በእግር ኳስ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ አነጋጋሪ እና አሻሚ ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንገብጋቢ የሆነው እና በቅርብ ጊዜያት ትልቅ ትኩረት እየተሰጠው የሚገኘው የእድሜ ጉዳይ ነው። በተለይም ፊፋ በሚያዘጋጃቸው የ17 እና የ20 አመት በታች ውድድሮች የሚሳተፋ ሀገራት በተደጋጋሚ እድሜያቸው ከተቀመጠው ገደብ በላይ የሆኑ ተጫዋቾችን ሲጠቀሙ ማስተዋል የተለመደ ነው። ችግሩን ለመቅረፍ ሲባልም የፊፋ ህክምና ኮሚቴ የተለያዩ ምርመራዎችን እየተጠቀመ ይገኛል። እነዚህ ምርመራዎች ፍትሃዊ የሆነ የውድድር መድረክን ለማዘጋጀት ያላቸው አስተዋፅኦ እጅጉን ላቅ ያለ ነው።
ፖል ጋርድነር የተባለው ፀሃፊ ሶከር አሜሪካ በተሰኘው ድህረ ገፅ ላይ ከእድሜ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ሄዶ በተመለከታቸው እናም በዘገባቸው የ17 አመት ውድድሮች ላይ የታዘበውን አስፍሯል።
እ.ኤ.አ በ1985፣87 እና 89 ከ17 አመት በታች ውድድር ላይ ስኬታማ መሆን የቻሉ የአፍሪካ እና የኤሲያ ሀገራት እድሜያቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾችን ይጠቀሙ እንደነበር ጥርጥር አልነበረም። በ1989 ስኮትላንድ ባዘጋጀችው ውድድር ላይ ሻምፒዮን የነበሩት የሳውዲ አረቢያ ተጫዋቾች እድሜያቸው ትልቅ ነው በሚል ብዙ ተቃውሞ አስተናግደው ነበር። በወቅቱ የፖርቹጋል 17 አመት በታች አሰልጣኝ የነበሩት ታዋቂው ካርሎስ ኬሮዥ ” ስለጉዳዩ መናገር አልችልም። ከዚህ በኃላ ብናገር ወደ ሀገሬ እንደሚያሰናብቱኝ የፊፋ አመራሮች ገልፀውልኛል” በማለት አስገራሚ ምላሽ ሰጥተው ነበር።
በ1991 ጋናዎች አሸናፊ ሲሆኑ በንዴት ፊታቸው የቀላው የስፔኑ አሰልጣኝ ሁዋን ሳንቲስቴባን ” የታዳጊዎች አሰልጣኝ በመሆን ብዙ አመት ሰርቻለሁ፤ ጋና ያሰለፈቻቸው ተጫዋቾች ከእድሜ በላይ እንደሆኑ እርግጠኛ ነኝ” በማለት ተናግረው ነበር።
የአፍሪካ ሀገራት በወጣቶች ውድድር ያላቸውን የበላይነት በዋና ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ላይ መድገም አለመቻላቸው አንድ የችግሩ ነፀብራቅ እንደሆነ ይገለፃል። የዕድሜ ማጭበርበር ችግር ጋር በተያያዘ የአህጉራችን ስም በብዛት እየተያያዘ ቢነሳም በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች በተደጋጋሚ ሲከሰት ይታያል። በ2013 የደቡብ አሜሪካ የ20 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ለፔሩ ተሰልፎ ሲጫወት የነበረው ማክስ ባሪዮስ የተባለ ተጫዋች ሲጣራ የ25 ዓመት ኢኳዶራዊ ሆኖ መገኘቱ እና ከውድድሩ መሰናበቱ ችግሩ የአፍሪካ ብቻ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።
ቅሬታዎች እየበዙ በሚመጡበት ወቅት ፊፋ ጉዳዩን የመቅረፍ ግዴታ ውስጥ ገባ። በ2003ቱ የፊንላንድ ዓለም ዋንጫ ወቅትም የፊፋ የሜዲካል እና የምርምር ማዕከል (F-MARC) X-rayን በመጠቀም ምርመራ ማድረግ ጀመረ። ይህ ምርመራ የእጅ አጥንቶች መግጠም አለመግጠማቸውን በመለየት አንድ ተጫዋች ከ18 ዓመት በላይ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ያግዛል። የአጥንቶች ማደጊያ ስፍራዎች (Growth Plates) በውልደት ክፍት ሆነው የሚገኙ ሲሆን በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ደግሞ እየገጠሙ ይሄዳሉ። ይህንን መርህ (principle) በመጠቀም ነው ፊፋ ስራውን የጀመረው። በርግጥ በX-ray አጥንቶችን በመመልከት የታዳጊዎችን ዕድሜ የመተንበይ ምርመራ በሃገራችንም ጭምር በወንጀል ምርመራ ህክምናው (Forensic Medicine) የተለመደ ነበር። ይህም እንደ አስገድዶ መድፈር አይነት ወንጀሎች ሲፈፀሙ እና ተጠቂዎቹ ለአቅመ አዳም ወይም ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ መሆናቸው በፍርድ ቤት የቅጣት ማክበጃ ተደርጎ የሚታይ ከሆነ የሚደረግ ነበር።
የF-MARC ሰብሳቢ የነበሩት ፕሮፈሰር ጂሪ ቮራክ X-ray ከመጠቀም ይልቅ MRI የተሻለ ምስልን ከመስጠቱም ባሻገር ከx-ray ከሚወጣው ከፍተኛ ጨረር እንደሚከላከል የህክምና ቡድኑ እንዳመነበት ከተናገሩ በኋላም ይህን መሰረት በማድረግ F-MRCA የመጀመሪያ ምርመራውን ከተለያዩ አህጉራትና የዘር ግንድ በተወጣጡ 500 ተጫዋቾች ላይ አከናወነ። እነዚህ ተጫዋቾች እድሜያቸውን የሚገልፁ የልደት ሰርተፍቲኬቶች ነበሯቸው። ይህንም በመጠቀም ምርመራው ምን ያህል ተአማኒነት እንዳለው ለማወቅ ተቻለ፡፡ በእጅ ላይ የሚገኙት አጥንቶች ከ17 ዓመት በፊት አይገጥሙም በሚለው መርህ መሰረትም ምርመራው ተከናወነ። አጥንቶቹ ከገጠሙ ግን ተጫዋቹ 99.9% በሆነ እርግጠኝነት ከ17 ዓመት በታች እንደሆነ መናገር ይቻላል።
ፕሮፌሰር ቮራክ ሲናገሩ ” የእጅ አንጓ (Wrist) MRI ቀላል ፣ አስተማማኝ እና ምቹ ነው። ከ17 ዓመት በታች የሆኑ ተጫዋቾችን ያለ ምንም እክል መለየት ያስችላል።” ብለው ነበር።
የፊፋ አባል ሀገራት በየግላቸው እንደዚህ ያለውን ምርመራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም በበኩሏ ከእድሜ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄ የሚነሳባት ሀገር አንደመሆኗም ምርመራውን ማከናወን ጀምራለች። በየዓመቱ የወጣቶች የሊግ ውድድሮች ከመጀመራቸው አስቀድሞ በተለይም በጳውሎስ ሆስፒታል ይህ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። ከዚህ በፊት ከ17 አመት ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በዚህ መሰረት የተደረገውን ምርመራ ሳያልፉ ቀርተው እንደገና እድሜያቸው ትክክል የሆኑ ተጫዋቾች እንደተመረጡና በድጋሚ የተዋቀረው ቡድንም ግብፅን ከሜዳው ውጪ 3-1 መርታት መቻሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ።
በአጠቃላይ የአጥንት መግጠም (Fusion) የሚከሰተው የአጥንት ክፍል የሆኑት Epiphyses እና Metaphyses ሲገናኙ ነው። ይህ ደግሞ የሚከናወነው እድሜ እና ጊዜን ጠብቆ መሆኑ ለእድሜ ማረጋገጫ ምርመራ አመቺ አድርጎታል ። የእጅ አንጓ (Wrist) የምንለው የሰውነት ክፍል ውስጥ 8 ትንንሽ አጥንቶች (Carpal bones) ይገኛሉ። እነዚህም አጥንቶች Scaphoid, Lunate, Triquarteum, Pisiform, Trapizium, Trapizoid, Capitate እና Hamate ይሰኛሉ። ክንዳችን ላይ ሁለት አጥንቶች የሚገኙ ቢሆንም (radius እና ulna የሚባሉ) ከእጃችን አንጓ አጥንቶች (Carpal bones) ጋር ግንኙነት ያለው ግን ራዲየስ የሚባለው አጥንት ብቻ ነው። የሰው ልጅ እድሜ 17 ሲደርስ 8ቱ የካርፓል አጥንቶች ዕድገታቸውን የሚጨርሱ ሲሆን በራዲየስ እና ካርፓል አጥንቶች መሃከልም እንደአጥንት ያልጠነከረ ልስልስ አጥንት (cartilage) ይፈጠራል። ይህ ደግሞ Radius ከእጃችን አንጓ አጥንቶች እንዲገናኝ ያደርገዋል ።
ከ20 በታች መሆን አለመሆናቸውን የምናረጋግጥበት ምርመራ የሚካሄደው Scapula በተሰኘው አጥንት ላይ ነው ።Scapula (Shoulder Blade ) በጀርባችን ከ2ኛው እስከ 7ተኛው የጎድን አጥንቶች ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን በቀኝ እና በስተግራ የሚገኙ ሁለት አጥንቶችን ይገልጻል፡፡ ይህም አጥንት የተለያዩ ጡንቻዎችን ደግፎ የያዘ ነው።
እድሜያቸው ትክክል የሆኑ ተጫዋቾችን በመመልመል እና በማሰልጠን ለውድድር ማብቃት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው። ውጤት እናገኝበታለን በማለት የሚደረጉ የዕድሜ ማጭበርበር ተግባራት ለዕገዳ እና ቅጣት ከመዳረጋቸውም በላይ የሌሎችን ቦታ የሚነፍግ ፤ የታዳጊዎችንም ተነሳሽነት የሚጎዳ ትክክል ያልሆነ አሰራር ነውና መቅረት ይኖርበታል። በሃገራችን በቅርብ ዓመታት የተጀመረው እና ከወዲሁ ውጤት እያሳየ የሚገኘው በወጣቶች ውድድር ላይ የሚሳተፋ ተጫዋቾችን የዕድሜ ተገቢነት በዘመናዊ የህክምና ዘዴ የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።