በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ተስተካካይ መርሀ-ግብር ዛሬ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ወልዲያን 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
የካቲት 9 እንዲደረግ ተወስኖ በወላይታ ድቻ የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ምክንያት ተራዝሞ ወደ ዛሬ በመጣው ጨዋታ ባለማዳዎቹ ባሳለፍነው ረቡዕ የግብፁን ዛማሌክ የረቱበትን ሙሉ ስብስብ ይዘው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በተመሳሳይ ወልዲያም የሊጉን መሪ ደደቢትን በ14ኛው ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ 1-0 ሲያሸንፍ በተጠቀመበትን ሙሉ ቡድን ነበር ጨዋታውን የጀመረው። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ለቁጥር የሚያስቸግር የደጋፊ ብዛት በሶዶ ሰታዲየም ዙሪያ የታየ ሲሆን ጨዋታውም መጀመር ከነበረበት 15 ደቂቃ ዘግይቶ እንዲጀመር ሆኗል።
በመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን አረጋግተው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉ ቢሆንም ባለሜዳዎቹ ወላይታ ድቻዎች ሙከራዎችን በማድረጉ በኩል የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ገና በ2ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም እያሱ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጃኮ አራፋት በግንባሩ የሞከረበት እና ወደ ውጪ ወጣችበት አጋጣሚ ነው። በመቀጠልም 23ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ለያሬድ ዳዊት አቀብሎት ያሬድ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ክልል ያሻገራትን እና ጃኮ ሳይደርስባት ወደ ውጪ የወጣችበት ሲሆን 27ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በእለቱ በግራ መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የቆዩት ተሰፋ ኤልያስ ፣ በዛብህ መለዮ እና ያሬድ ዳዊት በጥሩ ቅብብል የወልዲያን ግራ መስመር ሰበረው ገብተው ያሬድ ዳዊት ለጃኮ አራፋት ቢያቀብለውም ኤሚክሪል ቢሊንጌ በፍጥነት ይዞበታል። ከዚህች ሙከራ በኃላም ድቻዎች ተጭነው ለመጫወት ጥረታቸውን ቀጥለው 30ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም እያሱ ለጃኮ አራፋት አቀብሎት ጃኮ ከቢሊንጌ ጋር 1 ለ 1 ተገናኝቶ አገባት ተብሎ ሲጠበቅ በሚያስቆጭ መልኩ ሙከራው ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በተመሳሳይ በ38ኛው ደቂቃ ላይም በዛብህ መለዮ ከወልዲያ ግራ ሳጥን ጠርዝ ላይ ያገኛትን ኳዋስ ወደ ጎል ሞክሮ በዳንኤል ደምሴ ተጨርፋ ወደ ውጪ ወጥታለች።
በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወልዲያዎች የአቻነቱን ነጥብ ለማግኘት በሚመስል መልኩ ኳስን መሃል ሜዳ ላይ በማንሸራሸር እንዲሁም በአንዳንድ አጋጣሚዎች በግራ መስመር በኩል በያሬድ ሀሰን እና ምንያህል ተሾመ አማካኝነት ኳስ ለአጥቂው አንዱዓለም ንጉሴ ለማድርስ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው 41ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ሀሰን በቀኝ መስመር በመግባት ያሻማውን ኳስ አንዱዓለም ንጉሴ ተወርውሮ በግንባሩ ለመግጨት ቢሞክርም ኳሷን ሳያገኛት ቀርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ የኳስ ፍሰት እና ፍጥነት ያለው አጨዋወት ለመተግበር ሲንቀሳቀሱ ቢስተዋልም ወደጎል መቅርብ እና ሙከራዎችን ማድረግ ግን አልቻሉም። በተለይም የወልዲያዎቹ ብሩክ ቃልቦሬ ፣ ምንያህል ተሾመ ፣ ያሬድ ሃሰን እና ሐብታሙ ሸዋልም ኳስን በአግባቡ ለመቀባበል እና ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ የሜዳው ጥራት ለአጨዋወታቸው ምቹ አለመሆን ተጽዕኖ ሲፈጥርባቸው ተስተውሏል፡፡ 57ኛው ደቂቃ ላይ በድቻ በኩል በሁለተኛው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ጥሩ ያልነበረው ዘላለም እያሱ በአምረላት ደልታታ ከተቀየረ በኃላ ቡድኑ በተደጋጋሚ በእሸቱ መና እና አመረላ ደልታታ አማካይነት በቀኝ መስመር በኩል ጫና በመፍጠር ወደ ወልዲያ ግብ ክልል ለመግባት ሲሞክር ታይቷል። ይህም ጫና በርክቶ 66ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ተስፉ ኤልያስ ወደ ግብ ክልል አሻግሮት ውብሸት አለማየው በግንባሩ ሲሞክር ከጎሉ በቀኝ አቅጣጫ ይገኝ የነበረው አምርላ ደልታታ በአግባቡ ተጠቅሞ ድቻን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከዚህች ጎል መቆጠር በኋላም ድቻዎች የበዛብህ መለዮን ጉዳት ተከትሎ በገባው በረከት ወልዴ እና በግብ አስቆጣሪው አምረላ ደልታታ አማካኝነት ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ለመድርስ በመሞከር ከወልዲያ በተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። በተለይም በ 75ኛው ደቂቃ ላይ አምረላ ደልታታ በቀኝ መስመር ይዞ በመግባት በቀጥታ የሞከረው ኳስ ተጠቃሽ ሲሆን በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪነቱን ያሳየው ይሄው የመስመር አጥቂ 89ኛው ደቂቃ ላይም ከግራ መስመር ያሬድ ዳዊት ያሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ሞክሮ ቤሊንጌ በአስደናቂ ሁኔታ ወደ ውጪ አውጥቶበታል። በዚህ ሁኔታ ድቻዎች ጫናቸው ቀጥሎ 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ከመሃል ሜዳ የተሸገረው ኳስ በቀኝ የጎሉ አቅጣጫ ለሚገኘው ጃኮ አራፋት ደርሶት ቀጥታ ወደ ግብ ክልል እየገፋ በመሄድ የቤሊንጌን መውጣት አይቶ ከጭንቅላቱ በላይ ከፍ በማድርግ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። እንግዶቹ ወልዲያዎችም አጥቂው ኤዶም ኮድዞን በሙሉቀን አካለ ቀይረው በማስገባት ጫና ለመፍጠር ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርተው ከሶስት ጨዋታዎች በኃላ ሽንፈት እንዲገጥማቸው ሆኗል።
በውጤቱም ወላይታ ድቻ ነጥቡን 19 አድርሶ ደረጃዉን ወደ 8 ሲያሻሽል ፤ በአንፃሩ ወልዲያ በ18 ነጥቦች 11ኛ ሆኖ የመጀመሪያውን ዙር አገባዷል።
የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡት አስተያየት
ዘነበ ፍሰሀ – ወላይታ ድቻ
“ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ በእንቅስቃሴም ጥሩ ነበርን። በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ተጋጣሚያችን ወልዲያዎች ኳስ ለመጫወት ፍፁም ፍቃደኛ አይመሱሉም። የእነሱ እንቅስቃሴ ደካማ በመሆኑ ምክንያት እኛ በርካታ አጋጣሚን ፈጥረን አምክነናል። በሁለተኛ አጋማሽ ግን በእረፍት ሰአት ተጫዋቾቼ ተጠንቅቀው እና ተረጋግተው እንዲጫወቱ እና ጎልም ማስቆጠር እንደሚችሉ ነግሬያቸዋለሁ። ተጫዋቾቹም በተቻላቸው መጠን አስተካክለው በመግባት ግቦችን አስቆጥረን አሸንፈን ወጥተናል።
” ከዛማሌክ ጨዋታ ድል በኋላ ይህን ያህል ደጋፊ ተገኝቶ ሳይ ውጤቱ የእውነት ይገባናል የሚል ስሜት ፈጥሮብኛል። በጣም ደስ ብሎኛል። ”
ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ወልዲያ
“ይህ ጨዋታ ነው ማለት ይከብደኛል። ምክንያቱም ይህ ሜዳ ነው ለማለት ይቸግረኛል። እኛ ኳስ ለመጫወት ብንፈልግም በሜዳው ምክንያት እንደፈለግን መሆን አልቻልንም። ለኛ ብቻ ሳይሆን ለድቻዎች ይህ ሜዳ የሚመቻቸው አይመስለኝም። ይህን ሜዳ ፌድሬሽኑ ሊመለከተው ይገባል፡፡”