በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ወደ ምድብ ድልድል ለማምራት ቅዱስ ጊዮርጊስ የዩጋንዳው ኬሲሲኤን አዲስ አበባ ላይ ረቡዕ ያስተናግዳል፡፡ ፈረሰኞቹ ዓምና ወደ ምድብ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የገቡሲሆን ይህንን ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ለመድገም ከፊታቸው የካምፓላውን ክለብ ፈተና ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ከ10 ሰዓት ጀምሮ ቦሌ አከባቢ በሚገኘው የልምምድ ሜዳው ለጨዋታው የሚረዳውን የመጨረሻ ዝግጅት አድርጓል፡፡ የረጅም ግዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው አማካዩ ናትናኤል ዘለቀ ውጪ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የክለቡ ተጫዋቾች በልምምዱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ከተሸነፈ በኃላ የቡድኑ መንፈስ ለውጥ እያሳየ መሆኑን ምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ “ጥሩ ነገር ሰርተናል፡፡ ልጆቻችንም ለጨዋታው ያላቸው መነሳሳት ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ባስመዘገብነው ውጤት ሁሉም ቢከፋም ሁለም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ነበር ልምምዳቸውን የሰሩት፡፡ የሀዋሳው ሽንፈት በክለባችን ታሪክም ሆነ በእያንዳንዳችን ላይ ተፅዕኖ አምጥቶ ነበር፡፡ በዛ ጨዋታ ላይ የሰራናቸው ስህተቶች ተማምነን እና ለኬሲሲኤው ጨዋታ ጥሩ መሻሻሎችን ለማየት ጠንካራ ስራዎች ሰርተናል፡፡ ደጋፊዎቻችን ባገኘናቸው ውጤቶች ተከፍተዋል ፤ እኛም ይህንን በሚገባ ስለምናውቅ ደጋፊዎቻችን ለማስደስት በ90 ደቂቃው ጨዋታ የሚገባንን ውጤት ለማግኘት በጥሩ መነሳሳት ላይ እንገኛለን::” ብለዋል።
ምክትል አሰልጣኙ ጨምረው የክለቡ የመጀመሪያ ተመራጭ ግብ ጠባቂ የሆነው ሮበርት ኦዶንካራ ከሀዋሳው ጨዋታ በኃላ መጠነኛ ጉዳት ያለበት ከመሆኑ ውጪ ሌሎች ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ በዚህ ላይ አያይዘውም ስለዩጋንዳ ቻምፒዮኑ መረጃዎችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ “ኬሲሲኤ አንዳንድ ጨዋታዎችን እና ለመጨረሻ ግዜ የተጫወተውን የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ምስሎችን ለማየት ሞክረናል፡፡ እነሱ የሚጫወቱበትን መንገድ አይተን እኛ እንዴት መጫወት አለብን የሚለው ላይ ሰርተን ጥሩ ነገሮችን በቡድናችን ላይ ተመልክተናል፡፡” ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።
ሰኞ ማለዳ ወደ አዲስ አበባ የደረሰው የዩጋንዳው ኬሲሲኤ በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ብቸኛው የሃገሪቱ ክለብ ነው፡፡ ዓምና በማሜሎዲ ሰንዳውንስ ተሸንፎ ወደ ምድብ ማለፍ ያልቻለው ክለቡ በዘንድሮው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ የማዳጋስካሩን ስናፕስ ስፖርትስን ከሜዳው ውጪ ባስቆጠረው ግብ አሸንፎ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተገናኝቷል፡፡ ክለቡ በአዲስ አበባ ቆይታው ሁለት ልምምዶችን የሰራ ሲሆን ስናፕስን ካሸነፈው ቡድን ውስጥ የተካተቱ ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡
የኬሲሲኤ ምክትል አሰልጣኝ የሆኑት ሞርሊ ብያክዋሳ ተጫዋቾቻቸው ከሜዳቸው ውጪ የሚያስፈልጋቸው ውጤት እንደሚያመጡ ተማምነዋል፡፡ “ልምምዳችን ጥሩ ነበር፡፡ ሙሉ ትኩረታችን በነገው ጨዋታ ላይ ብቻ ነው፡፡ ልጆቻችን አሁን ላይ በራስ መተማመናቸው መልካም የሚባል ነው። አሁን ላይ ከሜዳችን ውጪ እንደምናሸንፍ እተማመናለው፡፡ ሁሉም ተጫዋቾች በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ቡድኖች ጋር የመጋጠም እድል አግኝቻለው እና በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በጣም ጠንካሮች እንደሆኑ በሚገባ እንረዳለን፡፡” ብለዋል።
ሁለት የሴካፋ ዞን ክለቦችን የሚያገናኘው ጨዋታ ነገ በ10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል፡፡