በቶታል ካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የኢትዮጵያው ወላይታ ድቻ በመጪው ረቡዕ ሀዋሳ ላይ የግብፁን ዛማሌክን ያስተናግዳል፡፡ በቅድመ ማጣሪያው የዛንዚባሩን ዚማሞቶን በአጠቃላይ ውጤት 2-1 የረታው ድቻ ተጋጣሚ የሆነው ዛማሌክ ዛሬ ምሽት 20 ተጫዋቾችን ይዞ አዲስ አበባ እንደሚደርስ አስታውቋል፡፡
በግብፅ ፕሪምየር ሊግ አጀማመሩ መልካም ያልነበረው ዛማሌክ ከበርካታ አሰልጣኞች ለውጥ በኃላ በቅርብ ሳምንታት ወደ ድል መመለስ ችሏል፡፡ የአምስት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ ዛማሌክ አምና ከተሳተፈበት ቻምፒየንስ ሊግ ወርዶ በሁለተኛው የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ላይ መሳተፉን ለሚጀምርበት ጨዋታ ቅዳሜ ለሊት ወደ ኢትዮጵያ መዲና የሚደርስ ይሆናል፡፡ በአዲስ አበባ የአንድ ቀን ቆይታ ካደረገ በኃላ ሰኞ ጨዋታው ወደ ሚካሄድበት ሀዋሳ የሚያመራ ሲሆን ቀለል ያለ የልምምድ ፕሮግራም በስፍራው ለማካሄድ እንዳቀደ ተነግሯል፡፡
ዛማሌክ ከ2005 በኃላ ከኢትዮጵያ ክለብ ጋር ሲገናኝ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ክለቡ በ2005 ከቅድስ ጊዮርጊስ ጋር 2-2 ተለያይቶ ወደ ቻምፒየንስ ሊጉ ምድብ ያመራ ሲሆን በ1968 ከምድር ጦር፣ በ1991 ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አዲስ አበባ ላይ ተጫውቶ በሁለቱም ጨዋታዎች ተሸንፏል፡፡ ዛማሌክ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶም የኢትዮጵያ ክለቦችን አሸንፎ አያውቅም፡፡
ዛማሌክ በያዝነው ሳምንት በሊግ ጨዋታ ታላል ኤል ጋይሽን 3-0 የረታ ሲሆን በደረጃ ሰንጠረዡ ከመሪው አል አሃሊ በ21 ነጥቦች ርቆ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ክለቡ ኤሃብ ጋላልን አሰልጣኝ አድርጎ በውድድር አመቱ አጋማሽ ቀጥሯል፡፡ አሰልጣኙ በ2008 ምስር ኤል ማቃሳን ይዘው በተመሳሳይ ውድድር መከላከያን በድምር ውጤት 6-1 አሸንፈዋል፡፡ ምስር ኤል ማቃሳ በግብፅ ክለቦች ታሪክ የኢትዮጵያን ክለብ ከሜዳው ውጪ ያሸነፈ ብቸኛው ቡድን ነው፡፡
የወላይታ ድቻ እና ዛማሌክን ጨዋታ ማላዊያን ዳኞች የሚመሩት ይሆናል፡፡ በመሃል አርቢትርነት እስማኤል ቺዚንጋ በካፍ የተሾሙ ሄንድሪክ ማሴኮ እና ኤድዋርድ ካምባቱዋ ረዳቶች ናቸው፡፡ ጨዋታው የግብፅ የስፖርት ቴሌቭዥን ጣቢያ ዲኤምሲ ስፖርት በቀጥታ ለማስተላለፍ ከስምምነት መድረሱ ዛሬ ከግብፅ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡