርሃ ግብር መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ለሚመለከቷት የእግር ኳስ አፍቃሪያን ዋንጫዋን በቅርብ እርቀት ለመመልከት እና ፎቶ ለመነሳት የተሻለ አጋጣሚ መሆኑ ይታወቃል።
ዛሬ ረፋድ ከሱዳን ካርቱም ወደ አዲስ አበባ የገባችው ይህቺ ክቡር ዋንጫ ለሁለት ቀናት በሃገራችን እንደምትቆይ የተነገረ ሲሆን ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ ከደረሰች በኃላ ወደ ብሄራዊ ቤተመንግስት አምርታ ጥሪ ለተደረገላቸው ግለሰቦች እና የሚዲያ አባላት ባሉበት ይፋዊ አቀባበል ተደርጎላታል። 7 ሰዓት በጀመረው ይፋዊ የአቀባበል ስነ-ስርሃት የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት የተከበሩ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ የኢፌድሪ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስቲር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻን ጨምሮ የኮካ ኮላ እና የፊፋ ተወካዮች ባሉበት የተደረገ ሲሆን ለተመረጡ ሰዎች የፎቶ መነሳት ፕሮግራምም ተከናውኗል።
ፕሮግራሙ የተጀመረው የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ካምፓኒ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ሃቪየር ሲልጋ አልኮቬራ ንግግር ሲሆን ከስምንት አመት በኃላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ዋንጫው በመምጣቱ ደስተኛ መሆናቸውን እና የእግር ኳስ አፍቃሪው ህብረተሰብ የደስታውን ስሜት እንዲያጣጥም በመጋበዝ የዋጫውን ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ፋይዳ አስረድተዋል። “ዋንጫው እዚህ በመምጣቱ ልትደሰቱ ይገባል።በተለይ ወጣት እና ታዳጊ ተጨዋቾች እጅግ ይበረታታሉ ብለን እናምናለን። ኢትዮጵያ በአለም ደረጃ በአትሌቲክሱ እንደምትታወቅ በደንብ እናቃለን ነገር ግን በእግር ኳስም እንደዚሁ ለመታወቅ ጠንካራ ስራዎችን መስራት አለባችሁ።”ብለዋል
በመቀጠል የኢፌድሪ የወጣቶ እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስቲር ክብር አቶ ርስቱ ይርዳው እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ዋንጫው ወደ ሃገራችን በመምጣቱ ደስተኛ መሆናቸውን በመግለፅ ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ያደረጉት ፊፋ እና ኮካ ኮላን አመስግነዋል። አቶ ጁነይዲ ባሻ በተለይ ኮካ ኮላ ከፌደሬሽኑ ጋር እየሰራ ባለው የታዳጊዎች ፕሮጀክት ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን ተተኪ እግር ኳስ ተጨዋቾችን ለማፍራት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በስተመጨረሻ ባደረጉት ንግግር “በአለም የስፖርት ውድድሮች ውስጥ የሚሊየኖችን ስሜት በመግዛት የቅድሚያውን ድርሻ የሚይዘው የፊፋ የአለም ዋንጫ እንዲዘዋወርባቸው ከተመረጡ አስር የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ስለሆነ ሁላችንም ደስ ይለን ይገባል።
“ዋንጫውን በአካል ማየት በህይወት ዘመን ብዙ ጊዜ ሊያጋጥም የማይችል እድል እንደመሆኑ ለብዙዎቹ የእግር ኳስ ደጋፊዎች የዋንጫውን አቀባበል ስነ ስርአት ዋጋው የት ድረስ ከፍ ያለ መሆኑን እንረዳለን። በተለይም ደግሞ አብዛኛው ህዝቧ ወጣት ወደሆነባት ኢትዮጵያ መምጣቱ የሃገራችን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በአለም ውድ የሆነውን ሽልማት በቅርበት ለማየት እና ደስታውን ለመካፈል የሚችሉበትን እድል ይፈጥራል።”
ከንግግራቸው በኃላ ፕሬዝዳንቱ ከፊፋ ዙሪክ ማርኬቲንግ ማኔጀር ሉካስ ራቾ የአለም ዋንጫውን የሚመስል ግን አነስ ያለ ዋንጫ በስጦታ መልክ የተበረከተላቸው ሲሆን ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኃላ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ፕሮግራሙ ከመጠናቀቁ በፊት ፕሬዝዳንቱ ዋንጫዋን በይፋ አንስተው ለታዳሚያኑ ያሳዩ ሲሆን ከዋንጫው ጋርም ከተመረጡ እንግዶች ጋር ፎቶ ተነስተዋል።
ነገ በጊዮን ሆቴል ለ10000 የእግር ኳስ አፍቃሪያን ክፍት ሆኖ የፎቶ መነሳት ፕሮግራም ይኖራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ስነ ስርዓት መሰረዙ የተገለፀ ሲሆን ለ3000 የእግር ኳስ አፍቃሪያን እና ለተመረጡ ግለሰቦች ብቻ በሂልተን ሆቴል ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተጠቁሟል።