ብሄራዊ ሊግ ፡ በቀጣዮቹ 4 ቀናት ሩብ ፍፃሜውን የሚቀላቀሉ ክለቦች ይለያሉ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ መካሄዱን ቀጥሏል፡፡ ለቀጣዮቹ 4 ቀናት የሚደረጉ ጨዋታዎችም ለሩብ ፍፃሜ የሚያልፉ ቡድኖችን ይለያሉ፡፡

እስካሁን ሆሳእና ከነማ እና ጅማ አባ ቡና ከምድባቸው ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ ወልዋሎ ፣ አርሲ ነገሌ ፣ ቡራዩ ከነማ ፣ ሱሉልታ ከነማ ፣ መቐለ ከነማ ፣ ሼር ኢትዮጵያ ፣ ውሃ ስፖርት እና ደቡብ ፖሊስ ከምድቡ መሰናበታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ወደ ሩብ ፍፃሜ ቀሪዎቹን 6 ቡድኖች ለመለየት የሚደረጉት ጨዋታዎች ከወዲሁ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ በተለይም 4 ተቀራራቢ የማለፍ እድል ያላቸውን ክለቦች ያፋጠጠው ምድብ 3 ከባድ ፍልሚያ ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምድቡን በ8 ነጥብ የሚመሩት ጅማ ከነማ እና ሀላባ ከነማ ከምድቡ መውደቃቸውን ካረጋገጡት መቐለ ከነማ እና ሼር ኢትዮጵያ ጋር ሲጫወቱ 7 ነጥብ ያላቸው ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እና ሰበታ ከነማ እርስ በእርስ ይፋለማሉ፡፡

ከምድብ 4 ከዞናቸው በአስደናቂ ብቃት የመጡት መድን እና ደቡብ ፖሊስ ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ አይደለም፡፡ ደቡብ ፖሊስ ከምድቡ መሰናበቱን ሲያረጋግጥ መድን በሌሎች ቡድኖች ውጤት ላይ የተንጠለጠለ ጠባብ እድል ይዞ የመጨረሻ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

ከምድቡ ሆሳእና ማለፉን ያረጋገጠ ሲሆን 8 ነጥብ የያዘው አውስኮድ የተሻለ የማለፍ እድል ይዟል፡፡ መውደቁን ያረጋገጠው ደቡብ ፖሊስን ካሸነፈ በቀጥታ ወደ ሩብ ፍፃሜው ያልፋል፡፡ ወሎ ኮምቦልቻ (7 ነጥብ) እና መድን (5 ነጥብ) ሆሳእና እና ውሃ ስፖርትን ካሸነፉ ወደ ሩብ ፍፃሜው ለማለፍ የአውስኮድን መሸነፍ ይጠባበቃሉ፡፡

ከምድብ 2 ጅማ አባ ቡና ወደ ሩብ ፍፃሜው ማለፉን በማረጋገጡ ለቀሪዋ አንድ ቦታ 4 ክለቦች ይፋለማሉ፡፡ 7 ነጥቦች የሰበሰበው አዲስ አበባ ከነማ ከሌሎቹ የተሻለ እድል ይዞ ማለፉን ያረጋገጠው ጅማ አባ ቡናን ይገጥማል፡፡ 6 ነጥብ የያዘው ባቱ ከነማ የአዲስ አበባ ከነማን ነጥ መጣል እየተመኘ ከሱሉልታ ከነማ ጋር ይጫወታል፡፡ 4 ነጥብ የያዙት ሻሸመኔ ከነማ እና ናሽናል ሴሜንት ጠባብ የማለፍ ተስፋ ይዘው እርስ በእርስ ይፋለማሉ፡፡

ከምድብ 1 ሶስት የማለፍ ተስፋ ያላቸው እና 3 መውደቃቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ነገ ይጫወታሉ፡፡ በ9 ነጥብ አናት ላይ የተቀመጠው ፋሲል ከነማ 8 ነጥብ ከሰበሰበው ድሬዳዋ ከነማ ጋር ይጫወታል፡፡ 8 ነጥብ ያለው ፌዴራል ፖሊስ አርሲ ነገሌን ይገጥማል፡፡ ካሸነፈም ወደ ሩብ ፍፃሜው ያልፋል፡፡

 

ፎቶ – ዛሬ ወደ ሩብ ፍፃሜው መግባቱን ያረጋገጠው ሆሳእና ከነማ

ያጋሩ