​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ |  ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ደደቢት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ የአምናው ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የወቅቱ የሊጉ መሪ ደደቢት የሚገናኙበትን ተጠባቂ ጨዋታ ያስተናግዳል። 

ቦታ- አዲስ አበባ ስታድየም

ቀን- እሁድ የካቲት 18 2010

ሰዐት- 10፡00

ዳኞች፡ ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ (ኢንተርናሽናል)

ረዳት ዳኞች ክንዴ ሙሴ (ኢንተርናሽናል) እና ትግል ግዛው (ኢንተርናሽናል)

የቅርብ ጊዜ ውጤቶች

ቅዱስ ጊዮርጊስ| አቻ-አቻ-ተሸ-አሸ-አቻ

ደደቢት| አሸ-ተሸ-አሸ-አሸ-አሸ

ጨዋታው ቀድሞ በተያዘለት የ12ኛ ሳምንት መርሀ ግብር ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ አጓጊነቱ ከዚህም በላይ ከፍ ባለ ነበር። በዛን ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ ሽንፈት ሳያስተናግዱ የሚገናኙበት ዕድል የነበረ ሲሆን ደደቢት ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ካሸነፈ በኃላ የሚደረግ በመሆኑም የቡድኑ አስገራሚ ግስጋሴ በቅዱስ ጊዮርጊስ ይገታል ወይስ እንዳስደመመን ይቀጥላል የሚለው ጥያቄ መልስ በእግር ኳስ አፍቃሪውን ዘንድ ሲጠበቅ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ቀን ከአንድ ወር በላይ መራዘም በኃላ ዛሬ ላይ ቢደርስም የክለቦቹን የዋንጫ ጉዞ የመወሰን ሀይል ያለው እንደመሆኑ አሁንም የበርካቶችን ቀልብ መግዛቱ አልቀረም። 

ከ11ኛው ሳምንት በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሶዶ አምርቶ በወላይታ ድቻ እንዲሁም ደደቢት አዲስ አበባ ላይ ጅማ አባ ጅፋርን አስተናግዶ ሁለቱም በተመሳሳይ 2-1 ውጤት የአመቱን የመጀመሪያ እና ብቸኛ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል። ከዛሬው ጨዋታ አስቀድሞ ይህን ሽንፈት የሚያስረሳ ድል ማግኘት የቻለው ደደቢት በመጨረሻ ጨዋታው መከላከያን 4-0 ማሸነፍ ሲችል ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ከድሬደዋ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጋር ያደረጋቸው ሁለት የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። በመሆኑም ከወቅታዊ አቋም አንፃር ደደቢት የተሻለ ግምት እንዲያገኝ አድርጓል። 

በሌላ በኩል የዛሬው ተጠባቂ ጨዋታ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቡድን ጥቂት ግብ ካስተናገደ ቡድን የሚያገናኝ ነው።  ከጀመሪያዎቹ አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ግብ ሳያስቆጥር ከሜዳ የወጣው ደደቢት ከዚያ በኃላ ግን በአንድም ጨዋታ የተጋጣሚውን መረብ መድፈር ተስኖት አልታየም። ቡድኑ ሲዳማ ላይ አምስት ግቦችን ያዘነበትን ጨዋታ ጨምሮ እስካሁን 24 ግቦችን አስቆጥሯል። በሌላ በኩል ቅዱስ ጊዮርጊስ  ከመቐለ ከተማ ጋር በመሆን በሊጉ ዝቅተኛ የግብ መጠን (6) ያስተናገድ ክለብ ነው። ከነዚህ ስድስት ግቦች አራቱ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች የተቆጠሩ መሆናቸው ቡድኑን የሚያሰጋው ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታን ጨምሮ ከስድስተኛው ሳምንት እስከ 11ኛው ሳምንት በተደረጉ ሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት ከሜዳ መውጣት ችሏል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ደደቢትን በኢትዮጵያ ፕሪምየሪ ሊግ መመልከት ከጀመርንበት 2002 ጀምሮ ሁለቱ ቡድኖች 16 ጊዜ ተገናኝተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ሻምፒዮን በሆነባቻው ያለፉት አራት አመታት አንዴም በደደቢት ያልተሸነፈ ሲሆን የደደቢት የመጨረሻ ድል የተመዘገበው ቡድኑ ዋንጫ በነሳበት የ2005 የውድድር ዘመን 3-1 ባሸነፈበት ወቅት ነው። አምና 2-0 እና 3-2 በሆኑ ውጤቶች የዛሬ ተጋጣሚውን ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን በ11 ጊዜ ድል ቅድሚያውን ሲወስድ ደደቢት ሶስት ጊዜ አሸንፎ ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሆነዋል። በአማካይ 2.8 ግቦች በተቆጠሩባቸው በእነዚህ 16 ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 28 እንዲሁም ደደቢት 17 ጊዜ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችለዋል። 

የቡድን ዜናዎች

ከጉዳት አንፃር በሁለቱም ክለቦች በኩል መልካም ዜና ነው ያለው። አራት የሚደርሱ ተጨዋቾቹ የረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ይገኙ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከናትናኤል ዘለቀ በቀር ሌሎቹ ወደ ሜዳ እየተመለሱለት ይገኛል። አሜ መሀመድ የአዳማውን ጨዋታ የጀመረ ሲሆን ታደለ መንገሻንም በዚሁ ጨዋታ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተመልክተነዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሳልሀዲን ሰይድ ከቡድኑ ጋር ሙሉ ልምምድ እየሰራ ሲሆን መጠነኛ ጉዳት ገጥሞት የነበረው አስቻለው ታመነም ለዛሬው ጨዋታ እንደሚደርስ ይጠበቃል። በደደቢት በኩል ከአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ቅጣት ውጪ ብቸኛው ከጨዋታ ውጪ የሚሆነው ተጨዋች በጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ የቀይ ካርድ ሰለባ የሆነው ጌታነህ ከበደ ነው። ከዚህ ውጪ አቤል ያለው እና አስራት መገርሳ ለዛሬው ጨዋታ እንደሚደርሱ ይጠበቃል።  


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ

ከአጨዋወት ምርጫ አንፃር ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ከኃላ መስርተው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በመግባት ዕድሎችን ለመፍጠር ቅድሚያ ይሰጣሉ። የቡድኖቹ የማጥቃት ሂደት የኳስ ቁጥጥራቸውን ተከትሎ በአብዛኛው ወደ መስመር አጥቂዎቻቸው በሚላኩ ኳሶች ላይ የተመሰረተ መሆኑም በመጠኑ የሚያመሳስላቸው ሌላኛው ነጥብ ነው። ሆኖም ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደተጋጣሚዎቹ አቀራረብ እና እንደ ጨዋታው ሂደት በረዥሙ ወደ ተጋጣሚ የመከላከል ዞን የሚጥላቸው ኳሶች እንዲሁም ደደቢት ከአማካይ ክፍሉ ወደ አጥቂዎቹ ኳስን የሚያሰራጭበት አንፃራዊ ፍጥነት በቡድኖቹ መሀከል ከሚታዩ የአጨዋወት ልዩነቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሰልጣኝ ቫዝ ፒኒቶ ስር ሆኖ እየተከተለ ባለው የጨዋታ አቀራረብ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ አስጨንቆ በርካታ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገር ይስተዋላል። ቡድኑ ያስቆጠራቸው አብዛኛው ግቦችም የተገኙት ከቆሙ ኳሶች መነሻነት እና በቀጥተኛ አጨዋወት ከሚፈጠሩ ዕድሎች መሆኑ የቡድን ውህደቱ ከተፈለገው የአጨዋወት ዘይቤ ጋር ተጣጥሞ እንዳላለቀ የሚያሳይ ነው። የተጨዋቾች ጉዳት ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀስ ሲሆን ቡድኑ ጥሩ መግባባት ላይ የደረሰ ምርጥ 11 እንዳይኖረው እና አጨዋወቱም በድግግሞሽ እየተሻሻለ እንዳይመጣ ያደረገ ይመስላል።

የመስመር ተከላካዮቹን የማጥቃት ተሳትፎን ጨምሮ የፈረሰኞቹ ሶስቱ አማካዮች እና የመስመር አጥቂዎች የቦታ አያያዝ በተጋጣሚ አጋማሽ ላይ በርካታ የተሳኩ ቅብብሎችን ለማድረግ በሚያመች ቅርፅ እና ርቀት የተበጀ ባለመሆኑ በተለይ ጠንካራ የመከላከል መሰረት ካላቸው ቡድኖች ጋር ሲገናኝ እንዲቸገር አድርጎታል። ታታሪ አማካዮችን ይዘው እና የመሀል ክፍላቸው ላይ በቁጥር በዝተው ለተከላካይ መስመራቸው በቂ ሽፋን በመስጠት በተመሳሳይ አቀራረብ የገጠሙት ወላይታ ድቻ እና ድሬደዋ ከተማ ይህን ችግሩን በጉልህ አሳይተዋል። መሰል ጥንቃቄ የነበረው እና በማጥቃቱ በኩል የተሻለ ድፍረት ያሳየው አዳማ ከተማ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ የመሀል ክፍል ብቻ ሳይሆን የኃላ መስመር ድክመትንም ያጋለጠ ነበር። በመሆኑም በተለይ በማጥቃት ሂደቱ ላይ የዛሬው ጨዋታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንደሰሞኑ ሁሉ ቀላል እንደማይሆን መገመት ይቻላል።

የደደቢት የውድድር ዘመን ከተከታታይ ድሎቹ እና ካስቆጠራቸው በርካታ ግቦች አንፃር በአመዛኙ በጥሩ ጎኑ የሚነሳ ነው። ከዛሬ ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ የአማካይ ክፍል ውህደት መያዙ እና የተሻለ የግብ አስቆጣሪዎች ስብጥር ያለው መሆኑ በማጥቃቱ ረገድ የበላይ እንዲሆን አድርጎታል። ሆኖም ቡድኑ የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ እንዲሁም የጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴዎቹ እንደሚያሳዩን በተጋጣሚ ጫና ውስጥ የሚወድቅባቸው እና የተመጣጠነ የሚባለው የቡድኑ ቅርፅ የሚፋለስባቸው አጋጣሚዎችም እንዳሉ መናገር ይቻላል። እነዚህ ሁኔታዎች እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለ በከፍተኛ የአሸናፊነት ስነልቦና ላይ ከተመሰረተ ቡድን ጋር ሲጫወት በቀላሉ አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ግልፅ ነው። 

ደደቢት ላይ ሊነሳ የሚገባው ሌላው ወሳኝ ነጥብ የተጨዋች ምርጫው ነው። በዚህ ረገድ ቡድኑ መንታ መንገድ ላይ የቆመ ይመስላል። ስድስቱን ጨዋታ ሲያሸንፍ ዋና ተዋናይ ከነበሩ ተጨዋቾች መሀከል ሰለሞን ሀብቴ ፣ አቤል እንዳለ ፣ የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል ያለው በዘንድሮው የውድድር አመት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ መግባት የጀመሩ ሲሆኑ በወጥነት መሰለፋቸውም ለነበራቸው የሜዳ ላይ መግባባት ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። ሆኖም ከጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ እና በመከላከያው ጨዋታ  የአንጋፋዎቹ ብርሀኑ ቦጋለ ፣ ፋሲካ አስፋው እና ኤፍሬም አሻሞ ተፅዕኖ ከፍ ብሎ ታይቷል። ይህ ሁኔታም ቡድኑን ከየአብስራ ተስፋዬ በቀር ለሌሎቹ ወጣት ተጨዋቾች ከሽንፈት በኃላ ተጨማሪ ዕድልን በመስጠት እና በአንጋፋዎቹ በመቀጠል መሀል እንዲቀመጥ ያደረገው ይመስላል። እንደዛሬው ላለ ወሳኝ ጨዋታም የትኞቹ ተጨዋቾች ተመራጭ እነደሚሆኑ ለመወሰን ቀላል አይመስልም። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

አብዱልከሪም መሀመድ – ሳላዲን ባርጌቾ – አስቻለው ታመነ – አበባው ቡታቆ

አብዱልከሪም ኒኪማ – ሙሉአለም መስፍን – ምንተስኖት አዳነ

በሀይሉ አሰፋ – አቡበከር ሳኒ – ጋዲሳ መብራቴ

ደደቢት (4-3-3)

ክሌመንት አዞንቶ

ስዩም ተስፋዬ  – ደስታ ደሙ – ከድር ኩሊባሊ – ብርሀኑ ቦጋለ

ፋሲካ አስፋው – አስራት መገርሳ – የአብስራ ተስፋዬ

ሽመክት ጉግሳ – አቤል ያለው – ኤፍሬም አሻሞ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *