በ2018ቱ የቶታል አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታዎች በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ ሲደረጉ የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዩጋንዳው ሻምፒዮን ኬሲሲኤ ጋር ይጫወታል። ሁለቱ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ በምድብ ውድድሩ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ቢያንስ በአንድ ክለብ እንደሚወከል ያረጋገጠ እንደመሆኑ የክልሉ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረትን አግኝቷል።
ለሁለቱም ቡድኖች ተጫውቶ ያሳለፈው ዩጋንዳዊው አጥቂ ብራያን ኡሞኒም ለሞኒተር ጋዜጣ በጨዋታው ላይ አስተያየቱን ሰጥቷል። ከሁለቱ ቡድኖች በተጨማሪ ለደቡብ አፍሪካዎቹ ሱፐርስፖርት ዩናይትድና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶሪያ፣ ለአሜሪካው ፖርትላንድ ቲምበርስ፣ ለታንዛኒያው አዛም እና ለቬትናሙ ቤካሜክስ ዱዎግ ተጫውቶ ያሳለፈው ኡሞኒ የመጀመሪያው ጨዋታ ለዩጋንዳውያኑ ፈታኝ እንደሚሆን ያምናል።
“ኬሲሲኤ ከሜዳው ውጪ በሚያደርገው ጨዋታ ለማሸነፍ ይከብደዋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሜዳቸው በሙሉ ሃይላቸው በማጥቃት ስለሚጫወቱ ኬሲሲኤ በጥንቃቄ መጫወት፣ ክፍተቶችን በቶሎ መዝጋት እና እንደ ቡድን በህብረት መጫወት ግድ ይለዋል።”
ኡሞኒ በ2008ቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ላይ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ባጋጠመው የመሰበር ጉዳት ምክኒያት እስካሁን ወደሜዳ መመለስ ያልቻለ ሲሆን በቀጣዩ የዝውውር መስኮት ክለብ ለማግኘት እንዲረዳውም ከካምፓላው ክለብ ጋር አብሮ ልምምዱን እየሰራ ይገኛል። ተጫዋቹ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከተለየ 2 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ኬሲሲኤን መፈተን የሚችል ስብስብ በክለቡ ለመኖሩ እርግጠኛ እንደሆነ ይናገራል።
“ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳስን መያዝ እና በአጭር ቅብብል መጫወት ይወዳሉ፤ በዚህ አጨዋወትም ጥሩ ናቸው። በተጨማሪም ፈጣን የመስመር ተጫዋቾች እና ልምድ ያላቸው ጥሩ አጥቂዎችን ይዘዋል። በአሁኑ ሰዓት በቡድኑ ውስጥ ማን ቋሚ ተሰላፊ እንደሆነ ባለውቅም ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራን ጨምሮ ጠንካራ እና በኮከቦች የተሞላ ስብስብ እንዳላቸው አውቃለሁ። በዚህ የውድድር ዓመትም ጥሩ የሚባሉ ዝውውሮችን አድርገዋል።”
በተያያዘ ዜና የኬሲሲኤ የመሃል ሜዳ ወሳኝ ተጫዋች የሆነው ኢብራሂም ሳዳም ጁማ ባጋጠመው የተረከዝ ጉዳት ምክኒያት ቢያንስ ለ2 ወራት ከሜዳ እንደሚርቅ ታውቋል። ጁማ ክለቡ በዩጋንዳ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ከሲምባ ጋር ባደረገው ጨዋታ ጉዳቱን ያስተናገደ ሲሆን ከእርሱ በተጨማሪ አማካዮቹ ጁሊየስ ፖሎቶ እና ሙዛሚሩ ሙትያባ በጉዳት ላይ መገኘታቸው የቡድኑ አማካይ ክፍል ላይ መሳሳት ይፈጥራል በሚል ቢያሰጋም የሁለቱ ተጫዋቾች ወደ ልምምድ መመለስ ለክለቡ እፎይታን ፈጥሯል።።
የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹን የሚመሩ ዳኞችን ስም ይፋ ሲያደርግ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የሚደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ በሩዋንዳውያን አርቢትሮች ይመራል። ከ10 ቀናት በኋላ በካምፓላው ስታር ታይምስ ስታዲየም የሚደረገውን የመልስ ጨዋታ የመምራት ኃላፊነቱ ደግሞ ለኬንያውያን ዳኞች ተሰጥቷል።
የመጀመሪያውን ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች: ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኬሲሲኤ (አዲስ አበባ ስታዲየም):
- የመሃል ዳኛ: ጃን ክላውድ ኢሺምዌ (ሩዋንዳ)
- ረዳት ዳኛ 1: ሬይመንድ ኖናቲ ብዊሊዛ (ሩዋንዳ)
- ረዳት ዳኛ 2: ዜፋኒ ኒዮንኩሩ (ሩዋንዳ)
- 4ኛ ዳኛ: ሩዚንዳና ንሶሮ (ሩዋንዳ)
- የጨዋታ ኮሚሽነር: ሁሴን ስዋሌህ ምቴቱ (ኬንያ)
የመልሱን ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች: ኬሲሲኤ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ስታር ታይምስ ስታዲየም – ሉጎጎ):
- የመሃል ዳኛ: አንድሪው ጁማ ኦቲዬኖ (ኬንያ)
- ረዳት ዳኛ 1: ጊልበርት ቼሪዮት ኬንያ)
- ረዳት ዳኛ 2: ስቴፈን ይኤምቤ (ኬንያ)
- 4ኛ ዳኛ: ፒተር ዋዌሩ (ኬንያ)
- የጨዋታ ኮሚሽነር: ማሃማዱ ኑሩ ዲን ጃውላ (ጋና)
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዩጋንዳው ኬሲሲኤ ጋር የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 10፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።