መቐለ ዩኒቨርሲቲ ከሰኔ 22-29 የሚካሄደው የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታዎችን ያዘጋጃል። ስለ ውድድሩ እና ለማስተናገድ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በተመለከተም ዛሬ 10:00 ላይ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ተሰጥቷል።
እግር ኳስን ጨምሮ 10 የሜዳ እና የቤት ውስጥ ውድድሮችን ያካተተው ይህ ውድድር ለ9ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በኢትዮጵያ የተሻለ የስፖርት መሰረተ ልማት ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው መቐለ ዩኒቨርሲቲ የማዘጋጀት እድሉን ካገኘ ወዲህ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። በዛሬው መግለጫ ላይም ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ 10,000 የሚደርሱ በጎ ፍቃደኞች እንደተዘጋጁ ሲገለፅ ግንባታው ያልተጠናቀቀው የባሎኒ ስታድየምን ጨምሮ ሶስት የ3 በ 1 ሜዳዎች, 1 የቤት ውስጥ ውድድር የሚያስተናግድ ሜዳ እንዲሁም ግዙፉ የትግራይ ስታድየም ለውድድር ማከናወኛ እየተዘጋጁ መሆናቸው ተገልጿል።
በ1975 በአክራ ጋና የተጀመረው የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር በየ4 አመቱ አንድ ጊዜ ይካሄድ የነበረ ቢሆንም ከ1982 በኋላ ለ22 አመታት ተቋርጦ ቆይቷል። ውድድሩ በ2004 ናይጄሪያ ላይ ሲደረግ በድጋሚ በየሁለት አመቱ እንዲዘጋጅ ቢታቀድም በ2012 ናሚቢያ ካስተናገደችው ሻምፒዮና በኋላ የ2018ቱ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ውድድር የመጀመሪያው ይሆናል።