የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ ከሙሉ የበላይነት ጋር 4-1 በማሸነፍ ከተከታታይ 7 ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር ታጅቦ በተጀመረው ጨዋታ ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ አአ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ 1-1 ከተለያየበት ጨዋታ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርጎ ፍሬው ሰለሞንን በፍርዳወቅ ሲሳይ ምትክ በማስገባት ወደ ሜዳ ሲገባ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ደደቢትን ገጥሞ ያለምንም ግብ ካጠናቀቀው ስብስብ በኃይሉ አሰፋን በኢብራሂማ ፎፋና ምትክ በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል። በሙሉው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሀዋሳ ከተማ የእንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራ የበላይነት የተስተዋለበት ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍፁም ደካማ ሆኖ የታየበት ነበር።
ሀዋሳዎች ጨዋታው እንደተጀመረ ገና በ56ኛው ሰከንድ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ እስራኤል እሸቱ ሞክሮ ወደ ውጪ በወጣበት ሙከራ ፈረሰኞቹን መፈተን የጀመሩ ሲሆን በ11ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን ላይ አበባው ቡጣቆ በሰራው ያልተገባ አጨዋወት የእለቱ ዋና ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በዝምታ ማለፋቸውን ተከትሎ የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ውሀ ያዘለ ኮዳ በመወርወር በዳኛው ላይ ተቃውሞን አሰምተዋል። ጨዋታው በዚህ መልክ ቀጥሎ 13ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉአለም ረጋሳ ከቅጣት ምት በረጅሙ ያሻገራትን ኳስ ተጠቅሞ ፍሬው ሰለሞን ወደ ግብ ቢመታትም ሮበርት ኡዶንካራ አውጥቶበታል፡፡
በአማካዮቹ ሙሉአለም ፣ ፍሬው እና ታፈሰ ልዩ ብቃት ታግዞ ሀዋሳ እጅግ ማራኪ እና ፍሰት ያለው እንቅስቃሴ ባሳየበት ቀሪዎቹ የመጀመርያ አጋማሽ ሰላሳ ደቂቃዎች በርካታ ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል። ለአብነትም 15ኛው ደቂቃ ላይ በእለቱ ድንቅ ክህሎቱን ሲያሳይ የነበረው ታፈሰ ሰለሞን በግምት ከ25 ሜትር ርቀት አክርሮ የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ እንደ ምንም ወደ ውጭ ያወጣበት ፣ በ18ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ አለም ተስፋዬ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የመታትን ኳስ በድጋሚ ሮበርት በአስደናቂ ሁኔታ ያወጣበት እንዲሁም በ35ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በማጥቃቱ ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የተስተዋለው አዲስአለም ተስፋዬ ከመስመር ወደ ግብ የላካትን ኳስ ተጠቅሞ እስራኤል እሸቱ ወደ ግብ መትቶ የግቡን ቋሚ ታክካ የወጣችበት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ። በአንፃሩ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጓት ብቸኛ ተጠቃሽ ሙከራ 37ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ ወደ ግብ አክርሮ የመታት እና ቶጎዊው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳ እንደምንም ያወጣባት ነበረች።
42ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር አዲስአለም ተስፋዬ በረጅሙ የላከለትን ኳስ ፍሬው ሰለሞን በአግባቡ ተቆጣጥሮ ከግብ ክልሉ ጠርዝ አክርሮ የመታት ኳስ ሮበርት ግብ ላይ አርፋ ሀዋሳ ከተማን መሪ ማድረግ ችላለች። ከዚህች ግብ በኋላም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በሀዋሳ ከተማ 1-0 መሪነት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አሁንም ሀዋሳ ከተማዎች እጅግ የተሻለ እንቅስቃሴን ሲያደርጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ከመጀመርያው አጋማሽ ያልተሻለ እንቅስቃሴ እና ደካማ የጎል የማስቆጠር ጥረት አሳይተዋል። አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶም ጋዲሳ መብራቴ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ደስተኛ አለመሆናቸውን አስተውለናል።
በ56ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የላካት ኳስ ታፈሰ ሰለሞን ጋር ደርሳ አማካዩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን አልፎ ግብ ጠባቂው ሮበርት ኡዶንካራን ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ በመሸወድ አስደናቂ በሆነ አጨራረስ ሀዋሳን ወደ 2-0 መሪነት አሻግሯል።
በጨዋታው 64ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳን ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያከሽፍ የዋለው ሮበርት ኦዶንካራ በደረሰበት ጉዳት በዘሪሁን ታደለ ተቀይሮ የወጣ ሲሆን ዘሪሁንም የሀዋሳን ጥቃት መመከት ሳይችል ቀርቷል። 80ኛው ደቂቃ ላይ አንጋፋው አማካይ ሙሏለም ረጋሳ በሄኖክ ድልቢ ተቀይሮ ሲወጣ በስታዲየሙ የታደሙት ሁሉም ደጋፊዎች ቆመው በማጨብጨብ ያሳዩት አድናቆት ሌላው የእለቱ ተጠቃሽ ክስተት ነበር።
በ83ኛው ደቂቃ እስራኤል ፣ ታፈሰ እና ፍሬው በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ በመጠጋት የተሻገረውን ኳስ በጉዳት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ርቆ ቆይቶ በቅርቡ የተመለሰው እስራኤል እሸቱ በግምባሩ በመግጨት የሀዋሳን መሪነት ወደ ሶስት ማሳደግ ችሏል። በ85ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አዲስአለም ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ላይ በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ፍሬው ለታፈሰ ሲያመቻችለት በእለቱ ድንቅ የነበረው ታፈሰ ለራሱ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሮ መሪነቱን ወደ አራት ከፍ አድርጓል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ የመጨረሻው የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ በ90ኛ ደቂቃ ላይ አበባው ቡታቆ ከቅጣት ምት የመታውን ኳስ ሶሆሆ ሲመልሳት ሲዴ ኬይታ አግኝቶ የቅዱስ ጊዮርጊስን ብቸኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በውጤቱ መሰረት ባለፉት 7 ጨዋታዎች ያለ ድል የተጓዘው ሀዋሳ ከተማ ወደ አሸናፊነት ሲመልስ 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ1994 በኋላ ከፍተኛውን የጎል መጠን አስተናግዷል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ
ጨዋታው ጥሩ ነበር። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጉድለታችንን ለማረም መቻላችን እንደ ጥሩ ነገር ሊወሰድ ይችላል። በተለይ በማጥቃቱ ረገድ ያለፉት ጨዋታወች ላይ ከፍተኛ ክፍተት ነበረብን። ይህ ችግር ዛሬ ተፈቷል ብዬ ባላስብም በተወሰነ መልኩ ቀርፈናል ማለት እችላለሁ። ባለፉትን ተከታታይ ጨዋታዎች ፍሬውን በቅጣት አላገኘነውም ነበር። ዛሬ ማግኘታችን ይበልጥ አጠንክሮናል። ዛሬም በርካታ ተጫዋቾትን በጉዳት ሳንይዝ ብንገባም በጥሩ እንቅስቃሴ አሸንፈን ወጥተናል፡፡
ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
በቅድሚያ ሀዋሳ ከተማዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ዛሬ ሀዋሳወች ያሳዩት ብቃት ጥሩ ነበር። በሙሉ ደቂቃውም የተሻሉ ነበሩ ማለት ይቻላል። ነገር ግን በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ እንደልብ እንዲጫወቱ ሰፊ ክፍተት መስጠታችን የጎዳን ይመስለኛል። የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች የሚያደርጉትን ፈጣን እንቅስቃሴ ተጫዋቾቼ ለማስቆም ያደረጉት ጥረት ዝቅተኛ ነበር። ዛሬ በአጠቃላይ ጥሩ አልነበርንም ፤ በሁለተኛው ዙር ግን የተጎዱ ተጫዋቾች ሲመለሱ በእነሱ ታግዘን ተሻሽለን እንደምንቀርብ ብዬ ሙሉ እምነት አለኝ። በቡድኔም ሁሌም ደስተኛ ነኝ፡፡