ብሄራዊ ሊጉ ወደ ወሳኝ ምእራፍ ተሸጋግሯል

 

ከሀምሌ 25 ሀጀምሮ በድሬዳዋ እተካሄደ የሚገኘው የብሄራዊ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የምድብ ጨዋታዎችን ወደ ማገባደዱ እየደረሰ ነው፡፡ ነገ 4ኛ ጨዋታዎች የሚጠናቀቁ ሲሆን ቅዳሜ የምድብ ጨዋታዎች ተጠናቀው ወደ ሩብ ፍጻሜው የሚያልፉ ቡድኖች ይለያሉ፡፡

እስካሁን በተደረጉት ጨዋታዎች ጅማ አባ ቡና ከምድቡ ማለፉን ቀድሞ ያረጋገጠ ክለብ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከምእራብ ዞን የመጣው ጅማ አባ ቡና ዛሬ ጠዋት ባደረገው ጨዋታ ሱሉልታ ከነማን 1-0 በማሸነፍ በ10 ነጥብ ከምድቡ ማለፉን አረጋግጧል፡፡ በጳውሎስ ጌታቸው የሚሰለጥነው ሱሉልታ ከነማም ሽንፈቱን ተከትሎ ከምድቡ መሰናበቱን አረጋግጧል፡፡

በዚህ ምድብ በ7 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አአ ከነማ እና በ6 ነጥ 3ኛ ደረጃ ላይ ያለው ባቱ ከነማ ከጅማ አባ ቡና ጋር ለማለፍ ተፋጠዋል፡፡ ባቱ ከሱሉልታ ሲጫወት አዲስ አበባ ደግሞ ከጅማ አባ ቡና ይጫወታሉ፡፡ በመጨረሻው ጨዋታ እርስ በእርስ የሚጫወቱት ናሽናል ሴሜንት እና ሻሸመኔ ከነማ ከምድቡ ለማለፍ ጠባብ እድል ይዘው ይፋለማሉ፡፡

ከምድብ 1 ፋሲል ከነማ ፣ ድሬዳዋ ከነማ እና ፌዴራል ፖሊስ ተፋጠዋል፡፡ ትላንት አቻ ወደ ተከታዩ ዙር ያሳልፈው የነበረው ፋሲል ከነማ በፌዴራል ፖሊስ በመሸነፉ የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች በጉጉት እንዲጠበቁ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይም ድሬዳዋ ከነማ ከ ፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍፃሜ ግጥሚያ ያልተናነሰ ፉክክር ይካሄድበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፋሲል ካሸነፈ አልያም አቻ ከወጣ ወደ ሩብ ፍፃሜ የሚያልፍ ሲሆን ከተሸነፈ ግን የፌዴራል ፖሊስን ውጤት ይጠብቃል፡፡ ድሬዳዋ ከነማም ማሸነፍ ወደ ተከታዩ ዙር ሲያሳልፈው አቻ እና ሽንፈት ግን የፌዴራል ፖሊስን ውጤት እንዲጠብቅ ያስገድደዋል፡፡ ከምድቡ መሰናበቱን ያረጋገጠው አርሲ ነገሌን የሚገጥመው ፌዴራል ፖሊስ መሸነፍ ወደ ተከታዩ ዙር ያሳልፈዋል፡፡ አቻ ደግሞ የፋሲል እና ድሬዳዋን ውጤት እንዲጠብቅ ያስገድደዋል፡፡ ወልዋሎ ከቡራዩ ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ለመርሃ ግብር ማሟ ብቻ የሚደረግ ይሆናል፡፡

የምድብ 3 እና 4 አራተኛ ጨዋታዎች ነገ የሚደረጉ ሲሆን ወደ ቀጣዩ ዙር አላፊውን ቡድን ፍንጭ ይጣሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ዛሬ ከምድብ 3 በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ጅማ ከነማ መቐለ ከነማን 3-1 በማሸነፍ የምድቡ መሪ መሆን ችሏል፡፡ ነገ ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸው ሀላባ ከነማ እና ደ/ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርጉት ጨዋታም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ ከምድብ 4 ደግሞ ሶስቱም ጨዋታዎች የምድቡን እጣ ፈንታ የመወሰን አቅም አላቸው፡፡ አውስኮድ መድንን ፣ ሆሳእና ከነማ መሰናበቱን የረጋገጠው ውሃ ስፖርትን የሚያሸንፉ ከሆነ ማለፋቸውን ከ90 በመቶ በላይ ያረጋግጣሉ፡፡ በተቃራኒው ደቡብ ፖሊስ ፣ መድን እና ውሃ ስፖርት ተጋጣሚዎቻቸውን ካሸነፉ ከዚህ ቀደም እንደተገመተውም ምድብ 4 ትክክለኛው የሞት ምድብ ይሆናል፡፡

ከጨዋታዎቹ ጎን ለጎን የውድድሩ ስነ ስርአት ኮሚቴ 2 ዳኞችን ጨዋታ በአግባቡ አልመሩም በሚል ከውድድሩ አሰናብቷቸዋል፡፡ አርቢቴር ዘካርያስ እና አርቢቴር ለሚ ከውድድሩ የተሸኙ ሲሆን በምትካቸው 2 ዳኞች መመደባቸውም ታውቋል፡፡

የውድድሩ 5ኛ ጨዋታዎች የቡድኖችን እጣ ፈንታ የሚለዩ ፍልሚያዎች በመሆናቸው በተመሳሳይ ሰአት ሊካሄዱ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ ለጨዋታዎቹም ከዚህ በፊት በዝናብ ምክንያት ተሰርዚ የነበረው ሳቢያን ሜዳ እና አንድ ጨዋታ ተደርጎበት የነበረው የመከላከያ ሜዳ ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ያጋሩ