ጅማ አባ ቡና
በከፍተኛ ሊግ በምድብ ለ የሚገኘው ጅማ አባ ቡና በዘንድሮ ዓመት አሰልጣኝ ግርማ ሀ/ዮሀንስ ቢቀጥርም በክለቡ ደጋፊዎች ተደጋገሚ ተቃውሞ ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየታቸው የሚታወስ ነው። ክለቡ በምትካቸው የቀድሞው የቡድኑ አሰልጣኝ የነበረው አንተነህ አበራን በጊዜያዊነት የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በማድረግ የሾመ ሲሆን አሰልጣኙ የቡድኑን መልበሻ ቤት የማረጋጋትና ቡድኑ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የመመለስ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
ሀምበሪቾ
በአስረኛው ሳምንት ሊካሄድ የነበረው የሀምበሪቾ እና ጅማ አባ ቡና ጨዋታ በጊዜው ሀምበሪቾ በሜዳው ጨዋታ እንዳያደርግ የተቀጣውን ቅጣት ይግባኝ በመጠየቁ በይደር ቆይቶ ሳይደረግ መቅረቱ ይታወሳል። ጨዋታው የካቲት 23 (ነገ) ሊካሄድ ታስቦ መርሀ ግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም ሜዳው ለሌላ መርሀ ግብር መያዙን ሀምበሪቾ በማሳወቁ ወደ የካቲት 26 (ሰኞ) መዞሩን የኢትዮጽያ እግር ኳስ ፌዴረሽን የከፍተኛ ሊግ ክፍል አስታወቋል።
ሀዲያ ሆሳዕና
በቅርቡ ኢዘዲን አብደላን አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው ሀዲያ ሆሳዕና መሐመድ ራዚክ የተባለ የጋና ዜግነት ያለው ተጫዋች ወደ ክለቡ ማምጣቱ ታውቋል። ክለቡ ተጫዋቹን በሁለተኛው ዙር መጠቀም ይችላል ተብሏል።
አማራ ውሃ ስራ እና የነቀምት ከተማ ጨዋታ
ተስተካካይ የጨዋታ መርሀ ግብር የፊታችን ዓርብ ሊደረግ ታስቦ የነበረው ጨዋታ የአማራ ውሃ ስራ እና የነቀምት ጭዋታ መርሀ ግብር ነቀምት ከተማ ቡድን ባጋጠመው የመንገድ ችግር ምክንያት ወደ ባህር ዳር ጉዞ ማድረግ ሳይችል በመቅረቱ ጨዋታው በሌላ መርሀ ግብር እንደሚከናወን ተገልጿል።
የዚህ ሳምንት ተስተካካይ መርሀ ግብሮች
(ሀሉም ጨዋታዎች 09:00 ይጀምራሉ)
23-06-2010
ሽረ እንዳስላሴ ከ የካ ክፍለ ከተማ
ደሴ ከተማ ከ ሱሉልታ ከተማ
24-06-2010
ወሎ ኮምቦልቻ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ
ቡራዩ ከተማ ከ ፌዴራል ፖሊስ
25/06/2010
ወልቂጤ ከተማ ከ ነገሌ ከተማ
ደቡብ ፖሊስ ከ ስልጤ ወራቤ
ናሽናል ሴሜንት ከ ሻሸመኔ ከተማ
26/06/2010
ሀምበሪቾ ከ ጅማ አባ ቡና
ተዋወቁት
ስም: ዳንኤል ገበየው
ትውልድ ቦታ: ቢሾፍቱ
ቁመት: 1.71 ሜትር
ክብደት: 67 ኪ/ግ
የሚጫወትበት ቦታ – አማካይ
ክለብ – ኢትዮጵያ መድን
የቀድሞ ክለብ – ቢሾፍቱ ከተማ
” የእግር ኳስ ህይወቴ የጀመረው በትውልድ ከተማዬ ቢሾፍቱ ህትመት ኮምፓሽን በሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው። ከዛም በስፈራችን ባለው ቡድን ስጫወት ቆይቼ የኦሮሚያ ሻምፒዮና ጨዋታዎች ላይ ታድሞ የነበረው የቢሾፍቱ ከተማ አሰልጣኝ ወደ ቡድኑ በቢጫ ቲሴራ አስገብቶኛል። በቢሾፍቱ ከተማ በክለብ ደረጃ ታቅፌ የጨዋታ ህይወቴን የጀመሩኩ ሲሆን በክረምቱ እረፍት ላይ ሆኜ የቀድሞ የበጎ አድራጎት ቡድኔን ተቀላቅዬ በምጫወትበት ወቅት ከኢትዮጽያ መድን ጋር ስንጋጠም አሰልጣኝ ደረጄ ተመልክቶኝ መድንን እንድቀላቀል ጥያቄ ሲያቀርብልኝ ማመን አልቻልኩም ነበር። ሆኖም እውን ሆኖ አገኘሁት። ”
የተጫዋቾች ቅጣት
ቅጣት አንድ
የናሽናል ሴሜንት ከ ዲላ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በ29ኛው ደቂቃ ላይ በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት ላይ በተሰጠው የቀይ ካርድ ሰለባ የሆኑት ከናሽናል ሴሜንት መሀመድ አህመድ እና ከዲላ ከተማ ወንድወሰን ኃይሌ የኢትዮጽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ በዕለቱ በዳኝነት ላይ የነበሩትን ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊድያ ታፈሰ የነበረውን የዕለቱን ክስተት በሪፖርት ከማቅረብ በተጨማሪ በአካል በመቅረብ ያስረዱ ሲሆን በዚሁ መሰረት ሁለቱም ተጫዋቹች የ4 ጨዋታ እና የአራት ሺ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
ቅጣት ሁለት
ጥር 27 ቡታጅራ ከተማ ከ ናሽናል ሴሜንት ባደረጉት ጨዋታ የዕለቱ ዳኛ ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተው በፍጥነት ሰጥተው በመሮጥ ላይ ሳሉ የናሽናል ሴሜንቱ ፈይሰል አሚን የዳኛውን ውሳኔ በመቃወም ዳኛው ላይ ጉዳት አድርሶ ዳኛው ሜዳ ላይ ራሳቸውን ስተው በመወደቃቸው በአቅራቢያው ወደ ሚገኝ ሆስፒታል በመጎዝ ህክምና አግኝተዋል። የዕለቱም ዳኛ በአካል በመቅረብ እንዲሁም ኮሚሽነር ባቀረቡት መሰረት ተጫዋቹ ለአንድ አመት እገዳ እና የአስር ሺህ ብር ቅጣትተላልፎበታል።
ቅጣት 3
የወሎ ኮምበልቻው ሳላህዲን ሙሰማ ከ አማራ ውሀ ስራ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ በ 80 ኛው ደቂቃ ላይ የአማራ ውሀ ስራ ተጫዋችን በክርኑ በመማታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዶል በዚህም ምክንያት ተጨዋቹ ሳላህዲን ሙሰማ የአራት ጨዋታ እና የአራት ሺ ብር ቅጣት ተላልፎበታል።
የቡድን ቅጣት
ወሎ ኮምበልቻ ከ አዲስ አበባ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በተከሰተው የደጋፊ ረብሻ ቅጣት የተላለፈበት ወሎ ኮምበልቻ ከሜዳ ውጭ ሁለት ጨዋታ እና የብር ቅጣት የተለፈበት ቢሆንም ባስገባው ይግባኝ ቅጣቱ ወደ አንድ ጨዋታ ዝቅ ማለቱ ታውቋል። የፊታችን ቅዳሜ ኮምቦልቻ ላይ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የወሎ ኮምቦልቻ እና የለገጣፎ ለገዳዲ ጨዋታ ወደ ወልድያ መሐመድ ሁሴን አል-አሙዲ ስታደዮም ሊካሄድ መታሰቡን ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች።
የወሎ ኮምቦልቻን የቅጣት ዜና ዘግይተው የሰሙት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ጨዋታው ወደ እሁድ እንዲራዘም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ አካል ማቅረብ ያቀረቡ ቢሆንም ጥያቄቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶል። ከዚህ ቅጣት ጋር ተያይዞ የወሎ ኮምበልቻ ቡድን መሪ ለሶከር ኢትዮጽያ በቅጣቱ ዙሪያ ያላቸውን አስታያየት ገልፀዋል። ” አወዳዳሪው ኣካል ቅጣቶችን ሲጥል ቡድኑ ከዚህ ቀደም የነበረውን የቅጣት መዝገብ ከግምት ውስጥ ቢያስገባ እና ቡድኖች የሚያስገቡትን ቅሬታ በሚገባ አጢኖ ቢሆን ጥሩ ነው”