የአሰልጣኞች ገጽ | የውበቱ አባተ እግርኳሳዊ ሐሳቦች [ ክፍል ሁለት ]


የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት በሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ማቅረባችን የሚታወስ ነው። በክፍል አንድ መሰናዷችን አሰልጣኙ በእግርኳስ የተለያዩ ሀሳቦች ዙርያ ያለውን አተያይ ከስራ ልምዱ በመነሳት አጋርቶናል። ዛሬም በክፍል ሁለት ሀሳቡን ማጋራቱን ይቀጥላል።


ሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም 


ክፍል አንድን ሊንኩን ተጭነው ያገኛሉ | LINK


በኢትዮጵያ እግርኳስ አሰልጣኞች ከውጤት ጋር በተያያዘ ብቻ የሚመዘኑበት ጠባብ መስፈርት ምን ያህል ጎጂ ነው? ብዙውን ጊዜ በአጨዋወት የማራኪነት ይዘት፣ በረጅም ጊዜ እቅድ ጠንካራ መሠረት የጣለ ዘላቂ ቡድን መስራት፣ በወጣቶች ላይ እምነት ጥሎ ቡድን የሚገነባ እና ሌሎችም የአሰልጣኞችን ብቃት ግምት ውስጥ የማይከተው የመገምገሚያ መንገድ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አብራራልን

ይህ እንደ ክለቦቹ አስተዳደሮች ፍላጎት ይለያያል፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም! ብዙውን ጊዜ ቀጣሪዎችህ ውጤት ላይ ያተኩራሉ፡፡ ዋናው ነገር ‘የትኛውን አይነት ውጤት ነው እንድታመጣ የሚፈለገው?’ የሚለው ይመስለኛል፡፡ ዋንጫ ማስገኘት፣ ደረጃ ውስጥ ማስገባት፣ ወይስ ወደ ታችኛው የውድድር እርከን ከመውረድ ማትረፍ…? ልትገመገምባቸው የሚገቡ መመዘኛዎች መሆን ያለባቸው እነዚህ ይመስሉኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ ላለመውረድ የሚታገልን ቡድን ብትይዝና እስከ ተወሰነ ሳምንት ድረስ ያስመዘገብከው ውጤት ከቡድኑ እቅድ አንፃር እጅግ አናሳና ተስፋ ሰጪ ካልሆነ “የመረጥንህ ክለቡ ወደ ታችኛው ሊግ እንዳይወርድ ቢሆንም እየተመዘገበ ያለው ዝቅተኛ ውጤት ደግሞ ቡድኑ ወዴት እየሄደ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ እየተፈጠረ ያለው ችግር ምንድን ነው?” ተብለህ መጠየቅ አለብህ፡፡

“በሒደት ወጣቶችን እንድታፈራና እስከዚያው ድረስ ግን ቡድናችን በዚህ የደረጃ ወሰን ውስጥ እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡” ልትባልም ትችላለህ፡፡ መገምገም የሚኖርብህ በተሰጠህ የሐላፊነት ልክና በተሰፈረልህ የእቅድ መጠን ነው፡፡ እኔ እንዲያውም ከክለቦች ይልቅ በብሔራዊ ቡድኖች ደረጃ ያለው ነገር አይመቸኝም፡፡ ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠን እንደ መስፈርት ከሚወሰዱት ነገሮች አንዱ ውጤት ነው፡፡ ውጤት መመዘኛ መስፈርት ይሆንና <አንደኛ እና ሁለተኛ> የወጣውን አሰልጣኝ <ላለመውረድ> ከሚታገለው አሰልጣኝ እኩል ውድድር ውስጥ ይገባል፡፡ ከዚያም አንደኛ ደረጃ ላይ ያለውን ‘ጎበዝ አሰልጣኝ’፥ በሰንጠረዡ ግርጌ ያለውን ደግሞ ‘ሰነፍ አሰልጣኝ’ በማለት ይፈረጃል፡፡ እኔ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ተገቢ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ውጤት ያለው አሰልጣኝ <ምን ግብአት አግኝቶ እና በምን ላይ ሰርቶ?>፤ ሌላኛው በደረጃ ዝቅ ያለውስ አሰልጣኝ <የነበረው ግብዓትና የሰራበት የትኩረት አቅጣጫ  ምን ላይ ነበር?> በሚል አግባብ መለካት ቢለመድ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

ሁሉም ቡድኖች ተመሳሳይ ደረጃ ሊኖራቸው እንደማይችል እየታወቀ ውጤትን ዋነኛ መስፈርት አድርጎ የስራ ልምድ ማስረጃዎችን (ሲቪ) በመመልከት “እገሌ እኮ ዋንጫ በልቷል!፤ ዋንጫ ላገኘ ደግሞ መስፈርቱ 25 ነጥብ ያሰጣል፡፡” በሚል አሰራር ዋንጫ ያላገኘ 25 ነጥቦችን ያጣል ማለት ነው፡፡ ውጤታማነት የሚታይበት መንገድ ቴክኒካልም አይደለም፤ ቁጥር ላይ የተመረኮዘ፣ ለሌላ ጉዳዮች ዋጋ የማይሰጥና መደረግ የሌለበት ነው፡፡ ደጋግመህ ዋንጫ ብታሳካ አልያም በብዛት ዝቅ ባለ ደረጃ ብትጨርስ “በምን አይነት ቡድን ነው?” ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ክለቦች ጋር ግን ቅድሚያ የሚሰጡት ነገር ስላለ ሊያሰናብቱህም ሊያቆዩህም የሚችሉት በራሳቸው መንገድ ነው፡፡ አመራሮቹ መጠየቅ ያለባቸውም ከአሰልጣኙ ጋር በገቡት ውል መሰረት <የተስማሙትን> መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ ለዋንጫ መፎካከር የሚችል ስብስብ ይዘህ ላለመውረድ የምትጫወት ከሆነ ሁኔታውን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ነው ‘በያዝነው ነገር መለካት አለብን፡፡’ የምለው፡፡ ለምሳሌ በእኛ ክለብ ዙሪያ ብዙሃን መገናኛዎች ላይ የተለያዩ ነገሮች እሰማለሁ፡፡ ከB ቡድን ያደጉ 13 ልጆች አሉን፡፡ ከዋናው ቡድን Back-4 (አራቱ የመከላከል መስመር ተጫዋቾች) በአዳማው ጨዋታ (ቃለ መጠይቁ የተደረገው አዳማ ከሐዋሳ በአዳማ ከተማ ከተጫወቱ በኋላ ነበር፡፡) ሶስቱ ከታች የመጡ ተጫዋቾች በቋሚነት ተሰልፈዋል፡፡ ማንም ሰው ያንን ተግባር በመልካም ጎኑ ሲያነሳ አላይም፤ እውነታው ይህ ስለሆነ እንጂ በውሳኔዬ ለመወደስ አልያም በሽፋን ስር ለመጠለል አስፈልጎኝ አይደለም፡፡ “በታዳጊዎቹ ልጆች ከመጠቀም ይልቅ ልምድ ባላቸው ለምን አልተጫወትክም?” ተብዬ ልጠየቅ እችላለሁ፡፡ የዝውውር ሒደቶች በራሳቸው የተሻሉና ምርጥ ተጫዋቾችን የማንጠቀምበት ሁኔታዎችን ይፈጥሩብናል፡፡ ለምሳሌ ‘ጋዲሳ መብራቴ ለምን ለቀቀ? ጥሩ ገንዘብ ስለቀረበለት፤ለምን ሙጂብ ቃሲም ወደ አዳማ፣ ጃኮ አራፋት ደግሞ ወደ ወላይታ-ድቻ አመሩ? በተመሳሳይ የተሻለ ገንዘብ ስለቀረበላቸው ነው፡፡ አስቻለውስ ለምን ወደ ቡና ሄደ? እንዲሁ በገንዘብ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ የምታሰለጠንው ቡድን ሌሎቹ የሚጓዙበትን መንገድ የማይከተል ከሆነ ቆም ብለህ ታስብና ማድረግ ያለብህን ትወስናለህ፡፡ ‘ልጆቼን ብቁ ማድረግ አለብኝ፡፡’ ወደሚል ድምዳሜም ትደርሳለህ፡፡ በወጣቶች ስትሰራ ደግሞ በዛ ውሳኔህ ከምትገመገምበት ይልቅ አንድ የተወሰነ ርዕስ ተመርጦ በሱ ረዘም ያለ ክርክር፣ ውይይትና ተገቢ ያልሆነ ትችት መቅረብ ይጀምራል፡፡

ለምሳሌ በዚህ አመት በሙሉአለም ረጋሳ ጉዳይ እንደተነሳውና ለረዥም ጊዜ የቆየው (ወደ 4 ወር ገደማ የፈጀ) ሁኔታ ማለቴ ነው፡፡ “እንዴት ሙሉአለም ወደ ኳስ ተመለሰ?” አይነት ከርክር፡፡ እኔ እኮ ወደ ላይ ባሳደኳቸው 13ቱ ልጆች ቦታ ለጊዜው 6 ተጫዋቾችን ከብሄራዊ ሊጉ ክለቦች ባስፈርም  ይሻለኛል፤ ውሳኔውን እንደ ቡድን እና እንደ አገር ካየኸው ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ለራሴ ሲቪ የምጨነቅ ከሆነ “እናንተ ሌላ የሚያድጉበትን መንገድና ሁኔታ አመቻቹላቸው፤ እኔ ግን እነዚህን ተጫዋቾች አልፈልግም፡፡ የምፈልጋቸውን ተጫዋቾች በግዢ አምጡልኝ፤ አለበለዚያ በስምምነት ስራውን ማቆም እችላለው፡፡” ማለት አይከብደኝም፡፡

የምንመዘንበት መንገድ የእኛ አገር አሰልጣኞችን እድለኛ አያደርግም፡፡ ለምሳሌ የእናንተው ባልደረባ ኦምና ታደለ ጋር በጋቶች ጉዳይ ደውዬለት ነበር፡፡ ጋቶች በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ ስለ ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች ባነሳው ነገር ከልቤ አዝኜበት ነበር፡፡ በእርግጥ እኔን በግል አልሰደበኝም፤ ሆኖም ግን ሙያውንና አሰልጣኞችን ማክበር አለበት፡፡ ተጫዋቹ ከመሰረቱ ጀምሮ አሁን ያለበት ደረጃ እስከሚደርስ ድረስ በርካታ አሰልጣኞች በተጫዋችነት ህይወቱ ወስጥ አልፈዋል፡፡ መጀመሪያ የመለመሉት፣ ወደዚህ ያመጡትና ያሰለጠኑት፣ ያሰሩት፣ ያበሉትና ያጠጡት አሰልጣኞች ወይም ሰዎች የእግርኳስ ግንዛቤያቸው በየትኛውም ደረጃ ይገኝ ዋጋ አላቸው፡፡ ‘አባትህን እውቀት የለውም’ ብለህ እኮ ልትንቀው አይገባህም፡፡ ቤታችንን የምንንቅ ከሆነማ ሁላችንም ጎዳና መውጣት ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ ወደ ውጪ ወጣ ስትል ያለውን ልዩነት ማንም አያጣውም፤ ያንን ስላየህ ይህንን መናቅ አለብህ ማለት ነው? በአጋጣሚ ጥሩ እድል ከተገኘ የተሻለ ቦታ ልትገኝ ትችላለህ፡፡ ሌሎች ያንን እድል ያላገኘን ብዙ ነገር አምልጦን ሊሆን ቢችልም የራሳችን የሆነ ነገር ደግሞ ይኖረናል፡፡ ለምሳሌ እኔ ስለ እግርኳስ ባለኝ አመለካከት ከማንም የማላንስበት ነገር አለኝ ብዬ እከራከራለው፡፡ በኳስ ባለን ትምህርት፣ ችሎታ ወይም አቅም ማንም ሊበልጠን ይችላል፡፡ “ስለኳስ ምንም ግንዛቤው በሌላቸው ሰዎች ነው ስንሰለጥን የቆየነው፡፡” የሚል አስተያየትን ስህተት አድርጌ ነው የማስበው፡፡ በእርግጥ እሱ ላይ ብቻ አይፈረድም፡፡ ከዚያ በፊትም የተለያዩ  የክለብ አመራሮች ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

“አሰልጣኞቻችን Lesson Plan የላቸውም፡፡” የሚል ትችትም ቀርቦ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ Lesson Plan እኮ የከተማ ፕላን አይደለም፡፡ የምታስተምረውን ነገር ወይም ወርሐዊና አመታዊ እቅድህን ለመስጠት ከባድ ነገር አይሆንም፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ “አያውቁም፤ አልተማሩም፡፡” እንባላለን፡፡ ውዝግቦችን መፍጠር ስለማልፈልግ ነው እንጂ በአሰልጣኞች ላይ የሚነሱ ብዙ አግባብ ያልሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ባለሙያዎቻችንን እያከበርን የሚጎድላቸውንና የሚቀራቸውን ነገሮች ብንወያይና ጥረት አድርገን የምንሻሻልበትን ሁኔታ ብንፈጥር የሚሻል ይመስለኛል፡፡ መጠየቅ  ሲኖርብንም ስርዓት ባለው መንገድ መወቀስና መተቸት ይገባል፡፡ ለዚህ አገር እግርኳስ ችግር የመጀመሪያዎቹ ተጠያቂዎች እኛው አሰልጣኞች ነን፤ በዘርፉ እየሰራንና እየተከፈለን ያለነው ባለሙያዎች በመሆናችን ከእኛ ውጪ ሌላ ማን ሊጠየቅ ይችላል? ነገርግን የምንሻሻለው ለከት ባጣ ትችት ስለተቀጠቀጥንና ስለተብጠለጠልን ወይም ደግሞ ያለውን ነገር እንደሌለ በማሰብና ዋጋ ባለመስጠት አይደለም፡፡ እውነቱን ለመናገር አገር ውስጥ እየመጡ ያሉትን የውጭ አሰልጣኞች በእግርኳስ እይታ ዙሪያ በሚፈልጉት ነገር ላይ ቁጭ ብለን ስናወራ ምንም የተለየ ነገር አለመኖሩን ነው የምንገነዘበው፡፡

ግርም የሚለኝ ይህ ሁሉ ተመልካች የመጣው በፈረንጆቹ አሰልጣኞች ነው እንዴ? እስቲ ተመልከት ያን ሁሉ ከስታዲየሙ ተርፎ በየሰፈሩና በየአደባባዩ የሚታየው የቡና ደጋፊ ፈረንጅ ነው ያመጣው? አይደለም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስስ ቢሆን በፈረንጆች ስለሰለጠነ ነው እንዴ ቡድኑ በተደጋጋሚ ዋንጫ የሚያሸንፈው? አይደለም፡፡ በአስራት ሐይሌ ሰባት ጊዜ ወስዷል፤ በመንግስቱ የአሰልጣኝነት ዘመን ዋንጫ አሸንፏል፤ ስዩም ከበደም ቢሆን ይህንኑ አሳክቷል፡፡ ጊዮርጊስ ከጥንት ጀምሮ መሀል መሀል ላይ ሌሎች ቡድኖች ቢገቡበትም ዋንጫ ሲያገኝ የኖረ ክለብ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ፈረንጅ ስለመጣ አይደለም፡፡ በእርግጥ ‘ከውጪ የሚመጡ አሰልጣኞች እውቀት የላቸውም’ ማለት አይደለም፤ ያላቸውም የሌላቸውም አሉ፡፡ ጉብዝናቸውና ድክመታቸው ላይ አስተያየት የምንሰጠው ስራቸውን በደንብ ከመረመርን በኋላ ነው፡፡ ዝምብሎ በጅምላው “ከኛ አገር አሰልጣኞች የውጪ አሰልጣኞች ይሻላሉ፡፡” ማለት ልክ አይመስለኝም፡፡ ፈረንጅ ስለመጣ ብቻ እኮ ለውጥ አይመጣም፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያ 15 ብራዚላውያንን ብታመጣና ለአፍሪካ ዋንጫ ብታልፍ በምንድን ነው ደስ የሚለን? ለአሰልጣኙ   ችግር ላይኖረው ይችላል፤ ግን በቃ የራሳችንን ነገር ነው ማግኘት ያለብን፡፡

በየጊዜው ከውጪ የሚመጡ አሰልጣኞች ብዙ ገንዘብ እያስወጡህም የምትፈልገውን ላያሳኩልህ ይችላሉ፡፡ የክለብ አመራሮች ለምን እዚህ አገር ያለ አሰልጣኝ ላይ እምነት ጥለው ስራውን አያሰሩም?ለምሳሌ በኢትዮጵያ ቡና በጥሩ ብቃት ተጫውተው ያሳለፉ ብዙ ተጫዋቾች አሉ፡፡ የላይሰንሱ ጉዳይ ይቅርና በስም ልናነሳቸው የምንችላቸው እነ አንዋር፣ ካሊድ፣ እድሉ፣ አሸናፊ በጋሻው፣ ደብሮም እና ሌሎች በርካታ የቀድሞ ተጫዋቾችን ሰብስበህ የቡናን ጠንካራ የአሰልጣኞች ስታፍ አዋቅረህ ከውጪ ደግሞ በአሰልጣኝነት ጥሩ ልምድ ያላቸውን ኮርስ የሚሰጡ ባለሙያዎች ታመጣና የሚያስፈልገውን ተግባራዊና የጽንሰ-ሐሳብ ትምህርት እንዲማሩ ታደርጋለህ፡፡ ይህንን በተለያዩ ወቅቶች እና በተለያዩ ባለሙያዎች እየደጋገምክና ራሳቸው ደግሞ በግል እንዲጥሩ እየረዳሀቸው የራስ መተማመናቸውንና አቅማቸውን አጎልብተህ ብቁ ከሆኑ ሐላፊነት ትሰጣቸዋለህ፡፡በዚህ መንገድ በየክለቦቹ የራሳችንን ብቁ አሰልጣኞች ማፍራት የምንችል ይመስለኛል፡፡

እነዚህንና ሌሎች ብዙ ችግሮችን ስታይ አሰልጣኝነት እንደ ተራ ነገር መሰደቢያ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ጎበዝ አሰልጣኞችን መጠየቅ፣ ‘አያውቁም’ ተብለው የሚታሰቡትን ደግሞ ማሳወቅ፡፡ መባል የማይኖርባቸውን ነገሮች መተው! አሁን እናንተ የከፈታችሁት ገጽ ምንአልባትም የተወሰኑ ሰዎችን አመለካከት በመቀየር ረገድ መጠነኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብዬ አስባለው፡፡

ሌላው በተደጋጋሚ ጊዜ በሚዲያዎች የምሰማው “አሰልጣኞች ሌቦች ናቸው፡፡” የሚለውን አስተያየት  ነው፡፡ እንደዚህ አይነት አሉታዊ አስተያየቶችን ከሚሰጡት ውስጥ ደግሞ ራሳቸው አሰልጣኞች ይገኙበታል፡፡ ሚዲያ ላይ “የሆነ ቡድን አሰልጣኝ የምትሆነው ለኮሚቴ ገንዘብ ከፍለህ ነው፡፡” ብሎ ይናገራል፡፡ ራሱ አሰልጣኝ ነው፤ ነገ እኮ ይቀጠራል፡፡ ሲቀጠር እሱ ከፍሎ ነው የሚቀጠረው? ምን ማለት ነው? በራሱ ላይ የደረሰበት ችግር ካለ “በእንደዚህ አይነት ቦታ ይህን አይነት ችግር ገጥሞኛል፡፡” ብሎ በድፍረት ግልጹን መናገር! አለቀ! በቃ! እኔ አንተን ሌባ እላለው፤ አንተ እሱን ሌባ ትላለህ፤ እሱ ደግሞ እኔን ሌባ ይላል፡፡ ይህስ ምን ማለት ነው? ማን ማንን ነው ሌባ የሚለው? ” ጎበዝ የሆነ ሰው ልክ አሁን እናንተ ቁጭ ብላችሁ እንደምታዋሩኝ ሙሉ መረጃ ይቅርና ትንሽ መረጃ ይዞ መጥቶ ‘በጭምጭምታ የሚነገር እንደዚህ እንደዚህ አይነት ነገር አለ፡፡ ለምን አታጠራውም?’ ብሎ መጠየቅ! እኔ በተፈጥሮዬ ፊትለፊተኝነትና ግልጽነትን እደፍራለሁ፤ የሆነ ነገር ካየሁብህ እነግርሀለው፤ ማስተካከል ያለብህን ጉዳይ ካለም ‘አስተካክል!’ እልሀለው፡፡ ‘ይጠቅምሀል-ይጎዳሀል?’ አንተ ትወስናለህ፡፡ ከጠቀመህ ትወስዳለህ፤ ካልጠቀመህ ትተወዋለህ፡፡

በዚህ መንገድ ለመማማር ስንችል ለምን ወደ መወነጃጀል እንሄዳለን? ስለተወነጃጀልክ እኮ ምንም የሚፈጠር ነገር የለም፡፡ በእርግጠኝነት የምናገረው የራስህን ሰው ካላከበርክ ማንም አያከብርህም፡፡ እኔ አንተ ለምትሰራው ስራ እውቅና ካልሰጠው እና በተገቢ ሁኔታ ካላከበርኩህ ምንድን ነው የምፈይደው? የእኛ ባለሙያዎች ዝም ማለት በራሱ ራሳችንን መከላከል እንዳንችል አድርጎ ትችቱና ወቀሳው ከአቅም በላይ ሄዷል፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ እስክናዝን ድረስ አሰልጣኞች በየቦታው እንሰደባለን፤ የማያውቁን ሰዎች ሁሉ እኮ ናቸው የሚሰድቡን፡፡

ካቻምና ወሊሶ ሄደን የገጠመኝ ነገር አለ፡፡ “በተቀያሪዎች መቀመጫ በስተቀኝ ያለው የእንግዳው ቡድን ነው፡፡” የሚል ደንብ ለሁላችንም ተሰጥቶናል፡፡ እዛ ስንሄድ እነሱ ቀኙ ላይ ሄደው ተቀመጡ፡፡ “በቀኙ መቀመጥ ያለብን እኛ ነን፡፡” በሚል ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ ኮሚሽነሩ ወደ አዲስ አበባ ደወለ፡፡ ‘እንዴት ወደ አዲስ አበባ ትደውላለህ? ይህቺን ችግር ራስህ መዳኘትና መፍታት አትችልም?’ ብዬ ጥያቄ አንስቼ መጨቃጨቁ ቀጠለ፡፡ ይህን የሚያይ አንድ ደጋፊ “ውበቱ ሌባ!” በማለት መሳደብ ጀመረና ጨዋታው እስኪያልቅ ስድቡ ቀጠለ፡፡ ወደ መጨረሻ አካባቢ እኔ ራሴ መሳቅ ጀመርኩ፡፡ ከመናደዴ የተነሳ የመውረድ ደረጃ ላይ ስለሚገኙ ‘ደግነቱ ዛሬ ብቻ ነው የምትሰድቡኝ፤ ሌላ ጊዜ ወደዚህ ስለማንመጣ ብዙም ችግር የለውም፡፡’ አልኩኝ፡፡ ሰው እኮ ሳያውቅህ ነው የሚሰድብህ፤ ሌባ የሚልህ፡፡ አንድ ጊዜ ደግሞ 2000ዓ.ም አካባቢ እንዲሁ ጎንደር ላይ ለመጫወት ሄድንና ሀይለኛ ዝናብ ጥሎ መጫወት አልቻልንም፡፡ በማግስቱ “ባህርዳር ሄዳችሁ ተጫወቱ፡፡” ተባልንና ወደ ባህርዳር ተመለስን፡፡ ጨዋታው ከፋሲል ጋር ነበር፤ አሰልጣኛቸው ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ነበር፡፡ እየተጫወትን አንደኛው ደጋፊ ከትሪቡን እንደጉድ ይሰድበኛል – “ይህን እግርኳስ 30 አመት ሙሉ ገድለኸው…” ሲለኝ በጣም ሳቅኩኝ፤ እኔ እኮ አሰልጣኝነት ከጀመርኩ ገና 2 አመቴ ነበር፡፡  ዞር ብዬ ሳየው “ምን ታየኛለህ ደሞ? አይንህ ይፍሰስ!” ይለኛል፡፡ በእኛ ሙያ እኮ ዙሪያ ገባውን ነው የምትሰደበው፤ ደጋፊው፣ የክለብ አመራሮች አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛውም ይጨፈልቅሀል፤ ታዲያ ምንድን ነው የምታተርፈው? ቢያንስ እንደዚህ ራሳችንን የምንገልጽበት መድረክ መፈጠሩ ጥሩ ነው፡፡

እንደዚህ አይነት ድርብርብ ችግሮች ተስፋ መቁረጥ ውስጥ አሊያም “እኔ ምን አገባኝ!” የሚል አመለካከት ውስጥ አልከተተህም? ‘ለማይለወጥ ነገር ይህን ባበረክትም ባላበረክትም ምን እፈይዳለሁ?’ ብለህ አታውቅም?

በፍፁም!!! እኔ በተፈጥሮዬም ቢሆን እንደዚህ አይነት ሰው አይደለሁም፡፡ ተስፋ የመቁረጥ ነገር አላስተናግድም፤ በተለይም ደግሞ በእግርኳስ ሁልጊዜ ተስፈኛ ነኝ፡፡ ነገሮች ይለወጣሉ፤ እኛም እንቀየራለን የሚል ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡ ሰፈር ውስጥ በማሰለጥንበት ጊዜ አዲስ አበባ ጨዋታ ለማየት መጥቼ ወደ አዳማ እየተመለስኩ በህዝብ ማጓጓዣ መኪና ውስጥ አንድ ሳምሶን ጨነቀ የሚባል ድሮ የመብራት ሐይል ተጫዋች የነበረ ጓደኛዬ ጋር ተገናኘንና አብረን ተቀምጠን  በኢትዮጵያ እግርኳስ ዙሪያ ስናደርግ የነበረው ውይይት በአካባቢያችን የነበሩትን ሰዎች ትኩረት ሳበ፡፡ የእሱ እምነት “ይህቺ አገር እግርኳሷ ባጠቃላይ ተስፋ የለውም፡፡” የሚል ነበር፡፡ እኔ ጋር ደግሞ ጥሩ ተነሳሽነትና ተስፈኝነት ስለነበረ “በፍጹም ነገሮች ከተስተካከሉ ጥሩ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡” እያልኩ ተከራከርንና በመጨረሻ ላይ “ያንተ ነገር በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ጭላንጭል ብርሀን አይቶ ተስፋ እንደሚያደርግ ሰው ነው፡፡” አለኝ፡፡ ነገሮች ይቀየራሉ፤ ስለእውነትም ስለማይመስሉን ነው እንጂ የተለወጡ ነገሮችም እኮ አሉ፡፡ ተጫዋቾች ወደ ውጪ ሀገሮች ወጣ ብለው መጫወት ጀምረዋል፤ጥቂት አሰልጣኞችም ቢሆኑ እየወጡ ማሰልጠን ጀምረዋል (አብረሐም መብራህቱ፣ ስዩም ከበደ፣ ሰውነት ቢሻው – በየመን፤ እኔም በሱዳን ሰርተናል)፡፡ ያለብዙ ስራ እነዚህ ነገሮች ከተገኙ አቅደንና ጠንክረን ከሰራን ለውጥ የማይመጣበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚያስፈልገን ጠንካራ መሪ ብቻ ነው፤ ያንን ካገኘን ሁሉም ነገር ይቀየራል፡፡ የህዝብ ወይም የአገር ሰነፍ የለም፤ መለወጥ እንችላለን፡፡ ስለዚህ እኔ ተስፋ ቆርጬ አላውቅም፡፡

እውቀትህን ለማዳበር በርካታ የእግርኳስ መጻሕፍትን እንደምታነብ፤ ተግባራዊ የልምምድ ስልጠናህን ደግሞ በዘመናዊ መሳሪያዎች እንምታሰራ እናውቃለን፡፡ እነዚህና ሌሎችም ግብዓቶች ስራህን ምን ያህል እያቀለሉልህ ነው?

ዘመናዊ የተግባር ማሰሪያ ቁሳቁሶቹ እጅጉን ይጠቅሙሀል፡፡ ተጫዋቾቹ የተሻለ ስራ እንዲሰሩ ይረዳሀል፤ መስራት የምትፈልገውን ተግባር እንድታከናውን ያግዝሀል፡፡ መጻሕፍቱ ደግሞ በእግርኳሱ አዳዲስ የሆኑ ነገሮችን ያስገነዝቡሀል፡፡ የትልልቅ አሰልጣኞችን የህይወት ተመክሮ ትማርበታለህ፤ ፈተናዎችን እንዴት እንዳለፉ፣ እግርኳሳዊ ፍልስፍናቸው ምን ላይ እንደሚያተኩር፣ ምን አይነት ግብአቶችን እንደሚጠቀሙ እና ሌሎችንም ብዙ ነገሮች ያሳውቁሀል፡፡ እነዚህ ሁሉ ደግሞ ያለህን አቅም እንድታጎለብት ያደርጉሀል፡፡

በቅርቡ ለተጫዋቾቼ ክላስ ውስጥ ሁሌም መሀል መሀል ላይ እንደማደርገው በLCD ዘና የሚሉበትን የሆነ በታብሌቴ ከራሴ ቴሌቪዥን የቀረጽኩትን ምስል አሳየኋቸውና ወዲያው መሳሳቅ ጀመሩ፡፡ እኔ ባሳየኋቸው አዝናኝ ምስል የሚስቁ መስሎኛል፡፡ በኋላ እርስበርስ ሲንሾካሾኩ ሰማሁና ‘ይህን ያህል አስቋችሁ ነው ብዬ?’ ጠየቅኋቸው፡፡ ለካ እኔ ያላስተዋልኩት እነሱ ግን ያዩት ነገር ነበር፡፡ የቤቱ ቴሌቪዥን 29 ኢንች ስፋት ያለው ከኋላው የጎበጠ የድሮ ሞዴል ቲቪ ነው፤ ስለቆየ የቻናል መቀያየሪያ ቁልፎቹ ወደ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እነሱ የሚስቁት “የኮች ቲቪ የነተበች ናት፡፡” በሚል ስሜት ነው፡፡ ለነገሩ ሲነግሩኝ እኔም እነሱ ባዩበት አቅጣጫ ተመልክቼ በጣም ሳቅሁኝ፡፡ ‘ይህ ዘመናዊው ፍላት ቲቪ ዋጋው ስንት ነው? ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ መልስ አልሰጡኝም፤ ዝምታን መረጡ፡፡ ‘እኔ ዋጋውን አላውቀውም፤ ያያችሁትን ቲቪም ቢሆን በስጦታ መልክ ያበረከተልኝ ሰው ነው፡፡ እኔ ላሳያችሁ የፈለግሁት እና እናንተ ያያችሁት ነገር አልተገጣጠሙም፡፡ ለማንኛውም ይህ የምታዩት የአፕል ምርት ላፕቶፕ 34 ሺህ ብር ነው፤ ይህ ሶኒ ፕሮጄክተር ደግሞ በ800 ዶላር የተገዛ ነው፡፡ ሌሎች ሌሎችም በራሴ ያወጣኋቸው ወጪዎችን ለስራችን ስል ያደረግሁት ለኔም ለናንተም ስለሚጠቅመን ነው፡፡ ቲቪው ምናልባት 20ሺ አለዚያም 30ሺ ቢሆን እንኳ መግዛት ከባድ ነገር ሆኖ አይደለም፤ ቅድሚያ የምሰጠውና የሚያስጨንቀኝ ኳሱ ነው፤ ቤቴን እንኳ ቦታ አልሰጠሁትም፡፡’ ብዬ መከርኳቸው፡፡ አየህ ሰው የሚያየው ሌላውን ነገር ነው፡፡ ከስልጠና ጋር በተያያዘም ሁሉንም የልምምድ አይነቶች በምፈልገው መርሃ ግብር መሰረት የማዘጋጀው  ሶከር ቱቶር፦ታክቲካል ማናጀር 2.6 የሚባለውን ሶፍትዌር በመጠቀም ነው፡፡ ይህንንም በራሴው ገንዘብ የገዛሁት ነው፡፡ በሶፍትዌሩ የትኛውንም አይነት የልምምድ ፕሮግራሞች ትፈጥርበታለህ፡፡ ይህን እንኳ ለማድረግ ሶፍትዌሩ፣ ላፕቶፕና ፕሪንተር ያስፈልግሀል፤ ሁሉንም የማዘመኛ ስራ በራሴ ወጪ ነው የምሰራው፤ ሁሌም በሙያህ ወደተሻለ ነገር መጓዝ ገንዘብ ሊያስወጣህ ይችላል፡፡ ሆኖም ገንዘቡን ያገኘኸው ከእግርኳሱ ስለሆነ የምታወጣውም ለእግርኳሱ እንደሆነ ማሰብና መልሰህ እንደምታገኘው ማወቅ ይኖርብሀል፡፡ አልፎ አልፎ ሌሎች ቁሳቁሶችንም ሳገኝ እንዲሁ እገዛለሁ፤ ለራሴ አንዳንድ ነገሮችን ለመሸመት የስፖርት ቁሳቁሶች ሱቅ ገብቼ አሁን በቡድኔ የምንጠቀምበትን ዘመናዊ የበረዶ መያዣና መታሻ አየሁና ገዛሁ፡፡ ምክንያቱም ወደ ክለቤ ሀዋሳ ሳስብ የሚገለገሉበት እቃ የበረዶዋ ባልዲ መሳይ መያዣ መሆኗ ትዝ አለኝ፤ ሰው ሲመታ እንኳ የሚታሸው ባረጀና ባፈጀ ዘዴ በደረቁና በግግሩ በረዶ ነበር፡፡ አውሮፓ ላይ የምታየው እንደ ጄል ያለውንና የተጎዳውን የሰውነት ክፍል በሙሉ ማዳረስ የሚያስችለው ነው፡፡ ስለዚህም እሱንና ሌሎች ሰውነት ላይ የሚለጣጠፉትን ነገሮች ገዝቼ መጣሁና ለክለቤ አስረከብኩ፡፡

የእውነት ነው የምለው እጅግ በጣም ተራ የሆነ ነገር ነው፤ ግን ደግሞ ትኩረት ሰጥቶት የሚገዛውና የሚጠቀምበት አካል የለም፡፡ ወደ ውጪ ስትወጣ ያሉት ዘመናዊ መሳሪያዎች ያስቀኑሀል፤ ያው ግን በራስህ ሁሉን ማምጣት አትችልም፡፡ ሆኖም በቀላሉ በእጅ ይዘሀቸው ልታመጣ የሚገቡህን ነገሮች ማምጣት አለብህ፡፡ እኔ የሆነ ወቅት ላይ እነዛን የሚቆሙትን ልምምድ ማሰሪያዎች፣ ስቲኮች፣ መዝለያዎች፣ ሬሲስታንስ ባንዶች፣ ላደሮችና ሌሎችም ሳመጣ ብዙዎቹ ሰዎች “እንዳው ምን ያደርግልሀል?” ብለውኛል፡፡  ለመሻሻል አቅምህ የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግ አለብህ፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎች ጥቂት ቡድኖች ውስጥ እንደዚህ አይነት ነገሮች እየተለመዱ ሲመጡ ስታይ ደስ ይልሀል፡፡

በአዳማ እያለዉ 4-4-2 ፎርሜሽንን በመምረጥ  በክፍል ውስጥ ሰሌዳ ላይ የአሪጎ ሳኪን 4-4-2 Zonal Play ሀሳብ ለማስረዳት እሞክር ነበር፡፡ ቀድሞ በብዛት የተለመደው 3-5-2 በመሆኑ በሜዳ ላይም 4-4-2ን እንዴት ለመተግበር  እንደምፈልግም ለማሳየትም እጥር ነበር፡፡ ከዚያ በብዙ ቡድኖች 4-4-2 እየተለመደ መጣ፤ እኔም በደደቢት 4-4-2 መጠቀሜን ቀጠልኩ፡፡ ቡና ስገባ ደግሞ ውበት ላለው እግርኳስና በርካታ የመቀባበያ ማዕዘናት የሚያስገኝልኝን 4-3-3 ቅድሚያ ሰጠሁት፡፡ በመቀጠል ደግሞ የነጓርዲዮላን መጻሕፍት ሳነብና በእንቅስቃሴያዊ ፍሰት እና በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ መማረክ ስጀምር ‘እኔስ ለምን አልተገብረውም?’ በማለት ለሱ ደግሞ መትጋት ጀመርኩ፡፡ የማልደብቀው ነገር ይህን ሁሉ ስታደርግና አዳዲስ ነገሮች ስትሞክር ከፍተኛ ፈተና ያጋጥምሀል፡፡ በክፍል ውስጥ የአሰልጣኝነት ትምህርት (ኮርሶች) ስንወስድ ካልገባኝ ጥያቄዎች እጠይቃለሁ፤ ሲጠየቅም መመለስ ካለብኝ እመልሳለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ሲደብራቸው ታስተውላለህ፤ “ምን አወቅሁ-አወቅሁ ይላል?” የሚሉም አሉ፡፡ “ላፕቶፕ ይዞ! ዝም ብሎ ሲያካብድ እኮ ነው፤ ባዶ አካባጅ!” ይሉሀል፡፡ ‘እኔ ሰው ላይ እስካልደረስኩ ድረስ የፈለጉትን ይበሉ፡፡’ ብዬ አልፋለሁ፡፡

ባህርዳር ላይ ኮርስ የወሰድን ጊዜ ከ34 የኮርስ ተሳታፊዎች አንድ እኔ ብቻ ነበርኩ የPower Point Presentation ያቀረብኩት፤ እሱንም እየፈራው፡፡ አብዛኛዎቹ በወረቀት አቀረቡ፡፡ ጥሩ ነገር አድርገህም ትሸማቀቃለህ፡፡ አንድ ሰው ብቻ ጥሩ አስተያየት ሰጠኝ፤ አብዶ የሚባል በጣም ጥሩ ሰው ነው፤ ‘በኮምፒውተር ባላቀርብ ይሻለኝ ነበር እንዴ?’ ብዬ ጠየቅሁት፡፡  “ምን ቸገረሽ አንቺ! ሌላው ቢችል እኮ ያቀርብ ነበር፤ እኔ በቻልኩ! አሳይሽ ነበር!” አለኝ፡፡ አመሰገንኩት፡፡ ከአንድ አመት በኋላ በወጣቶች አካዳሚ የA-Licence ኮርስ ሲሰጥ ከአስራ አምስት ሰው በላይ የPower Point Presentation አቀረበ፡፡ ስለዚህ በእንደዚህ አይነት መንገድ ውስጥ ብዙ የሚሞግት ነገር ይገጥምሀል፡፡ ተጫዋቾች ራሳቸው ክፍል ውስጥ በምታስተምራቸው ነገር “ምን ባክህ ለውጥ ለማይኖረው!” ይሉሀል፡፡ በሒደት ግን ሁሉም ግንዛቤው እየጨመረ ሲመጣ ያም ጊዜ እያለፈ፤ ነገሮች እየቀለሉ የተሻለ ነገር እየታየ ነው፡፡ ከተለመደው አሰራር እየወጣህ ወደ ዘመነው አካሄድ ስታመራ እየተከበርክ ትሄዳለህ፡፡ ሌላው አለመታወቅህ በራሱ ተጽእኖ አለው፡፡ እኔ በሰፈር ከዚያም በክለብ ደረጃ ከመጫወት የዘለለ እውቅና አልነበረኝም፡፡ በብሔራዊ ቡድን ሳትጫወትና በሚዲያ የሚታወቅ ነባር ስም ሳትይዝ መስራትም በመጀመሪያ ያስቸግራል፡፡ ዝነኛ ባለመሆንህ አንተን የማበረታታት ነገር አታይም፡፡ አሁን ያለው ነገር ግን ደስ የሚል ነው፡፡ ሰዎችም እየመጡ የምክርም የመጸሀፍም ነገር ሲጠይቁህ የበኩልህን ታደርጋለህ፡፡

ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ለማምጣት የሚለፉትም፣ በመካከለኛ ደረጃ የሚጥሩትም ሌሎች ብዙም የማይደክሙትም ያላቸው የውጤት ልዩነት እምብዛም መሆኑና የተቀባይነት ደረጃቸው ተመሳሳይነት ማሳየቱ የአሰልጣኞችን የመትጋት ፍላጎት ቀንሶታል ብለን ማሰብ እንችላለን?

እኔ ማውራት የምችለው ስለራሴ ብቻ ነው፤ ሌሎቹ ጋር ያለውን ነገር መናገር አልችልም፡፡ የማስበውና የሚሰማኝ ሌሎቹ እንደሚሰሩና በራሳቸው መንገድ እንደሚጓዙ በመሆኑ በምን ያህል ፍጥነት እየሄዱ እንደሆነ የሚያውቁት እነሱ ናቸው፡፡ እኔ በራሴ እንደምጥረው ሌሎች አሰልጣኞችም በራሳቸው እንዲሁ ይጥራሉ፡፡ አሰልጣኞች የሚያሰለጥኑትን ቡድን እንዲያሳድጉ ክለቦችም ለባለሙያዎቹ መሻሻል ግብዓት የሚሆኑና ሊሟሉ የሚገባቸውን ነገሮች ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ከነዛም ውስጥ የተጫዋቾች ደረጃ አንዱና ወሳኙ ነው፤ የትኛውንም ተጫዋች አቅም ስላለው ብቻ አምጥተኸው ብታስቀምጠው የሚሰራበትን ነገር ካልሰጠኸው ምንም ሊያደርግልህ አይችልም፡፡ አሰልጣኞች በምንሰራባቸው ቦታዎች በየመጫወቻ ስፍራው የተሻለ ሊያበረክቱ የሚችሉ ተጫዋቾችን ማግኘት በምንችል ሰዓት የበለጠ እንሰራለን፡፡ አሁንም አሰልጣኞች ያላቸውን አቅም እያሟጠጡ ባይጠቀሙ ምናልባትም ኳሱ ከዚህ በወረደ ደረጃ ሊገኝ በቻለ ነበር፡፡ በጣም ትንሽ የሚባል ነገር ውጤት እንድታጣ ሊያደርግህ ይችላል፡፡ እኔ በአሰልጣኝነት ዙሪያ ለውጥ እንዳለ ይሰማኛል፡፡ በበቀደሙ ጨዋታ እንኳን (በአዳማው ጨዋታ) ወደ አምስት ከወጣት ቡድኑ ያደጉ ልጆች ተጠቅሜያለው፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች ስታይ ለውጦች አሉ ብለህ እንድታስብ ያደርገሀል፡፡

ከምላሾችህ እንደተረዳነው የእግርኳስ ትልቁ ምስል መረሳቱ የሚያሳስብህ ይመስለናል፡፡ የአስተዳደር ችግሮች እና በሚዲያዎች በኩል የሚሰጠው ከሜዳው ላይ ይልቅ ከሜዳ ውጪ ባሉ ነገሮች ትኩረት የመስጠት ጉዳይ ምን ያህል አሳሳቢ ሆኖብሀል?

በእርግጥ ሜዳ ላይ ላለው ቴክኒካዊ ነገር  የአስተዳደሩ ስራ ትልቅ መሰረት ይጥላል፤ ብዙ ትኩረት ተሰጥቶ እሱ ላይ መነጋገሩም አንድ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም እግርኳሱን የሚመራው አስተዳደሩ ነውና፡፡ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ከዚያ በኋላ የሚመጡ ናቸው፡፡ ከላይ የሚታየው ነገር እቅዱ፣ ሜዳው፣ ጨዋታው… ሁሉም አመራሮች በሚያስተዳድሩት እግርኳስ ውስጥ የሚያልፍ ነው፡፡ ወደ ክለቦች ግን ስንመጣ የተቋቋሙበት አላማና የሚያራምዱት ነገር ትንሽ አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት አብዛኞቹን ጨዋታዎች ብትመለከት ላለመሸነፍ የሚደረጉ መሆናቸውን በቀላሉ ትረዳለህ፡፡ ላለመሸነፍ እንደ አንድ እቅድ የሚቆጠረው ነገር የዳኞችን ውሳኔ በጸጋ ባለመቀበል ጫና ውስጥ መክተት፣ በጨዋታ ጊዜ ዳኞችን መክበብ፣ ሰዓት ማባከን፣ አጥቅቶ ለመጫወት ፍቃደኛ አለመሆንና ሌሎችም አሰልቺ የሆኑ ነገሮችን እንመለከታለን፡፡ ይህኛው የእግርኳስ መንገድ ለእኔ ያሳስበኛል፡፡ ነገኮ ለብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችን የምትመርጠው ከዚሁ ሊግ ላይ ነው፡፡ በዚህ ስርዓት ታልፎ ሌሎች ቡድኖችን የማሸነፍ የስነልቦና አቅም ያላቸውን ልጆች ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ አንዳንድ ጨዋታዎች ላይ አግባብ ባይሆንም በተለያዩ ምክንያቶች እነዚህን ነገሮች (ሰዓት የማባከን ጉዳይ) ብታደርግ ምንም ላይሆን ይችላል፡፡ ከአቅምህ በላይ የሆነ ተጋጣሚ ሲያገኝህ እና የያዝከውን ወሳኝ ነጥብ አስጠብቀህ ለመውጣት ስታቅድ ልትጠቀመው ትችላለህ፡፡ በዋነኛ የእቅድ ደረጃ በዚህ ስልት የሚታወቁ ቡድኖችን ስታይ ያሳዝናል፡፡ ለእግርኳሱና ለተመልካች ሲባል ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ ለትልቁ ምስል ከዚህ መንገድ የራቁ ብዙ ቡድኖችን መፍጠር አለብን፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ አሰልጣኞች የምትማማሩበት፣ የምትወያዩበትና እግርኳሱን ለማሻሻል የምትመካከሩበት ዘላቂ የጋራ መድረክ ያልተፈጠረው ለምን ይመስልሀል?

የአሰልጣኞች ማህበር እንዳለ እሰማለሁ፤ ሁለት ማህበሮች ያሉም ይመስለኛል፡፡ የአዲስ አባባ እግርኳስ አሰልጣኞች ማህበርና የኢትዮጵያ እግርኳስ አሰልጣኞች ማህበር ናቸው፡፡ አዲስ አበባ በነበርኩበት ወቅት ላይም ተሳትፎ አደርግ ነበር፡፡ አልፎአልፎ ውይይቶች ይደረጉ እንደነበር አውቃለሁ፤ ምክክሮች በምን ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩሩ ጠለቅ ያለ መረጃ ባይኖረኝም አሁንም እንደሚደረጉ እሰማለሁ፡፡ እንደተባለው ግን ቢያንስ እንኳ በተወሰኑ ጊዜያት እንደዚህ አይነት መድረኮች ቢኖሩ፣ ማህበሩ የራሱ ድህረ-ገጽ ኖሮት የተለያዩ ትምህርታዊ መረጃዎችን ለባለሙያዎችም ይሁን ለሌሎች ሰዎች የሚተላለፉባቸው አጋጣሚዎች ቢፈጠሩ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በየትኛዉም አለም ያሉ ማህበሮች የራሳቸው ድህረ-ገጽ ኖሯቸው አባል ለሆኑት ግለሰቦች ጽሁፎችን ይልካሉ፤ሴሚናሮችን ያዘጋጃሉ፤ ይማማራሉ፤… እኛም ጋር ይሄ ነገር ከባድ ይሆናል ብዬ አላስብም፤ መረጃው ስለሌለኝ ምንአልባት እየሰሩ ከሆነ ግን አላውቅም፡፡

ከ1989 በኋላ በርካታ ትልልቅ አሰልጣኞች ያላገኙትን የዋንጫ አሸናፊነት በኢትዮጵያ ቡና አሳክተሀል፡፡ ወደ አሰልጣኝነት በመጣህ አጭር ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ በርካታ ደጋፊ ባለው ክለብ፣ ጠንካራ በነበረው የውድድር ዘመን ከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆነህ የሊግ ድል የተቀዳጀህበት ምስጢር ምንድን ነበር?

በግሌ የራሴ የምለው የተለየ ድርሻ አልነበረኝም፤ በእርግጥ ሁሉም ነገር ውስጥ ተሳትፎ አደርግ ነበር፡፡ በእኛ አገር እግርኳስ አሰልጣኝ ስትሆን ስራህ አሰልጣኝነት ብቻ ላይሆን ይችላል፤ በብዙ ነገሮች ውስጥ ትገባለህ፤ ራስህን በአያሌ ሁኔታዎች ውስጥ ታገኛለህ፤ በብዙ ነገሮች ውስጥ ድርሻ ይኖርሀል፡፡ በምግብ ጉዳይ፣በሰርቪስና ሌሎችም… ስራዬ ሜዳ ላይ ማሰልጠን ብቻ ነበረ ብዬ ልል አልችልም፤ ቡድኑ ውጤት እንዲያመጣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች መስተካከል ነበረባቸው፡፡ ቤትህ ስለሆነ ነገሮች ሲበላሹ ወይም ሲጎድሉብህ ትገባና የሚስተካከለውን ታስተካክላለህ፡፡እነዚህን ሁሉ ስራዎቹ ለመስራት የሚያስፈልጉ በርካታ ሰዎች መኖር ነበረባቸው፡፡ የአሰልጣኞች አባላት ቁጥር ያንን የሚያሟላ ስላልሆነ በጥቂት ሰዎች ትሰራለህ፡፡ የአሰልጣኞች ስታፍ ውስጥ የነበርነው እኔ፣ካሊድና ፈቱሼ ነን፡፡ ሌሎች ደግሞ ብዙ ቅርብም ባይሆኑ ከጀርባ እነ ጋሽ ስዩም አባተና በያን ፤ አስተዳደር ላይ ደግሞ እነ መቶ አለቃ ፈቃደ፣አቶ ይስማሸዋና አቶ ጸጋዬ ነበሩ፡፡ በብዙ ነገሮች ውስጥ ድርሻ ይኖርሀል፡፡ በምግብ ጉዳይ፣ በሰርቪስና ሌሎችም… እንዳላችሁት ከእኔ ቀድመው ቡድኑን ያሰለጠኑት ሰዎች እጅግ ጥሩ ነገር በመስራት ነው ከክለቡ ጋር ያሳለፉት፤ እነሱ ላይ ተጋርጠው የነበሩት ተግዳሮቶች እኔም ላይ ደርሰዋል፡፡ እንግዲህ ምናልባት ለየት የሚያደርገው ነገር የሚረዳህና የሚገነዘብህ ሰው ስታገኝ ስራህን ያቀልልሀል፡፡ በደጋፊው ማህበር አካባቢ ይሰሩ የነበሩት ልጆች በጣም ጠንካሮችና ቡድኑን የዕለት ተዕለት ስራቸው አድርገው የሚከታተሉ መሆናቸው እጅግ በጣም አግዞናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ውጤት ታጣለህ፤ ትሸነፋለህ፤ ደጋፊህ ቅር ሲሰኝና ሲቆጣ የማብረድና የማረጋጋት ስራ ይሰራሉ፡፡ ከክለብ አመራሮችም የማይሆን ነገር ሲገጥምህ እዛም ይሄዱና እንደ ገላጋይ ሆነው የተፈጠረውን አለመግባባት ይፈታሉ፡፡ ስለእውነት ነው የምለው የእነሱ በቅርብ መሆን እጅጉን ጠቅሞናል፡፡ ግማሽ አመት ላይ የአንደኛ ዙር መጠናቀቂያ አካባቢ ጥሩጥሩ ሰዎች  የነበሩበት ( ኤልያስ፣ ወርቅሸትና ሌሎችም) የክለቡ ቦርድም በቡድኑ ላይ እምነት እያሳደሩ፤ በጊዜ ሒደት እንደሚሻሻል እየተረዱና ማበረታቻ እየሰጡ ድጋፋቸውን አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም የተጫዋቾቹ ጥረት፣ የደጋፊው አስደናቂ ድጋፍና እድልም ታክሎበት ውጤታማ ልንሆን ችለናል፡፡

ቡናን ባለድል ካደረግክበት 2003 በኋላ በቀጣዩ የ2004 በክለቡ የነበረህ ውጤት በጣሙን የወረደ ነበር፡፡ በቀደመው አመት የጠቀስካቸው ድጋፎች ስላልነበሩ? ወይስ ሌላ ምን ተከስቶ ነው?

በትክክል! ምንም የተለየ ምክንያት አልጠቅስልህም፤ ጥያቄው ላይ ያለውን መልስ ነው የምመልሰው፡፡ አሰልጣኙ ራሴው ነበርኩ፡፡የተፈጠረው ነገር ዋንጫ መውሰዳችንን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ትኩረታቸው ኢትዮጵያ ቡና ላይ ሆነ፡፡ እኛ ደግሞ ከነበረው ቡድን የተሻለ ለማድረግ በምንንቀሳቀስበት ጊዜ እንደ አንድ ሆነን መንቀሳቀስ አልቻልንም፤ ክፍፍሎች ተፈጠሩ፡፡በመሀከል ግለሰቦችንና ተጫዋቾችን የሚደግፉ አካላት ይነሱና የራሳቸውን አንድ ቡድን ይፈጥራሉ፤ ተጫዋቾች ደግሞ በራሳቸው ሌላ ነገር ያመጣሉ፤ ክለቡ የሚፈልገው ሌላ ነገር ነው፡፡ በነዚህ ምክንያቶች አንድ ቡድን መሆን አልተቻለንም፡፡ በግልጽ የማስቀምጠው ነገር ይህንን ነው፡፡ ለምሳሌ ከእድሉ ደረጄ ጋር ከፍተኛ አለመስማማት ውስጥ ገባን፤ እኔ “ለአንድ አመት ነው መፈረም ያለበት፡፡” አልኩኝ፤ እሱ ደግሞ “ለሁለት አመት ነው መፈረም ያለብኝ፡፡” አለ፡፡ በግልም ሆነ እንደ ቡና ተጫዋችነቱ  በርካታ ደጋፊዎች ነበሩት፡፡ “ለሁለት አመት መፈረም አለበት፡፡” የሚሉ ወገኖችም ተነሱ፡፡ ‘ተጫዋቾቹ ቡድኑን በሚገባ አገልግሏል፤ ሆኖም ግን እንደ አሰልጣኝና ተጫዋች መተያየት ካልቻልን አብረን መቀጠል ይከብዳል፡፡ ከሚመለከተው ነገር ውጪ ሲገባ ላስቆመው ሞክሬያለው፤ ትልቅም ስለሆነ ከአንድ አመት በላይ መፈረም የለበትም፡፡’ የሚል አቋም ያዝኩና በመጨረሻም መቀጠል እንደሌለበት ውሳኔ አሳለፍኩ፡፡ ልዩነታችን ወደ መጥፎ አለመግባባት ሲደርስ አስቆምኩት፤ የሱን ማቆም ያልደገፉ ሰዎች ነበሩ፡፡  እንደገና ደግሞ እሱን ይተካልናል ብለን ያመጣነው ተጫዋች ደግሞ እንደ እድሉ ጥሩ መጫወት አልቻለም፡፡ ተጫዋቹ የአቅም ችግር ኖሮበት ሳይሆን ልጁ በተወሰኑ ሰዎች ተቀባይነት ባለማግኘቱ ጫናውም ነፃ አላደረገውም፤ ይህም ነገሩን ይበልጥ አባባሰው፡፡ የምንያህል ጉዳይም ተመሳሳይ ነበር፤ የተሻለ ብር ስላገኘ በራሱ ፈቃድ ነው ደደቢት የገባው፡፡ እኔ ዛሬ ነው ይህን የምናገረው፡፡ እሱ “ቡናዎች ስላላናገሩኝ ነው፡፡” ነው ያለው፡፡ እኔም፣ አቶ መንግስቱም፣ አቶ ጸጋዬም ቁጭ ብለን አናግረነው እሱ ከፈለገው ገንዘብ አንድ ብር ቅናሽ ቢኖረው እንደማይጫወት ነበር የገለጸልን፡፡ ምንያህል የጠየቀውን ገንዘብ ደግሞ በወቅቱ ኢትዮጵያ ቡና ሊከፍል የሚችለው አልነበረም፡፡ ሌላ ቦታ የተሻለ ነገር አግኘ፤ በተሻለ ብርና ለጊዜው ሪከርድ በነበረ ገንዘብ ደደቢት ገባ፡፡ የእነሱ መውጣት፣የሊጉ ውድድር ሲጀምር ነጥቦችን ከመጣላችን ጋር ተያይዞ እንደ ቡድን አንድ መሆን እንዳንችል አደረገን፡፡ አንድ ካልሆንክ ደግሞ ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ እግርኳስ የቡድን ስራ ነው፤አንድ ቦታ ላይ መፈረካከስ ከተጀመረ አከተመ ማለት ነው፡፡ መርከብ በለው፤ የሆነች ቦታ ላይ ትንሽ ሽንቁር ካለች በዛች ቀዳዳ የሚገባው ውሀ ቀስበቀስ መርከቡን ማስጠም ይጀምራል፡፡ የሆነው ነገር እንግዲህ ይሄ ነው፡፡

የአሰልጣኝነት ህይወት ለቤተሰብ አመቺ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ቤተሰቦችህ በስራህ ዙሪያ ምን አይነት አስተያየት ይሰጡሀል?

አመቺማ አይደለም፤ ካንተው ጋር አብረውህ ይጨናነቃሉ፡፡ አንዳንዴ እኔ ውጤት እንዲሰሙም አልፈልግም፡፡ ነገርግን እነሱ ቀድመው በስልክም ይሁን ከሰው ይጠይቁና ይሰማሉ፡፡ አገርና ከተማ ስትቀይርም ልጆችህ ትምህርት ቤት ይለቃሉ፤ በየጊዜው አዳዲስ የህይወት መንገድ እንዲላመዱ ይገደዳሉ፡፡ በጣም ያስቸግራል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ ስድብ ሲጨመርበት ኑሮን ከባድ ያደርገዋል፡፡ በሙያህ ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን ጓደኞችህንና ወዳጆችህንም ታስጨንቃለህ፡፡

በፊት ያልነበረህና ከሱዳን የእግርኳስ አሰልጣኝነት ልምድህ ያገኘኸው ምን የተለየ ነገር አለ?

ከቤተሰብ መራቅህ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢኖረውም ለስራህ ግን ሰፊ ጊዜ ታገኛለህ፤ ጊዜ ደግሞ ብዙ ነገሮችን የማየት እድል ይሰጥሀል፤ ብዙ ነገሮች ቅርብ ይሆኑልሀል፡፡

እኛ አገር በብዛት ከስፖርት ተመልካቹም ይሁን ባለሙያው ስለ ባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ፣ ሊቨርፑል፣ አርሰናል፣ ማንችስተር፣ ቼልሲ እና ሌሎችም ነው የምትሰማው፡፡ በእርግጥ እዛም ስለነዚህ ቡድኖች ይወራል፤ የስፔን፣ ጣልያንና እንግሊዝ ሊጎች ይታያሉ፤ የሚገርመው ከዛ ባልተናነሰ የሳውዲ አረቢያ ሊግ ይታያል፡፡ የአረብ አገሮቹ ሊጎች በደንብ ትኩረት ይደረግባቸዋል፡፡ የሱዳን ጨዋታዎችም በሌሎች አረብ አገር ቻናሎች ይታያሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች አንተ በአለም አቀፍ ደረጃ እንድትታይ ስለሚያደርጉ ራስን በደንብ ለማዘጋጀት ያነሳሱሀል፤ በሌሎች እይታ ውስጥ የመግባት ሰፊ እድልም ይሰጡሀል፡፡ እነሱ ወደ ውጪ ሀገር ወጥተው ነው የሚዘጋጁት፡፡ በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናትና ለሁለት ወር የሚሆኑ ጊዜያት ቡድኔ በግብጽ የዝግጅት ቆይታ አድርጓል፡፡ ሌሎች ደግሞ ወደ ኳታር ሔደው ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ ልክ እኛ ቡድኖቻችንን ይዘን ወደ ሀዋሳ፣ አዳማ፣ ደብረዘይት… ሄደን እንደምንዘጋጀው ማለት ነው፡፡

በእንደዚህ አይነት የዝግጅት ወቅቶች ብዙ የወዳጅነት ጨዋታዎችን የማድረግ አጋጣሚዎች ይፈጠርልሀል፡፡ እኛም ከሊቢያና ከሌሎች አገሮች ከመጡ ቡድኖች ጋር ስድስት ሰባት የሚደርሱ ጨዋታዎች አድርገናል፡፡ ሌሎች የሚሰሩትን ስራ በጨዋታና በልምምድ ወቅት የማየት እድል ታገኛለህ፡፡ ስትቀራረብ የምታገኛቸውና ብዙ የምትማርባቸው ሰዎች ይገጥሙሀል፤ስለዚህ ወጥተህ መስራት ብዙ ነገሮችን ይጨምርልሀል፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በተለይ ከአሰልጣኞች እይታ አንፃር በዘርፉ እንዲኖር አጥብቀህ የምትፈልገው ነገር ምንድን ነው?

ጠቅልሎ ለመመለስ ከበድ የሚል ይመስለኛል፡፡

ለአሰልጣኞች በስራቸው አመቺ ከባቢያዊ ሁኔታን ለመፍጠር…

ስልጠናው በቁጥር አነስ ባሉ ባለሙያዎች እየተሰራ ስለሚገኝ እዚህ አገር የአሰልጣኝነት ስራ ከባድ ነው፡፡ ሐላፊነቱ እጅግ በጣም ሰፊ ሆኖ የስራ ጫናው ደግሞ በአንድና በሁለት ሰው ላይ ያርፋል፡፡ አሰልጣኝ ሆነህ ስትሰራ ብዙ ሊደግፉህ የሚችሉ ሰዎች አብረውህ ሊኖሩ ይገባል፡፡ የአሰልጣኞች አባላት ቁጥር መጨመርና ይዘቱም መስፋት መቻል አለበት፡፡ የስነልቦና ባለሙያ፣ የህግ አስተማሪ፣ የስነ ምግብ ጉዳይ አማካሪ፣ የቴክኒክ መምህር ሆነህ አትችልም፡፡ ስለዚህ የሚረዱህ ብዙ ሰዎች አብረውህ ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ ሌላው ተጫዋቾች በአንድ ክለብ ለረጅም ጊዜ የሚፈርሙበት ስርዓት ቢኖርና ጎን ለጎን ለአሰልጣኞችም በቂ ጊዜ ተሰጥቷቸው በተረጋጋ መንፈስ ስራቸውን የሚሰሩበት ሁኔታ ቢመቻችላቸው ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡

በተጨማሪም የእግርኳስ ከባቢያችን ከሌሎች አገራት ገንጠል ያለ በመሆኑ በቀላሉ ወደ ውጪ ወጥተን የምንማርባቸው መንገዶች ቢፈጠሩ አሰልጣኞች የበለጠ እውቀታቸው ይጎለብታል፤ የልምዳቸው ደረጃ ከፍ ይላል፡፡ ብዙውን ጊዜ በፌዴሬሽኑ በኩል የሚመጡ ኮርሶችን ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ምክንያቶች የሚፈጠሩ እድሎች አሉ ብዬ አላስብም፡፡ በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ አማካኝነት ይህንን ክፍቶች የሚሸፍኑ ስራዎች ቢሰሩና ቶሎቶሎ ትምህርት የሚገኝበት አሰራር ቢፈጠር የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም የተሻሉ ተማሪዎችን የምታገኘው ጥሩ ጥሩ አስተማሪዎች ያሉበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ የበቁ ተጫዋቾች እንዲኖሩን እንዲሁ መጀመሪያ ጎበዝ አሰልጣኞች መፈጠር አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ አሰልጣኞች በግል ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡

በፕሪምየር ሊጉ ረጅም አመት የቆዩ ተጫዋቾች አሁንም ሰፊ ቦታ እየተሰጣቸው ይገኛሉ፡፡ የሊግ ውድድሮቻችን በርካታ ወጣቶች የሚታዩበት እንዲሆን ምን መደረግ አለበት ብለህ ታስባለህ?

ማን ምን እየሰራ እንደሆነ የሚጠቁምና ጠለቅ ያለ ግንዛቤ የሚሰጥ የሊጉ ቁጥራዊ መረጃ የለኝም፡፡ በየትኛውም አለም ቢሆን እግርኳስ ከእድሜ ጋር የሚሄድና ገደብ የተበጀለት ስፖርት በመሆኑ ማንም ሰው እንድትጫወት ቢፈልግና ቢፈቅድልህ ወሰኑን ካለፍክ መጫወት አትችልም፡፡ ስለዚህ ወጣቶችን መተካት ግድ መሆኑ የሁልጊዜም እውነታ ነው፡፡ ጥያቄውን በማሰለጥነው ክለቤ ስመልስልህ በአዋሳ U20፣ U17፣ U15 እና U13 የሚሰሩ ልጆች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ልጆች ለዋናው ቡድን እንደ ግብአት በመሆናቸው ከነሱ ውስጥ ያሳደግናቸው ወደ 13 የሚጠጉ ልጆች አሉ፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ዋናው ሊግ ላይ በምንፈልገው መጠን ወጣት ተጫዋቾችን ባናይ እንኳን ካደጉባቸው ክለቦች ወደ ሌላ እድልን ወደሚሰጧቸው ቡድኖች እንዲሁም ሊጎች እየሄዱ ሲጫወቱ እንመለከታለን፡፡ ይህ ያልታየ ነገር ይመስለኛል፡፡ ሁላችንም ወጣቶች እያደጉ እንዳልሆነ ነው የምናስበው፤ግን ብዙ ወጣቶች እያደጉና እየተጫወቱ ነው፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ካሉት 16 ቡድኖች ስንት ልጆች አድገዋል? በመቁጠር መድረስ ይቻላል፡፡ በታችኞቹ ሊጎች ያሉ ክለቦች ተጫዋቾችን ከየት ነው የሚያመጡት? ግልጽ እኮ ነው፤ምንጮቻቸው እነዚህ ከታች የሚያድጉት ወጣቶች ናቸው፡፡ ‘በአንድ ክለብ ውስጥ በዋናው ቡድን ወጣቶች አልተካተቱም፡፡’ ማለት ‘ወጣቶች እያደጉና እድል እየተሰጣቸው አይደለም’ ማለት ሊሆን አይችልም፤ ኳስ አቁመዋል ማለትም አይደለም፡፡ ሌላ ቦታ ሄደው ከታችኛው ሊግ ጀምረው ራሳቸውን እያበቁ የሚያድጉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ በየትኛውም አገር በአንድ ጊዜ ወጣቶችን ወደ ዋናው ቡድንና ላይኛው ሊግ የሚያሳድግበት አካሄድ ያለ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ግን ከእድሜ ጋር በተገናኘ በትልቁ ሊግ መጫወት የማያስችላቸው ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካታ ተጫዋቾች ስለመኖራቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

ስለዚህ በክለቦች ያሉ የወጣት ቡድን እርከኖች ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾችን በሌላ መንገድና ክለብ እንዲሁም የሊግ ደረጃ የምናይበት እውነታ ስላለ ይህን እንረዳ የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ በውጭ እግርኳስ በአንድ ምሳሌ ባስረዳ የማንችስተር ዩናይትዶቹ ፖውል ፖግባና ዤራርድ ፔኬ ልምድ ይህን ሀሳብ የሚያጠናክር ይመስለኛል፡፡ ሌላ ምሳሌ ልጨምር፦ በ2004 ዓ.ም. ከፕሮጀክት መልምለን ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያስገባነው ልጅ፣ከB ያሳደግነው አብዱረህማን እና ሌሎችም ነበሩ፡፡ የፋሲሉ አብዱረህማን እንዲያውም ብሄራዊ ቡድን ሁሉ እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ‘ቡና ውስጥ አላደገም፡፡’ ማለት ልጁ አላደገም እንድንል አላደረገንም፡፡ የወልዋሎው ከድርም እንዲሁ በቡና አድጎ በሌላ ክለብ እየተጫወተ ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቶች እድል አይሰጣቸውም በሚለው ሀሳብ ለመስማማት እቸገራለሁ፡፡

አሰራሩ የወጣቶቹን ማደግየ ሒደታቸውን አያጓትተውም? በተለያዩ  መንገዶች ዞረው መምጣታቸው ልምድ ቢያስገኝላቸውም በእግርኳስ የቆይታ እድሜያቸው ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖስ?
ተጫዋቾቹ በሚጫወቱበት ቦታ በክለቡ የተሻለ የሚያበረክት ካለ ምን ታደርጋለህ? ከሁለት አንዱን እኮ ነው መምረጥ ያለብህ፤ የቦታውን መደበኛና አንጋፋ አልያም ወጣቱን፡፡ እዚህ ጋር ምርጫው የወጣቱም ይሆናል፤ ‘ከአንጋፋው ጋር ለረጅም ጊዜ ቆይቼ ልምድ እየተጋራሁ መቆየት ወይም እድል ወደማገኝበት ቦታ ማምራት’ የሚል፡፡ አሰልጣኙም እንዲሁ በነባሩና በወጣቱ የመጠቀም ውሳኔ በእጁ ነው፤ የብቃትን ልክ በመመልከት የራስህን ውሳኔ ታሳልፋለህ፡፡ በሀዋሳ መሳይ ጳውሎስን እንይ፡፡ ልጁ ከታች ነው ያደገው፤ እድል ተሰጠውና ሲታይ የሚያበረክተው ነገር ከትልልቆቹ ጋር በንጽጽር ያልተናነሰ ሆኖ ተገኘ፤ ልምድና ሌሎች ብዙ የሚቀሩት ነገሮች ቢኖሩም ያሳየን ግን እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ነበር፡፡ ይኸው ባለፉት ሁለት አመታት ቋሚ ተጫዋች ሆኗል፡፡ ከታች መጥቶ እድል ለማግኘት ዋናውን ቡድን ሰብሮ የመግባት አቅም ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን የግድ በወጣት ለመተካት ብለህ ቡድንህ ውስጥ ያለውን ልምድና የተሻለ ጎን ወደ ኋላ ገፍተህ በወጣቶች ለመወዳደር ትቸገራለህ፡፡ ስለዚህ ይሄ የምርጫ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በልምድ ጉዳይ ያለን ግምት እጅጉን ይገናል፡፡በዚህም ምክንያት ልምድ ስላለው ብቻ ሰፊ እድል የማግኘትና ስህተቶችን ቢፈጽም እንኳ በብዛት ቦታ የመስጠቱ ነገር ወጣቶችን የማያበረታታ ሒደት ይመስላል፡፡ ወጣቶች እድል አግኝተው የሚያሳዩት የመጠነኛ ደቂቃዎች ብቃት ብዙም ዋጋ ሲሰጠው አይታይም፤በቀጣይ የሚሰለፈው ያው ባለ ልምዱ ነውና፡፡ ይህ ሁኔታ ብዙ ወጣቶችን እንዳናይ አልፎም አንጋፋዎቹን ደግሞ ይበልጡን እንዳይጥሩ ያደርጋቸዋል የሚል አመለካከት አለ፡፡

ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ብቃታቸው ወርዶም የተፈላጊነት መጠናቸው አለመቀነሱና በሌሎች ቡድኖች መፈለጋቸው በዝውውር ገበያው ላይ በደንብ የሚስተዋል ጉዳይ ሆኗል፡፡ የዋንጫ ስኬት ያስመዘገበ ተጫዋችም ይሁን ክለቦች በመጥፎ አቋም ሲወርዱ ጥሩ ባልነበረ አቋም አብሮ የነበረ ተጫዋችም በተለይ ወደ ሊጉ በሚመጡ አዳዲስ ቡድኖች የመፈለግ እድላቸው ግልጽ ነው፡፡ ተቀራራቢ ባልሆነ ስኬትና የብቃት ደረጃ ተመሳሳይ የሆነው ተፈላጊነት ተጫዋቾችን እንዳይተጉ አያደርግም?

ጥያቄውን ተረድቼዋለሁ፤ ግን አሁንም ወደ ቀደመው ሀሳቤ ነው የምመለሰው፡፡ በየትኛውም አለም ተጫዋቾች ክለባቸው ሲወርድ በኮንትራት ስር ከሆኑ አብረው ይዘልቃሉ፡፡ ከኮንትራት ነፃ የሆነና በላይኛው ሊግ የመጫወት አቅም ካለው ታች ወርዶ ሊጫወት አይችልም፡፡ ጉዳዩን በጠቅላይ መልክ መወከል የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ሰው ካልሰራ አይለምድም፡፡ እውነታው ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ከአዲሶቹ የተሻለ እድል አላቸው፡፡ ይህንን አሰራር የሚያፋልስ አቅም ያለው ሰው ካለ ለእኔ ይህኛው ሊበልጥብኝ ይችላል፡፡

ለምሳሌ በባንክ ቆይታዬ የነበረኝን ተመክሮ ልጥቀስ፦አንድ ከB ያሳደኩትና አንድ ደግሞ በዋናው ቡድን የሚጫወቱ ተጫዋቾች ነበሩኝ፡፡ ሁለቱን ሳነፃፅር ባለልምዱ በአእምሮአዊ ነገሩና ጨዋታን በማንበብ ብቃቱ የተሻለ ሲሆን አዳጊው ደግሞ በትጋት ይበልጠዋል፡፡ ተጫዋቾችን በየመጫወቻ ቦታቸው በመመደብ ሙሉ ቡድኑን የመገምገም ስራ ስሰራ የሁለቱ ተጫዋቾች የመጨረሻ ውጤት ለየቅል ሆነ፡፡ ወጣቱ ልጅ ባለልምዱን በብዙ እጥፍ አስከነዳው፤እኔ ግን አሁንም የመጫወት እድል የሰጠሁት ለነባሩ ተጫዋች ነበር፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ በምትፈትነውና በተግባር በምታየው  መካከል ሰፊ ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ በዚህ መሠረት ትልቁ ልጅ በተግባርም ያሳየው ብቃት የሚያስደስት ስላልነበር ለታዳጊው ልጅ እድሉን ሰጠሁትና በቡድኑ  ውስጥ ትልቅ ለውጥ ፈጠረ፡፡ ሲኒየሩ ልጅ በሶስት የመገምገሚያ ፈተና ያላስመዘገበውን ውጤት ወጣቱ በአንድ ፈተና አሳካ፡፡ እንደዚህ አይነት ልዩነቶችን እያየህ እድል አለመስጠት አትችልም፡፡ ሁሉም ነገር ግምገማና ፈተና ይፈልጋል፡፡ በሚመዘገበው ውጤትም ሁለቱን ማበረታታትና ማሻሻል ይኖርብሀል፡፡ ተጫዋቾች የመጨረሻ ጥሩ ብቃታቸው ላይ እስከሚደርሱ ድረስ ልታግዛቸውና ልትረዳቸው ይገባሀል፡፡ ሁሌም ከፍ ባለ የብቃት ደረጃ እየተጫወቱ የሚቆዩበት ዘመን እንዲጨምር መጣር አለብህ፡፡ ወጣቶችም ከአንጋፋዎቹ እየተማሩ ማደግ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚያዩት ሒደቱን ሳይሆን የመጨረሻ ውጤቱን ስለሆነ አሰልጣኞችም ራሳቸውን ጫና ውስጥ እንዳይከቱ ሲሉ እንደዚህ ያደርጋሉ፡፡

በእናንተ የአንጋፋነት ዘመንና አሁን ያሉት ወጣት አሰልጣኞች የበለጠ ልምዳቸው ሲጎለብት የወደፊቱ የኢትዮጵያ አሰልጣኞች ዘመን ምን አይነት መልክ ይኖረዋል ብለህ ትገምታለህ? 

ይህንን ለመተንበይ በጣም ቢከብድም አሰልጣኞች ብቻቸውን ምንም ሊፈጥሩ አይችሉም ፤ ወደፋትም ቢሆን ለብቻቸው ተገንጥለው ሌላ ነገር ያመጣሉ ብዬ አላስብም፡፡ ሆኖም የተሻሉ የአሰራር መንገዶች እና እድሎች እንደሚመጡ ይሰማኛል፤የበቁ አሰልጣኞችም ይበዛሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ በሌላ በኩል ከአለም እድገት ጋር ተያይዞ እንደ አገር አሰልጣኞችም በሙያቸው ማደጋቸው ስለማይቀር ብሩህ የሆነ ነገር ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡
እንደዛ እንዲሆን ደግሞ ከጠባቡ ከባቢያችንም በላይ ማየት መጀመር አለብን፡፡ ጊዮርጊስ፣ ቡና፣ አዳማ፣… ከነሱም በላይ ማሰብ ይኖርብናል፡፡ አለምአቀፍ አሰልጣኝ መሆንን መመኘትና ለሱም መትጋት አለብን፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ ሆኜ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አሰለጥናለሁ ብዬ አልልህም፤ ለጊዜው ለዛ የሚሆን አቅም የለኝም፡፡ ሆኖም በአለም ውስጥ ወደ 210 የሚሆኑ የእግርኳስ አገሮች አሉ፤ ስለዚህ አሰልጣኞችቻችን ህልማችን በዛ መንገድ ቢሆን መልካም ነው ብዬ እላለሁ፡፡ እዚሁ የተወሰነ እቅድ ይዘን ብዙም መቀየር አንችልም፤ ሰፋ አድርገን የምናስብ ከሆነ ግን ራሳችንንም በብዙ ነገር ለማሳደግ እንሞክራለን፤ የእይታ አድማሳችንም በደንብ ይሰፋል፤ እድሉ ቢገኝና ብንሄድ ደግሞ የሚጠበቅብን ነገር ብዙ እንደሆነ ስለምንረዳ ራሳችንን እናዘጋጃለን፤ አሁን ነገሮች ይበልጥ ክፍት ሆነዋል፤ ስለዚህ እዚም ሆነ እዛ መልካም ነገር ሊገጥመን ይችላል፡፡

በእርግጥ አንዳንድ ሳንካ የሚሆኑ ነገሮች አሉብን፡፡ ለምሳሌ የሱዳን ገጠመኜን ልንገራችሁ፡፡ ከአንድ የሱዳን ክለብ ጋር የመነጋገር እድል ሰው አገኘልኝ፡፡ የስራ ልምድ ማስረጃዎቼን አዩና “በቃ እኛ ጋር ትሰራለህ፤ከክለቡ ስራ አስኪያጅ ጋር ተነጋግረን እንደውልልሀለን፡፡” አሉኝ፡፡ ከዛም የቦርዱ ዋና ሰው እኔን እንደመረጡ ሲነግሩትና መረጃዬን ሲያቀርቡለት አልተስማማም፡፡ “አይሆንም!” አላቸው፡፡ የሰውየው ምክንያት ያስገርም ነበር፡፡ “እኛ እሱን ብንቀጥር ‘የካርቱም ወጠኒ አሰልጣኝ ማን ነው?’ተብሎ ነው የሚጠየቀው፡፡ክለቡ እሱን ነው የሚያስተዋውቀው፡፡ ትልቅ አሰልጣኝ ብናመጣ ግን ክለባችን በአለምአቀፍ ደረጃ በአሰልጣኙ ምክንያት እውቅና ያገኛል፡፡” አላቸው፡፡ ከዛም የጋና የU20 እና ኋላም የዋናው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረውን ስቴፈን አፒያህን ቀጠሩ፡፡ “አሰልጣኝ ከኢትዮጵያ?” ይህ ጥያቄ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥርብናል፡፡ ከግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያና ሌሎች አገሮች ሲሆን ተቀባይነቱ ይጨምራል፡፡ በብሔራዊ ቡድን ያለን የእግርኳስ ደረጃ ሊገድበን ቢችልም ያን ለመቀየር መታገል ያስፈልጋል፡፡ ትንሽ የአሰልጣኝነት ኮርስ የወሰደ ነገርግን ብራዚላዊ ስለሆነ ብቻ የሚመረጥ አሰልጣኝ አለ፡፡ በአፍሪካ እግርኳሳችን በትልቅ ደረጃ መጠቀስ ሲጀምር የተቀባይነት እክል ከሚሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ይቀንሳል፡፡ ሌላው ቋንቋም አንድ ችግር ይፈጥራል፡፡ በአፍሪካ በአብዛኛው አረብኛና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ወደ ሆኑ አገሮች ሄዶ ለመስራት በነዚህ ጉዳዮችም መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ዋናው ሰፋ አድርጎ ማሰብና ብሩህ መመኘት ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *