የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ ሲደረጉ ደደቢት ፣ ወላይታ ድቻ ፣ ድሬዳዋ ፣ አአ ከተማ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ አሸንፈዋል።
ቅዳሜ 08:00 ላይ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ደደቢት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-1 አሸንፏል። በመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ተሽለው የታዩት ደደቢቶች በታዲዮስ አዱኛ ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል ። ኤሌትሪኮች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ኳሱን በሚገባ አደራጅተው ወደ ጎል የሚያደርጉት ሽግግር ዝቅተኛ በመሆኑ ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በአንፃሩ የደደቢትን የጨዋታ እንቅስቃሴ እና ሚዛን በመጠበቅ ጥሩ በሚንቀሳቀሰው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች እና የቡድኑ አምበል በሆነው 8 ቁጥር ለባሹ መድሃኔ ካህሳይ አማካኝነት ለአጥቂዎች በሚያደርሳቸው ጥሩ ኳሶች ውጤታማ መሆን የቻሉ ሲሆን ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራታቸው አስቀድሞ ምስጋናው መኮንን በጥሩ ሁኔታ ባስቆጠራት ሁለተኛ ጎል ታክሎ ደደቢቶች 2-0 እየመሩ እረፍት ወተዋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው ወደ ሜዳ የገቡት ኤሌክትሪኮች በሄኖክ ሞላ አማካኝነት ባስቆጠሩት ግሩም ጎል ውጤቱን ማጥበብ ሲችሉ ተጨማሪ ጎል ፍለጋ ተጭነው ቢጫወቱም ኢላማውን የጠበቀ ግልፅ የጎል እድል መፍጠር የቻሉት ደደቢቶች ነበሩ። ጨዋታውም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድበት ተጠናቋል ። ከደደቢት በኩል ምስጋናው መኮንን ከኢትዮ ኤሌትሪክ ደግሞ ሄኖክ ሞላ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳይተዋል።
10:00 በቀጠለው የእለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በአአ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል በተካሄደው ጨዋታ በስፍራው የነበረውን ተመልካች ያዝናና ጠንካራ ፉክክር ተደርጎበት በአአ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ ቁጥጥር ከጥሩ ከማይቋራረጥ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጋር ባስተናገደው በዚህ ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ነበሩ። በግምት 17 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ይበቃል ፈረጃ ወደ ጎልነት በመቀየር አአ ከተማ መምራት ችሏል። የተሰጠው ቅጣት ምት ሁለተኛ ቅጣት ምት ነው የገባው ጎል መፅደቅ የለበትም በማለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች የዳኛውን ውሳኔ ተቃውመዋል። ፈረሰኞቹ አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን ፍ/ቅ/ምት ቢያገኙም በዘንድሮ አመት ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለው የግራ መስመር ተከላካዩ ሳሙኤል ተስፋዬ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ኳሱን በማዳን ረገድ የአአ ከተማው ግብ ጠባቂ ናትናኤል ተፈራ ብቃት ጥሩ የሚባል ነበር።
በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መልካም ነገሮች መመልከት በቀጠለበት ሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ከፍለ ጊዜ የተጨዋች ለውጥ በማድረግ እና ወደ ዋናው ቡድን አድገው ተመልሰው ከ20 አመት በታች እየተጫወቱ በሚገኙት ተስፋዬ በቀለ እና አቤል አምበሴ የግል ጥረት ታክሎበት ፈረሰኞቹ ተጭነው እየተጫወቱበት በነበረው አጋጣሚ ኢብራሂም በያና ከቀኝ መስመር የተሻገረለት ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠራት ጎል ፈረሰኞቹ አቻ መሆን ችለዋል። ፍክክሩ ተጋግሎ በቀጠለበት ሁኔታ ወደ ጨዋታው መገባደጃ አካባቢ ከመስመር በጥሩ ሁኔታ የተሻገረለትን ኳስ ተቀይሮ የገባው ብሩክ ሰሙ ጎል አስቆጥሮ አዲስ አበባዎችን መሪ ማድረግ ችሎ ጨዋታው በአአ ከተማ 2 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። አወዛጋቢነት የበዛበት የዳኝነት ውሳኔ በታየበት በዚህ ጨዋታ የፈረሰኞቹ ተጨዋቾች ከዕለቱ ዳኛ ጋር በፈጠሩት አላስፈላጊ ክርክር ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ተስፋዬ በቀለ በዕለቱ ዳኛ የቀይ ካርድ ሊመለከት ችሏል።
በስታድየሙ የነበረው በርካታ ተመልካች በወጣቶቹ ጨዋታ ተደስቶ ሲወጣ ተጨዋቾቹም ላይ በብዙ ተመልካች መሀከል መጫወት ጥሩ ስሜት እንደፈጠረባቸውና የመጫወት ፍላጎታቸውን እንደጨመረው ገልፀዋል። ፌዴሬሽኑም በቀጣይ ብዙ ተመልካች በሌለበት እና ከእይታ በራቀ ሁኔታ እንዲሁም አመቺ ባልሆነ ሜዳ ከሚያደርግ ቅዳሜና እሁድ ከፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ አስቀድሞ ቢያጫውታቸው መልካም እንደሆነ ገልፀዋል።
የ6ኛ ሳምንት ውጤቶች
ምድብ ሀ
ቅዳሜ የካቲት 17 ቀን 2010
ኢትዮጵያ ቡና 2-2 መከላከያ
ዕሁድ የካቲት 18 ቀን 2010
አዳማ ከተማ 1-1 ጭላሎ
ጥሩነሽ ዲባባ 1-0 ኢትዮጵያ መድን
አካዳሚ 0-4 ድሬዳዋ ከተማ
ምድብ ለ
ቅዳሜ የካቲት 17 ቀን 2010
ደደቢት 2-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
አዲስ አበባ ከተማ 2-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ
ዕሁድ የካቲት 18 ቀን 2010
ወላይታ ድቻ 5-0 ሲዳማ ቡና