ከ17 አመት ቡድናችን ነገ ጋቦንን ይገጥማል


የኢትዮጰያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን (ቀይ ቀበሮዎቹ) በ2015 በኒጀር አስተናጋጅነት በ8 ሃገራት መካከል ለሚካሄደው ከ17 አመት በታች የአፍሪካ ለማለፍ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ነገ ከጋቦን ከ17 አት በታች ብሄራዊ ቡድን ጋር ያካሂዳል፡፡

በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እና ምክትሉ መሃመድ ኢብራሂምየሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄረዊ ቡድን ለ3 ሳምንታት በሃዋሳ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ በዚህ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ኢትዮጵያ ሆቴል ተቀምጦ ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡

አሰልጣኞቹ እና የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ስለ ዝግጅታቸው እና ስላጋጠሟቸው ፈተናዎች ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ምርጫው ዘንድሮ ከተካሄደው የ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ በርካታ ተጫዋቾችን ባለማካተቱ ዙርያ የተሰማውን ቅሬታ አስተባብለው በእድሜ ችግር እንዳልተመረጡ ተናግረዋል፡፡ በMRI ተመርምረዋል የተባሉት ተጫዋቾች እድሜም ጥርጣሬ የሚያስነሳ እንደሆነ ተገልጧል፡፡

አሰልጣኙ በጋዜጣዊ መግለጫቸው መሰረታዊ ስራዎችን ለመስራት እንደሞከሩ እና የስነ ልቦና ዝግጅት እንዳደረጉ የገለፁ ሲሆን ስለ ጋቦን ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ግን ከህዝብ ብዛቷ እና በታዳጊዎች ላይ የመስራት ጥሩ ልምድ እንዳላት ከማወቅ ውጪ ስለ ቡድኑ መረጃ እንደሌላቸው ገልጠዋል፡፡

የኢትዮጰያ ተጋጣሚ የጋቦን ብሄራዊ ቡድን ረቡእ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን ሀሙስ እና አርብ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ልምምድ ሰርተዋል፡፡

ጨዋታው ነገ ከቀኑ በ10 አሰት የሚጀምር ሲሆን በደርሶ መልሱ አሸንፎ የሚያልፍ ቡድን ቀጣዩን የማጣር ጨዋታ የፊፋ እገዳ የተነሳላት ናይጄርያ እና ኮንጎ አሸናፊ ጋር ይጫወታል፡፡

ያጋሩ