በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ሁለት ጨዋታዎች ተስተናገደው ሽረ እንዳስላሴ ወደ ምድቡ አናት ለመጠጋት ፣ ወሎ ኮምቦልቻ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የረዳቸውን ድል አስመዝግበዋል።
ሽረ እንዳስላሴ 2-1 ደሴ ከተማ
(በዳንኤል መስፍን)
በኦሜድላ ሜዳ 08:00 ላይ የተደረገው የሽረ እንዳስላሴ እና ደሴ ከተማ በሽረ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህ ጨዋታ ደሴዎች በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ብልጫ የወሰዱበትን አጋጣሚ ቢፈጥሩም በፊት መስመራቸው ላይ በቁጥር አንሰው በመገኘታቸው እንደወሰዱት ብልጫ የጎላ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም ። ሽረዎች በአንፃሩ ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ ወደ ጎል በመቅረብ የሚፈጥሩት አደጋ ቀላል የሚባል አልነበረም።
15ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን መልክ የሚቀይር አንድ ክስተት ተፈጠረ። የደሴው ግብ ጠባቂ አብርሃም ይርጉ ከግብ ክልሉ በመውጣት ኳስ በእጁ በመንካቱ የዕለቱ ዋና ዳኛ ለሽሬዎች ቅጣት ምት እና ግብጠባቂውን በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ሲያደርጉት ደሴዎች የዳኛውን ውሳኔ በመቃወም በተፈጠረው ውዝግብ ጨዋታው ከ10 ደቂቃ በላይ ለመቋረጥ ተገዷል። ጨዋታው ከተቋረጠበት ቀጥሎ በግምት 17 ሜትር ርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት ጅላሎ ሻፊ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎልነት ቀይሮ ጨዋታው በሽሬ 1 – 0 መሪነት ቀጥሏል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ የቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ደሴዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ በ34ኛው ደቂቃ ቢንያም ጌታቸው ጎል አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል ።
ከእረፍት መልስ ሽረዎች በልደቱ ለማ እና ብሩክ ገብረአብ አማካኝነት ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ሆኖም በ65ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ የተጣለለትን ኳስ ሰዒድ ሀሰን ተቀብሎ ወደ ሳጥኑ በመግባት የግብ ጠባቂውን አቋቋም በማየት የመታው ኳስ ወደ ጎልነት ተቀይሮ ሽረዎች መምራት ችለዋል። ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ሽረዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ መከላከልን በመምረጣቸው በተደጋጋሚ ከመሀል ሜዳ ወደ ፊት በሚጣሉት ኳሶች ደሴዎች ጫና በመፍጠር የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በሽረ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ በተከታታይ የነበራቸውን ተስተካካይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ነጥባቸውን 24 በማድረስ ደረጃቸውን ወደ 3ኛ ከፍ ሲያደርጉ በአንፃሩ ደሴ ከተማ ከ11 ጨዋታ 8 ነጥብ በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
አክሱም ከተማ 0-3 ወሎ ኮምቦልቻ
(በአምሀ ተስፋዬ)
በውድድር አመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታድየም የተደረገ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታ የሆነው ይህ መርሀ ግብር በፈጣን እንቅስቃሴ እና በሙከራዎች ታጅቦ ተጀምሯል። በ3ኛው ደቂቃ ላይ አክሱም ከተማዎች በሙሉጌታ ብርሀኑ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉ ሲሆን በተደጋጋሚ የተጋጣሚን የመሀል ተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት ቢሳናቸውም ኳስን በቀኝ እና በግራ ክንፍ በማመላለስ የወሎ ኮምቦልቻን የግብ ክልል በሚሻገሩ ኳሶች ሲፈትኑ ውለዋል። በተለይም በ19ኛው ደቂቃ ከግራ ክንፍ የተሻገረውን ኳስ አብዱራሂም ሙስጣፋ በደረቱ በማቆም ወደግብ ሞክሮ በግቡ አናት ሲወጣበት ልዑልሰገድ አስፋው እና ቴዎድሮስ መብራቱም ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
በተቃራኒው ወሎዎች ኳስ ሲይዙ ተጠጋግቶ በመጫወት የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾችን ወደ ራሳቸው በመሰብሰብ የተከላካይ እና የመሀል ክፍል አጣማሪ ተጫዋቾችን ሲለያዩና ተቃራኒው ቡድን በጣም በሚጠጋበት ጊዜ ኳስ ወደ ሁለቱ መስመሮች በመበተን የግብ ክልል ውስጥ በመግባት አደጋ ሲፈጥሩ ተስተውለዋል። በመጀመሪያውቹ አምስት ደቂቃዎች ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት ወሎ ኮምቦልቻዎች የመጀመሪያ ሙከራቸውን በ11ኛው ደቂቃ በሄኖክ ጥላሁን አማካይነት ካደረጉ በኃላ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ቡድን ሳጥን በመድረስ ሌሎች ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በ19ኛው ደቂቃ በግራ ክንፍ ሰለሞን ሀብቱ አመቻችቶ ለመላከ መስፍን ያቀበለው ኳስ መላከ መስፍን ከርቀት ሲሞክር ኳስ የግቡን አግዳሚ ግጭታ የወጣችበት አጋጣሚ ቡድኑን ቀዳሚ ለማድረግ በእጅጉ ተቃርባ ነበር። ሆኖም በ24ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ወጣቱ የፊት መስመር አጥቂ ሄኖክ ጥላሁን በግንባሩ በመግጨት ኳስን ከመረብ አገናኝ ወሎ ኮምቦልቻን ቀዳሚ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ከፍተኛ መነቃቃት የተፈጠራላቸው ወሎዎች ኳስን ከግባቸው ጀምሮ በመመስረት ፍጥነትን አክለውበት የአክሱም የግብ ክልልን ሲፈትኑ ታይተዋል። በ45ኛው ደቂቃ ላይም በቀኝ መስመር እየተመላለሰ ሲጫወት ያራፈደው ዳንኤል መኮንን ያሳለፈለትን ኳስ አስራት አሻግሬ ወደ ግብ አክርሮ በመምታት ወደ ግብነት ቀይሮ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።
ከዕረፍት መልስ ውጤቱን ለመለወጥ ተጭነው የታጫወቱት አክሱም ከተማዎች በ48ኛው ደቂቃ በቴዎድሮስ መብራቱ አማካይነት የጨዋታውን ውጤት መለወጥ የሚያስችል አጋጣሚ ቢፈጥሩም የወሎ ኮምበልቻው ግብ ጠባቂ አስራሚ በሆነ መንገድ አድኖበታል። ግብ ጠባቂው በ52ኛው ደቂቃ ላይም ልዑልሰገድ አስፋው ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ጠርዝ ላይ ሁለት የወሎ ኮምቦልቻ ተከላካዮችን በማታለል ወደግብ የመታትን ኳስ በድጋሚ አድኖበታል። በዚህ ሁኔታ አክሱም ከተማዋች ውጤቱን ለመለውጥ በዛ ያለ ሙከራዋች ቢደርጉም ሳይቀናቸው ቀርቷል።
ወሎዎች ከእረፍት እስከ 68ኛው ደቂቃ ድረስ ብልጫ ተወስዶባቸው የቆየ ቢሁንም ከስልሳዎቹ ደቂቃዋች በኃላ በእንቅስቃሴ መሻሻል በማሳየት ከመከላከል ሀሳብ ወጥተው ማጥቃት በመቻላቸው የግብ ዕድል መፍጠር ጀምረዋል። በዚህ ሂደትም የአክሱም ከተማ ተጨዋቾች ለማጥቃት ቦታቸውን ለቀው በሚወጡበት ወቅት በረጅሙ ወደ ፊት የሚጣሉት ኳሶች ለተከላካይ ክፍላቸው ፈተና ሆኖባቸውም ነበር። በተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድ 78ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስን ተክቶ የገባው ዘነበ አብርሀም ከቀኝ መስመር በፍጥነት ይዞ የገባውን ኳስ ወጣቱ አጥቂ ሄኖክ ጥላሁን ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛ ግብ አድርጓታል። በዚህች ግብም ዎሎ ኮምቦልቻዎች ጨዋታውን በሶስት ግቦች ልዩነት ማሸነፍ ችለዋል።
ውጤቱ መጥፎ አጀማመር ያደረገው ወሎ ኮምቦልቻ ነጥቡን 8 በማድረስ ወደ 13ኛ ከፍ እንዲል ሲረዳው አክሱም ከተማ በ13 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።