” ከዚህም በላይ ይገባን ነበር” አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ

በቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አንደኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ የግብፁ ዛማሌክን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል። ክለቡን ከተረከቡ በኋላ ሰረኬታማ ጉዞ እያደረጉ የሚገኙት አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ስለ ጨዋታው

” በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር። እንደጠበቅኩት ባይሆንም ከምላ ጎደል ጥሩ ነው። የመጀመሪያ አርባ አምሰት ጥሩ ተቆጣጥረን ተጫውተናል። በተደጋጋሚ ስህተት እንሰራለን ፤ ያንን ስህተት አርመን እና ቀርፈን ለመምጣት እንጥራለን፡፡ ”

ስለተጋጣሚያቸው

” ተጋጣሚያችን ጥሩ እንቅስቃሴ ነው የሚያደርጉት። እኛ እነሱ የሚያጠቁበትን እና የሚጫወቱበትን መስመር ሙሉ ለሙሉ ዘግተን ነው የተጫወትነው። ስለዘጋን የመጫወቻ መንገድ ከማጣታቸው በተጨማሪ እኛም ጥሩ ነበርን። ዛማሌኮች ጥሩ ቢሆኑም እኛ ደግሞ ኳሱን ተቆጣጥረን በመጫወት የተሻልን ነበርን፡፡ ”

ለእንዲህ አይነት ጨዋታዎች ስለሚሰጡ ከባድ ግምቶች

” በጣም በዚህ ላይ ሰርተናል። እኔ በጨዋታ ዘመኔ ለኢትዮጵያ ስጫወት የግብፅን ቡድን አውቀዋለው ። የግብፅን ልምድ ነግሬያቸዋለው ለተጫዋቾቼ ሜዳ ላይም አሳይቻቸዋለሁ ፤ በተለይ የነሱ የቅርብ ጊዜ ጨዋታ ( ኤል ጋኤሽን 3-0 ያሸነፉበትን ) አይተን በዛ መሰረት ነው የሰራነው። ጥቃት የሚያደርሱት በመስመር ነው ፤ የመስመር ጨዋታቸውን ሙሉ ለሙሉ ብሎክ አድገናል። ከዛም የተነሳ እነሱ የሚሄዱበት አጥተዋል። እኛ ደግሞ በጠንካራ ጎናችን ኳሱን ይዘን የመጫወት እንቅስቃሴን በማድረጋችን ዛሬ የተሻለ ውጤትን ይዘን ወጥተናል። ሆኖም ለመልሱ ጨዋታ ብዙ ነገር ይቀረናል። ”

ቡድናቸው ከዚማሞቶው ጨዋታ ስለመሻመሉ

” ምንጊዜም የባለፈውን ጨዋታ ነው መነሻ የምናደርገው። በዚማሞቶው የመጀመሪያ ጨዋታ ጥሩ ነበርን። እዚህ ሀዋሳ የመልሱ ጨዋታ ላይ ግን ጥሩ አልነበርንም። ያንን ቀርፈን ተጫዋቾቹ በራስ መተማመናቸው እንዲያድግ ብዙ ስራ ሰርቻለሁ። ከውጭ ዛማሌክን በጣም አገዝፈው እና አክብደው ነበር ያዩት። ነገር ግን እግርኳስ ጨዋታ በጣም ቀላል እንደሆነ እና ኳሱን ይዘን ከተጫወትን ማሸነፍ እና በኛ ኳስ መጠቃት እንደሌለብን ነግሬያቸው ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወታቸው ዛሬ ለድል በቅተናል። ከዚህም በላይ ይገባንም ነበር፡፡ ”

ስለ ደጋፊዎቹ

” እኔ መናገር ከምችለው በላይ ነው። ውጤቱ የወላይታ ድቻ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ይሄ ትልቅ ታሪክ ነው። ከተለያየ ቦታ ወላይታ ድቻን ብለው የመጡ ደጋፊዎት ውጤት ነው። ይሄ የወላይታ ድቻ ብቻ አይደለም። ደጋፊውን በጣም ነው የማመስግነው፡፡ ”

ስለመልሱ ጨዋታ

” ማሸነፍ መዘናጋትን ያመጣል። በቀጣይ እኛ ግን መዘናጋት እንደሌለብን እና ገና 90 ደቂቃ እንዳለ እናውቃለን። ከዛሬው ጨዋታ ነው የምንነሳው ፤ ከዛሬ ስህተታችን ታርመን በቀጣይ ለመልሱ እንዘጋጃለን ፡፡ ”

የዛማሌኩ አሰልጣኝ ኢሀብ ጋላል ለጋዜጣዊ መግለጫ ፍቃደኛ ባይሆኑም ምሽት ላይ በሆቴላቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ስለጨዋታው የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።

” ጨዋታው በጣም አስከፊ የሚባል ነው። እኔ በጣም የጠበኩት እና የምናሸንፍበት ጨዋታ ነበር። እኛ ግን ባሰብነው ልክ ለመጫወት አስበን በነበረው ዝናብ ይሁን የሜዳው ያለመመቸት እንዳሰብነው ልንጫወት አልቻልንም። ወላይታ ድቻን አስቀድመን ብዙም አናውቃቸውም ነበር። ዛሬ ግን በሚገባ ተመልክተናቸዋል። በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን እንደምንቀይረው ሙሉ እምነት አለኝ። ይህ እግር ኳስ በመሆኑ በቀጣይ የሚፈጠረውን እናያለን። ደጋፊዎቹ ግን ደስ ይሉ ነበር። ለኔ ደጋፊው ከጨዋታው ይልቅ ደስ የሚል ነበር። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *