በጥር ወር መጨረሻ መደረግ የነበረበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታ ዛሬ በተስተካካይ መርሀ ግብር ወልድያ ሼህ መሀመድ ሁሴን አል-አሙዲ ስታድየም ላይ ተካሂዶ የሊጉ መሪ ደደቢትን ያስተናገደው ወልድያ 1-0 በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።
ወልዲያ ባሳለፍነው ሀሙስ መከላከያን አስተናግዶ 2-0 ከረታበት ስብስቡ ውስጥ ነጋ በላይን በብርሃኔ አንለይ በመተካት ለዛሬው ጨዋታ በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገባ በአንፃሩ ደደቢት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ምንም ጎል ከተለያየበት ጨዋታ አማራህ ክሌመንት ፣ ከድር ኩሊባሊ ፣ አስራት መገርሳን በቅጣት እና በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ መሆናቸውን ተከትሎ በግብ ጠባቂነት ታሪክ ጌትነት እንዲሁም ተከላካዩ አንዶህ ኩዌኩ እና አማካዩ ፋሲካ አስፋው ተክተው በመግባት በተመሳሳይ የ4-3-3 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል።
በርከት ያለ ቁጥር ያለው ተመልካች የታደመበትን ይህን ጨዋታ ፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ በዋና ዳኝነት መርተውታል። ደደቢቶች የመጀመርያውን ጎል እስካስተናገዱበት 22ኛው ደቂቃ ድረስ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ኤፍሬም አሻሞ እና አቤል ያለው ያገኙትን የግብ አጋጣሚ ለመጠቀም ያደረጉት ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል። በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ ወልዲያዎች ጉልበት ላይ ያመዘነ ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት መመምረጣቸው የጨዋታውን እንቅስቃሴ ወደ ሌላ መልክ ቀይሮታል። በተለይ ብሩክ ቃልቦሬ በተደጋጋሚ የሚሰራውን አላስፈላጊ ጥፈት ፌዴራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ በቢጫ ማስጠንቀቂያ ብቻ ሲያልፉት አስተውለናል። በአንድ አጋጣሚ የዕለቱ ዳኛ እና ብሩክ ቃልቦሬ በፈጠሩት ውዝግብ ዳኛው ብሩክን በክንዳቸው አንገቱን ሲገፉት እሱም አፀፋዊ ምላሽ ሲሰጥ ለማየት ችለናል።
ጨዋታው በጥሩ እንቅስቃሴ ቢቀጥልም በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚፈጠሩ ውዝግቦች የተነሳ እየተቆራረጠ እና የማስጠንቀቂያ ካርድ ሳይለየው ቀጥሎ በ22ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን አካለ ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ለምንያህል ተሾመ አሻግሮለት ምንያህል በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ጎል ወልዲያዎች መሪ መሆን ችለዋል። ጎሉ ሲቆጠር በስታድየሙ ውስጥ የነበሩት የወልዲያ ደጋፊዎች ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ ልዩ ነበር።
በወልዲያዎች በኩል ከጎሉ መቆጠር በኋላ በአንድ አጋጣሚ አማረ በቀለ ከ28 ሜትር ርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት እንደምንም ያዳነበት የሚጠቀስ ቢሆንም ብዙም የሚገለፅ ሌላ የጎል ሙከራ ሳይታይ ጉሽሚያ በዝቶበት ሲቀጥል የዕለቱ ዳኛ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረትም አነስተኛ ነበር። በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ወልድያዎች ያገኙትን የማእዘን ምት ሲያሻሙ ኳሱን ያገኘው ደስታ ደሙ ከራሱ የግብ ክልል ኳሱን እየገፋ ወደፊት በመሄድ ፍጥነቱ እየተጠቀመ ተጨዋቾችን በአስገራሚ ሁኔታ እያለፈ ሳጥን ውስጥ በመግባት ብቻውን ነፃ ሆኖ ለቆመው አቤል ያለው አቀብሎት አቤል አገባው ተብሎ ሲጠበቅ በትኩረት ማጣት ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ ደደቢቶችን የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።
ደደቢቶች ከእረፍት መልስ አቤል እንዳለ እና ፋሲካ አስፋውን በአለምአንተ ካሳ እና በሰለሞን ሀብቴ በመቀየር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ጠንካራ ተብሎ የሚጠቀስ የጎል ሙከራ ማድረግ የቻሉት በሁለት አጋጣሚ ብቻ ነበር። በ73ኛው ደቂቃ ስዩም ተስፋዬ በጥሩ ሁኔታ የሰጠው እና አቤል ያለው ያመከነው ፤ 76ኛው ደቂቃ ላይ ከመአዘን የተሻገረውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ በግንባሩ ገጭቶ በግቡ አናት ላይ ለጥቂት የወጣበት አጋጣሚ ተጠቃሾች ነበሩ። ደደቢቶች የኳስ ቁጥጥር የበላይነታቸው ጥሩ ሆኖ በቆየበት ሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን የሚቆጣጠር እንደ አስራት መገርሳ አይነት ተጨዋች አለመኖሩ በቡድኑ ውስጥ እንደ ክፍተት የሚታይ ቢሆንም የወልዲያ ተከላካዮች ክፍተት ላለመስጠት ያደረጉት የመከለከል ብቃት ውጤታማ አድርጓቸዋል። ከዚህ ወጭ ወልዲያዎች ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት እና ጎል እንዳይቆጠርባቸው ወደ ኋላ በማፈግፈግ ሲከላከሉ የታዩ ሲሆን በ63ኛው ደቂቃ ምንያህል ተሾመ ለቡድኑም ለራሱም ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጨዋታው በተደጋጋሚ ኳስ አቀባዮች በኩል በትክክል ኳስን ከማቀበል ይልቅ ጨዋታውን ለማዘግየት የሚወስዱት አላስፈላጊ ድርጊት የዕለቱ ዳኛ የወልዲያውን የቡድን መሪ በመጥራት እንዲስተካከል ለማድረግ ቢሞክርም ባለመስተካከሉ የደደቢት የቡድን አባለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት ምንያህል ተሾመ ከእረፍት በፊት ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል በወልዲያ 1 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ወልድያ ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሎ 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በአንፃሩ ደደቢት በውድድር አመቱ ሁለተኛ ሽንፈት በማስተናገድ 29 ነጥብ በመያዝ የሊጉ መሪ በመሆን አንደኛውን ዙር አጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ – ወልድያ
ጨዋታውን በመጀመርያው አጋማሽ አጠናቆ ለመውጣት በጣም ተነጋግረን ነበር። ምክንያቱም ደደቢት ኳሱን በመቆጣጠር ከእኛ የተሻለ እንደሚሆን አስበናል። ባለን አቅም ተጭነን መጫወት ወስነን ነው የገባነው። ያው እንዳያችሁት ጎል አስቆጥረን ወጥተናል። ከእረፍት መልስ ልጆቼ ውጤቱን ማስጠበቅ እንዳለባቸው አስበን ገባን ፤ ያም ተሳክቶልን አሸንፈን ወጥተናል ።
ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ – ደደቢት
ጨዋታው ጥሩ ነበር። በእንቅስቃሴ የተሻልን ነበርን። 90 ደቂቃ መብለጥ ችለናል። የሚሆነው ሆኗል ውጤቱ አይገባንም ማሸነፍ ነበረብን ። ከዚህ ውጭ ምንም ማለት አልፈልግም። በዳኝነት ዙርያ ሜዳ ውስጥ ጨዋታ የነበረውን ነገር መናገር አልፈልግም።