የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛና ሁለተኛ ዲቪዚዮን የመጀመርያ የውድድር ዘመን አጋማሽ አፈፃፀም ሪፖርት እና ግምገማ በዛሬው እለት ረፋድ ላይ በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ተካሂዷል፡፡
ስብሰባውን የከፈቱት የወቅቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ በንግግራቸው እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት በተሻለ በሁለት ሊጎች የተከፈለ ውድድር በማድረግ እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ቢሆንም የተሻለ ውጤታማ ብንሆንም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ግን አሁንም የሚሰጠው ግምት አናሳ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ የክለብ አሰልጣኞች እና አመራሮች ከክለባዊ አስተሳሰብ ተላቀው ለሀገር መስራት እስከቻልን ድረስ ይበልጥ እግርኳሱን ማሳደግ እንደሚቻል እምነት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በንግግራቸው ማሳረጊያ ላይም እግርኳሱን በይበልጥ ለተመልካች ሳቢ እንዲሆንና በሂደት የተመልካች ቁጥሩን በመጨመር ለክለቦች ከገቢው ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድን ለመፍጠር ይበልጥ ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በመቀጠል የሁለቱን ዲቪዚዮኖች የአንደኛ ዙር አጠቃላይ ሪፖርት የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት አቶ ከበደ ወርቁ አማካኝነት የቀበረበ ሲሆን በአስገራሚ ሁኔታ ግን ቀደም ብሎ ለተሰብሳቢዎች በተበተነው የስብሰባ መርሃግብር ላይ ይቀርባል ተብለው የነበሩት የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ፣ የዲሲፕሊን ኮሜቴ ፣ የፀጥታና ስፖርታዊ ጨዋነት ሪፖርቶች ግን ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
ተሰብሳቢዎች ከሻይ እረፍት ሲመለሱም በቀረበው ሪፖርትና በአጠቃላይ የውድድር ሂደቶቹ ላይ እንደእንከን የተመለከቷቸውን ሀሳቦች አንስተው ከፌዴሬሽኑ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰቶባቸዋል፡፡ በተሰብሳቢዎቹ በዋነኝነት ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል የሴቶች ፕሪምየር ሊግ መርሃግብር ከወንዶቹ ጋር በተጣጣመ መልኩ ቢካሄድ ውድድሩ የሚካሄድበት ሰአት ቢስተካካልና ውድድሮቹ በሚካሄዱበት ወቅት በቂ የሆነ የፀጥታ ሀይል እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች እንዲቀርብ ቢደረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም በዛሬው እለት በቀረበው ሪፖርት ላይ ከሁለተኛ ዲቪዝዮን ወደ አንደኛው ዲቪዝዮን በሚያድጉ ክለቦች ቁጥር በውድድሩ መጀመሪያ ላይ ለክለቦች ከተሰጠው ደንብ ጋር የሚጋጭ መሆኑን የቅድስት ማሪያም ዩኒቨርስቲ ተወካይ ገልፀዋል። በተመሳሳይ የመከላከያው ተወካይ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ ውድድር ቢካሄድ የሚል ሀሳብ ቢያነሱም የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ የጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ በአሁኑ ወቅት በሁለቱም ዲቪዝዮኖች የሚገኙ ቡድኖች በቂ የሆነ የጨዋታ ብዛት ስለሚያገኙ እንዲሁም የጥሎ ማለፉ ውድድር ቢዘጋጅ በውድድሩ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን እንደወንዶቹ ሁሉ በአህጉራዊ ውድድር የመሳተፍ እድልን ስለማገኝ በቀጣይ ካፍ እንደ ወንዶቹ ሁሉ የቻምፒየንስ ሊግ እንዲሁም የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እስኪያዘጋጅ ድረስ ውድድሩ ላይካሄድ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም በአሁኑ ወቅት ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሊቢያ ጋር ጨዋታ ላለባቸው ሉሲዎቹ 3 ያክል ቡድኖች 3 እና ከዛ በላይ ተጫዋቾችን በማስመረጣቸው የአንደኛ ዲቪዝዮን ውድድሩን ለማካሄድ አስቸጋሪ ስለሚሆን በቀጣይ ብሔራዊ ቡድኑ በምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ የሴቶች ዋንጫ መሳተፉን ከግምት በማስገባት ብሔራዊ ቡድኑ የሚሳተፍባቸው ውድድሮች እስኪጠናቀቁ ድረስ ሊራዘም እንደሚችልም ተጠቁሟል። ነገርግን የሁለተኛው ዲቪዝዮን ውድድር ቀደም ሲል ለክለቦች በተገለፀው መሠረት በመጪው ሰኞ ጅማሮውን የሚያደርግ ይሆናል፡፡