​ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ | ወላይታ ድቻ ከነገው ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ ሰርቷል

በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ረቡዕ በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ከዛማሌክ ለሚያደርገው የአንደኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። ዛሬ ረፋድ ላይም የመጨረሻ ልምምድ አከናውኗል።

ወላይታ ድቻዎች ማክሰኞ በፕሪምየር ሊጉ ጅማ አባጅፋርን ከሜዳቸው ውጪ ገጥመው 2-1 ተሸንፈው ከተመለሱ በኋላ አርብ ወደ ሀዋሳ በማምራት በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ላለባቸው የዛማሌክ ጨዋታ ዝግጅታቸውን ማድረግ መጀመራቸው ይታወሳል። ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊትም ዛሬ ጠዋት ከ1:00 ጀምሮ ልምምዳቸውን አከናውነዋል። አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በኳስ ቁጥጥር የበላይ ለመሆን ያለመ ልምምድ ሲያሰሩ የተስተዋለ ሲሆን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴን የመተግበር ልምምድም የመርሀ ግብሩ አካል ነበር። የቡድኑ አባላት ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁትም ለጨዋታው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተዘጋጁ ይገኛሉ።

የጦና ንቦች ዚማሞቶን በገጠሙበት ጨዋታ የያዟቸው 18 ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምድ እየሰሩ የነበረ ሲሆን በጉዳት ዳግም በቀለ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑና አምረላህ ደልታታ ተክቶት እንደሚገባ ተነግሯል፡፡ ጅማ ከገጠሙበት ጨዋታ በፊት በምግብ መመረዝ ምክንያት ህመም እንደነበረባቸው ሲነገር የነበሩት ወሳኙ አጥቂ ጃኮ አራፋት እና ኃይማኖት ወርቁ በሙሉ ጤንነት ላይ መገኘታቸው ሲረጋገጥ በዛበህ መለዮም  ከጉዳት አገግሞ ለጨዋታው ብቁ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ጨዋታውን የሚመሩት አራቱም ዳኞች ከማሊ ሲመደቡ ኮሚሽነሩ ደግሞ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ናቸው። ዳኞቹ  ትላንት ምሽት ሀዋሳ በመግባት በሌዊ ፒያሳ ሆቴል ማረፊያቸውን አድርገዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *