ሉሲዎቹ መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ከሊቢያ ጋር ለሚኖራቸው የመጀመርያ ዙር የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታ ዝግጅታቸውን በኢትዮዽያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ ይገኛሉ ።
በ2018 በጋና አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያው ዙር ማጣርያዉን መጋቢት 26 ቀን ከሜዳው ውጭ ከሊቢያው አቻው ጋር ለሚኖረው ጨዋታ አሰልጣኝ ሰላም ዘራይ ባለፈው ሳምንት ለ36 ተጨዋቾች ጥሪ ማድረጓ ይታወሳል ። ተጨዋቾቹ ልምምዳቸውን በሚሰሩበት አካባቢ በሚገኘው ዞላ ኢንተርናሽናል ሆቴል ማረፊያቸውን በማድረግ በኢትዮዽያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ የመጀመርያ ምዕራፍ ሦስተኛ ቀን ልምምዳቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
የመጀመርያ ጥሪ ከተደረገላቸው 36 ተጨዋቾች መካከል የድሬደዋ ከተማዋ አጥቂ ትዝታ ፈጠነ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ልምምድ ውጭ ትሁን እንጂ የተቀሩት የቡድኑ አባላት በሙሉ ጤንነት ልምምዳቸውን በቀን ሁለቴ እየሰሩ ይገኛሉ። ዛሬ መመልከት እንደቻልነውም ለመጀመርያው ጨዋታ የሚያስፈልጉ 25 ተጨዋቾችን ለመለየት በሚያስችል መልኩ በሁለት ተከፍለው በሙሉ ሜዳ ተጫውተዋል።
አሰልጣኝ ሰላም ዘራይ ዝግጅታቸው በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ መሆኑን እና ሁሉም ነገር በተሟላ ሁኔታ እየቀጠለ እንደሚገኝ ገልፃ የመጀመርያው ምዕራፍ ልምምዳቸውን ነገ በማጠናቀቅ ከተጠሩት 36 ተጨዋቾች መካከል ሰባት ተጨዋቾችን እንደሚቀነሱ አሳውቃለች ። ይህ ዝግጅት ይቀጥልና እስከሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ ድረስ ሁለተኛ ምዕራፍ ዝግጅታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ተጨማሪ አምስት ተጨዋቾችን በመቀነስ ለደርሶ መልሱ ጨዋታ የሚያስፈልጉ የመጨረሻዎቹን 25 ተጨዋቾችን እንደሚለዩ ለሶከር ኢትዮዽያ አሳውቃለች ።
በተያያዘ ዜና በሊቢያ ባለው ወቅታዊ አለመረጋጋት ምክንያት ሊቢያዎች በመረጡት ገለልተኛ ሀገር ግብፅ ላይ ጨዋታው እንደሚከናወን ታውቋል። በዚህም መሰረት የመጀመርያው ጨዋታ መጋቢት 26 ግብፅ ላይ ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ በሳምንቱ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚደረግ ይሆናል ።