ከ50 አመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ፣ አመራርነት እና አማካሪነት የሰሩት አንጋፋው የስፖርት ሰው አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ የኢትዮጵያ እግርኳስን ለረጅም ዘመናት ጠንቅቀው የሚያውቁ ግለሰብ እንደመሆናቸው ዘንድሮ በእግርኳሱ እና በፌዴሬሽኑ ምርጫ ስለሚታየው ትርምስ አስተያየት ለመስጠት ሁነኛው ሰው ናቸው። አቶ ፍቅሩ ለሶከር ኢትዮጵያ በላኩት ፅሁፍ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ታይቶ የማይታወቅ ሁኔታ ውጥንቅጥ ውስጥ ገብቷል ይላሉ። ሙሉውን ጽሁፍ እነሆ !
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን (እ.ኤ.አ.) በ1943 የተመሠረተና (እ.ኤ.አ.) በ1952 በፊፋ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ እንዲህ ተዎርዶ አያውቅም፡፡ የፌድሬሽኑ መሥራች አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በመጀመሪያ ያረቀቀው መተዳደሪያ ደንቦች በፈረንሳይኛ እና አማርኛ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በየግዜው ነፃ የሚወጡት የአፍሪካ ሃገሮች ፌድሬሽኖቻቸውን ለማቋቋም እርዳታ የሚጠይቁት አቶ ይድነቃቸውን ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን መተዳደሪያ ደንቦችን ያረቀቀው በኃላም የኮንፌድሬሽኑ ፕሬዝደነት ሆኖ ያገለገለው አቶ ይድነቃቸው ነው፡፡ በፊፋም ደረጃ ቢሆን ኮንግረሱ ላይ በመከራከርና በማሳመን አንዳንድ አንቀፆች እንዲሻሻሉ አድርገዋል፡፡ ታዲያ እንደዚህ ተከብሮ እና ተመስግኖ የኖረው ፌድሬሽን ነው አሁን የዓለም መሳቂያ ሆኖ ከፊፋ ዋና ፀኃፊ የውርደት ደብዳቤ የደረሰው፡፡ ፌድሬሽኑን ያጨማለቁት ሰዎች ምርጫ እንኳን እንዴት እንደሚካሄድ የማያውቁ እና እንደገና ለመመረጥ እየደገሱ ያሉ ናቸው። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው እነኚህ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ የሚሯሯጡትን ግለሰቦች መርጠው የሚወክሉት ክልሎች ምን ኃላፊነት እንደማይሰማቸው መረዳቱ ነው፡፡ መራጮች ወይም ወካዮቹ ባለስልጣኖች ቢጠረጠሩ ተገቢ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የስፖርት ድርጅቶች መመራት ያለባቸው በክለቦች ተወካዮችና በስፖርት ባለሙያዎች መሆን እንዳለበት ግልፅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው በዘር መሣሪያ በመጠቀም ክልሎች ፈላጭ ቆራጭ የሆኑበት፡፡ እንደሌሎች ሃገሮች ክለቦች ስልጣኑን እስከሚረከቡ ድረስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽንም ሆነ ሌሎች ፌድሬሽኖችና የኦሎምፒክ ኮሚቴው የማንም መቀለጃ ሆኖ መቅረቱ አያጠራጥርም፡፡ ይሄን የእግርኳስ ፌድሬሽን ጭቃ ውስጥ የከተቱና ለውርደት ያበቁት ሰዎች ትንሽ ክብር ቢኖራቸው ኖሮ ለምርጫ መቅረብ አይገባቸውም ነበር፡፡ ዳሩ ግን አይን አውጣ ስለሆኑ እና ጥቅሙን ስለሚያውቁ ለመመረጥ ተሰልፈዋል፡፡ ለሥራ ፈቶችም ጥሩ ግዜ ማሳለፊያ ሆኗል፡፡ በፊፋና ካፍ ገንዘብ ከመንሸራሸር በላይ ኳስ ሜዳም በነፃ የሚያስገባ፣ ጋዜጣ ላይ የመውጣት እና በቴሌቪዥን የመታየት ጥቅምን ያስገኛል። የፊፋ ዋና ፀኃፊ ያስረዳናችሁ እና የመከርናችሁ ጉዳይ ምንም ስላልገባችሁ አንድ ሰው ልከን እንደገና በቀላል ቋንቋ እንዲገለፅላችሁ እናደርጋለን ብላ ስትፅፍ ውርደት ያልገባቸው ሰዎች ምን የሚገባቸው አይመስሉም፡፡ ብስጭቱ እኛ ሃገራችን ተዋረደች ብለን ለምንቆረቆረው ብቻ ነው፡፡
በቴሌግራምና በቴሌክስ በሚሠራበት ዘመን ውርደት የሚባል ነገር ያላጋጠመው የፌድሬሽን ፅህፈት ቤት አሁን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በኮምፒዩተርና በፋክስ በሚገለገልበት ወቅት ፌድሬሽኑ በሠራተኞች ድክመትና ኃላፊነትን መወጣት ባለመቻል አሳዛኝ ድርጊቶች ሊፈፀሙ ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽንን ለማገልገል የሚመረጡት ሰዎች ምንም ዓይነት የስፖርት አመራር እውቀት ስለሌላቸው የስራ ክፍፍል ሲደረግ የሚረከቡትን ሃላፊነት ለመወጣት ይቸገራሉ፡፡ ቀልጣፋ ዋና ፀሃፊ ካለ ግን ብዙውን ጉዳይ ሊያስተካክል ይችላል፡፡ ለምሳሌ የቡድን መሪ ተብሎ የሚደባደብ አለ፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ ሃላፊ ሆኖ ከአሰልጣኙ እሻላለው የሚል በጥባጭ አለ፡፡ ከቡድኖቹ ጋር ሽርሽር ለመሄድ ግን ሁሉም ተሯሩጦ ቪዛ ያወጣል፡፡ ትልቁ ችግር ግን እነኚህ የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባሎች የፌድሬሽኑን፣ የካፍን እና የፊፋን መተዳደሪያ ደንቦች ያለማንበብ ያለመረዳት ነው፡፡ ህጎቹን ቢያውቁ ኖሮ የፌድሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ በመጀመሪያው ግዜ ተካሂዶ አዲስ የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ባሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ በቀደመው ግዜ ፌድሬሽኑ ጠንካራ የህግ ኮሚቴ ነበረው፡፡ አባሎቹ በሙሉ በውጪ ሃገር የተማሩ የእንግሊዘኛም ሆኖ ፈረንሳይኛ ቋንቋ ዕውቀት የነበራቸው ቢሆኑም በሃገራቸው ቋንቋ በአማርኛ አበጥረው በነፃ የሚያገለግሉ ነበሩ፡፡ ከነርሱ መካከል አሁንም በህግ ስራ ተሰማርቶ አዲስ አበባ የሚገኘው ዳክተር ብርሃነ ገብራይ በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበረ በካፍም ሥነ-ምግባር ኮሚቴ ውስጥ አገልግለዋል፡፡ የፌድሬሽኑ ዋና ፀሃፊ በመሆን ሰላሣ ዓመታት ያህል ያገለገለው ካሣ ገብረጊዮርጊስም አዲስ አበባ ይኖራል፡፡ ፌድሬሽኑ ውስጥ በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ውስጥ ያገለገሉ ምንም ቢያረጁ አሁንም አሉ፡፡ ሌላው ችግር የቋንቋ ነው፡፡ እንግሊዘኛ በደንብ የሚገባቸው መፃፍና ማንበብ ብቻ ሳይሆን የመረዳት ችሎታ ከሌላቸው ከካፍ እና ከፊፋ ጋር መፋጠጥ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ችግር የተፈጠረው አንብቦ በአለመረዳት ችግር ነው፡፡
በቴሌግራምና በቴሌክስ በሚሠራበት ዘመን ውርደት የሚባል ነገር ያላጋጠመው የፌድሬሽን ፅህፈት ቤት አሁን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በኮምፒዩተርና በፋክስ በሚገለገልበት ወቅት ፌድሬሽኑ በሠራተኞች ድክመትና ኃላፊነትን መወጣት ባለመቻል አሳዛኝ ድርጊቶች ሊፈፀሙ ችለዋል፡፡
አሁን በማገልገል ላይ ያለው የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባሎች ለምርጫ ቀርበዋል፡፡ አብዛኞቹ ሊመረጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ምንም ዓይነት ለውጥ አይኖርም፡፡ የባሰ ያጨማልቁታል፡፡ አዳዲስ ወይም ከአሁን በፊት ያገለገሉ አዲስ ጥብቆ ለብሰው ለምርጫ ብቅ ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በፊፋ እንድትታገድ ያደረገው ሰው መላውን የኢትዮጵያ ስፖርት ለመምራት ገንዘቡን እየረጨ ጉድ ጉድ ይላል፡፡ እነርሱም ከተመረጡ ለውጥ የለም፡፡ ለውጥ ሊኖር የሚችለው የክለብ መሪዎች መብታቸው ተጠብቆ የመንግስት ካድሬ የሌለበት ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ ከራሳቸው መካከል ወጣት እና የበሰሉ የስራ አስኪያጅ አባሎች ሲመረጡ ነው፡፡ ሃገራችን የተማሩ ግለሰቦች አላጣችም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የፊፋ እና ካፍ መተዳደሪያ ደንቦች በጥሩ አማርኛ ተርጉሞ መጠቀም ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኛው እንኳን በሚጥፈው እና በሚናገረው ህዝብ ፊት እንዳይዋረድ የእግርኳስን ህጎችንና መተዳደሪያ ደንቦችን አጣርቶ ያውቃል፡፡ ለዚህ ነው ጋዜጠኞች ቢተቹ ቢተቹ የሚሰማቸው ስለጠፋ ከህዝብ ጋር ተሰልፈው ለውጥ የሚጠብቁት፡፡
ሌላ የሚያሳዝነው ድርጊት ሃገራችን ስትዋረድ ዝም ብሎ የሚመለከተው የስፖርት ሚኒስቴሩ መስሪያ ቤት ነው፡፡ ፎቶግራፍ አንሺና የቴሌቭዢን ካሜራ ያለበት ትዕይንት ለምሳሌ የዓለም ዋንጫ ጉብኝት ላይ ሁሉም ባለስልጣኖች ተሰብስበው ነበር፡፡ ጥሩ ፤ ግን ለግዜው የገጠመንን ችግር ለማስወገድ አይሰበሰቡም፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ መቼ እንደሚካሄድ ለግዜው አይታወቅም፡፡ ለምርጫም የቀረቡት ቢመረጡም ምንም እንደማይሻሻሉ የታወቀ ስለሆነ እንደውም የባሰውን እንደሚያጨማልቁት እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለእኛ የቀረን ለውጥ እንዲያሳየን ቁልቢ ገብርኤልን መለመን ብቻ ነው፡፡