የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎች መደረጋቸውን ቀጥለው ዛሬ በኦሜድላ ሜዳ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች አክሱም ከተማ እና የአማራ ውሃ ስራ ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ በመቀጠል የተደረገው የወሎ ኮምቦልቻ እና የሽረ እንደስላሴ ጨዋታ በሽረ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል። ደሴ ላይ ደግሞ ደሴ ከ መድን ነጥብ ተጋርተዋል።
የአክሱም ከተማ እና የአውስኮድ የመጀመሪያ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እጅግ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ይልቁንም አላስፈላጊ አካላዊ ጉሽሚያዎች የበዙበት ነበር። ጨዋታው በጀመረበት ደቂቃ ከመሀል ሜዳ ወደፊት የተጣለውን ኳስ ተጠቅሞ የአክሱም ከተማው ሙሉጌታ ብርሀኑ ወደ ግብ አክርሮ መትቶ የአውስኮድ ግብ ጠባቂ አድኖበታል። ከዚህ በኃላ እምብዛም ወደ አማራ ውሀ ስራ የግብ ክልል መጠጋት ያልቻሉት አክሱም ከተማዋች በ25ኛው ደቂቃ ልዑልሰገድ አስፋው እንዲሁም ሙሉጌታ ብርሀኑ ደግሞ በ40ኛው ደቂቃ ለግብ የቀረበ ሙከራ ከማድረጋቸው በቀር በርካታ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በተቃራኒው የአማራ ውሀ ስራ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ አክሱም ላይ የተሻለ ጫና ለመፍጠር ሞክሯል። 16ኛው ደቂቃ ላይም ከበስተግራ በኩል መስመር ላይ ሳሙኤል ዮሐንስ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት አምበሉ መላኩ ፈጠነ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ለውጦ አውስኮድን ቀዳሚ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኃላ የእንቅስቃሴ የበላይነት የነበራቸው አማራ ውሀ ስራዎች በቴዎድሮስ መንገሻ ፤ በድሩ ኑርሁሴን እንዲሁም ሳሙኤል ዮሐንስ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር።
በአውስኮድ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል ባመሩበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከዕረፍት መልስ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ አክሱም ከተማዎች ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል። መከላከልን ምርጫቸው አድርገው የገቡት አማራ ውሀ ስራዎች ረዣዥም ኳሶችን ወደፊት በመጣል በአጥቂው በድሩ ኑርሁሴን ለመጠቀም ጥረት ቢያደርጉም ፍሬ ሳያስገኝላቸው ቀርቷል። በሁለተኛው አጋማሽ ብዙ አላስፈላጊ ንክኪ በነበረው ይህ ጨዋታ አክሱም ከተማዋች የአቻነት ግብ ፍለጋ ደፋ ቀና እንዲሉ አስገድዶቸዋል። በዚህም የጨዋታው መጥናቀቂያ ሰዓት ላይ ሙሉአለም በየነ በግምት 18 ሜትር ርቀት ላይ አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ግብነት ተለውጦ አክሱሞች ነጥብ ተጋርተው ጨዋታውን አጠናቀዋል።
ቀጥሎ የተደረገው የተደረገው የወሎ ኮምቦልቻ እና ሽረ እንደስላሴ ጨዋታ ከመጀመሪያው ጨዋታ በኳስ ፍሰቱ የተሻለው ሆኖ ታይቷል። ይህ ጨዋታ ፍጥነት እና ሀይልም የተቀላቀለበት ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ተሽለው የታዩት ወሎ ኮምቦልቻዎች ኳስን ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለማድረስ ምንም ያህል ሳይቸገሩ የቀሩ ሲሆን አስራት ሸገሬ ፣ ሄኖክ ጥላሁን እና ዮናስ ግርማም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ኳስ እና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። በተቃራኒው የሽረ ቡድን ዕምብዛም ወደፊት መሄድ ሳይችል የቀር ሲሆን የወሎ ኮምበልቻው የመሀል አማካይ ወልዳይ ገብረ ስላሴ ወደፊት የሚመጡ ኳሶች እንከሽፉ እና ኢላማቸውን እንዳይጠብቁ ሲያደርግ ይታይ ነበር። በዚህም ምክንያት ለአጥቂው ኳስ በትክክል ሳይደርስ የቀረ ሲሆን ልደቱ ለማ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ በግራ እግሩ ከሞከራት ሙከራ ሌላ ጅላሎ ሻፊ የወሎ ተከላካዮች መዘናጋት ተከትሎ ሳሙኤል ተስፋዬ ያሻገረትን ኳስ አገባው ሲባል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ ሽረዎች ከመጀመሪያው አሰላለፋቸው በተለየ መሀል ላይ በቁጥር በመብዛት የኳስ ፍሰቱን ተመጣጣኝ ለማድርግ ችለዋል። 60ኛው ደቂቃ ላይም ሸዊት ዮሐንስ ከርቀት የመታው ኳስ ወደግብነት ተለውጦ ሽረን ወደ መሪነት አምጥቶታል። ከግቡ መቆጠር ባኃላ ወደ ኃላ ያፈገፈጉት ሽረዎች ተሳክቶላቸው መሪነታቸውን በማስጠበቅ ማሽነፍ ችለዋል። ውጤቱን ለመቀልበስ ሲጥሩ በነበሩት ወሎዎች በኩል በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት ሄኖክ ጥላሁን እና አስራት ሸግሬ እድል ሳይቀናቸው ቀርቷል። በውጤቱም ሽሬ እንደስላሴ የተስተካይ መርሀ ግብሮቹን እያሸነፈ መምጣቱን ተከትሎ ከመሪዎቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ችሏል።
ደሴ ላይ ደሴ ከተማ ኢትዮጵያ መድንን ያስተናገደበት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ደሴዎች በ24ኛው ደቂቃ በረከት ከማል በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠሩት ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችሉም በ35ኛው ደቂቃ ሀብታሙ መንገሻ መድንን አቻ ማድረግ ችሏል።