በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ያለፉት 8 አመታት ከተመለከትናቸው የውጭ ሀገር ዜግነት ካላቸው ተጫዋቾች መካከል በወጥነት ሲጫወት የቆየው አዳሙ መሐመድ የእግርኳስ ህይወት በጉዳት ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።
በዘንድሮ አመት በወልዲያ ለመቆየት ኮንትራቱን ማደስ የቻለው አዳሙ መሐመድ ባጋጠመው ከፍተኛ የጉልበት ጉዳት ምክንያት መጫወት የቻለው ታህሳስ ወር በዘጠነኛ ሳምንት ወልድያ በሜዳው አርባምንጭ ከተማን 2 – 0 በረታበት ጨዋታ ብቻ ላይ ነበር። በዚህም ጨዋታ ላይ በጉዳት ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል። ተጫዋቹ ካጋጠመው ጉዳት ለማገገም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ህክምና ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ከህመሙ መዳን አልቻለም። ከክለቡ እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ የጉልበቱ ጅማት እንደተበጠሰ እና ኢትዮዽያውያን ሀኪሞች ከዚህ በኋላ እግርኳስ መጫወት እንደሌለበት ነግረውታል። ታዲያ አዳሙ ሀገሩ ጋና በማቅናት የተሻለ ህክምና ለማድረግ በማሰብ ባሳለፍነው ሳምንት ለህክምናው ወጪው ይረዳው ዘንድ ተጨዋቾቹ በማዋጣት እስከ 70 ሺህ ብር እንዲሁም ክለቡ ወልድያ የተወሰነ ድጋፍ አድርገውለት ወደ ሀገሩ መሄድ ችሏል ።
አዳሙ መሀመድ እንደታሰበው ጤንነቱ የሚመለስ ከሆነ ወደ ወልዲያ ዳግም ተመልሶ ይጫወታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ያ የማይሆን ከሆነ ወልዲያ እና አዳሙ ተለያይተው ክለቡ ሌላ ተከላካይ ተጫዋች በምትኩ ለማስፈረም ይገደዳል።
በ2003 ለደደቢት በመፈረም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ጋናዊው ተከላካይ በሰማያዊዎቹ ማልያ ለአምስት አመታት የቆየ ሲሆን በሊጉን እና ጥሎ ማለፍ ድል ከቡድኑ ማጣጣም ችሏል። በ2008 ከደደቢት ጋር ከተለያየ በኋላ ከቀድሞ አሰልጣኙ ንጉሴ ደስታ ጋር አብሮ ለመስራት ወደ ወልዲያ ያቀናው አዳሙ ክለቡ በከፍተኛ ሊግ ከምድቡ ሁለተኛ በመሆን ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም እንዲመለስ እና በ2009 የውድድር አመት ለተጋጣሚ እጅግ አስቸጋሪ እና ጎሎች በቀላሉ የማይቆጠሩበት እንዲሆን ከፍተኛውን ሚና የተጫወተ ተጫዋች ነው።