በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የተስተካካይ መርሀ ግብሮች መካሄዳቸውን ቀጥለው በባህርዳር ደርቢ ባህርዳር ከተማ አውስኮድን አሸንፎ መሪነቱን ሲያጠናክር ኢትዮጵያ መድን ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል ነቀምት ላይ አስመዝግቧል።
በባህርዳር ደርቢ ባህርዳር ከተማ አማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትን (አውስኮድ) በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ገጥሞ 2ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ከወትሮው በተለየ ጨዋታው በስራ ቀን እንደመደረጉ በአነስተኛ የተመልካች ቁጥር ታጅቦ የተደረገ ሲሆን በተለምዶ ካታንጋ እየተባለ ከሚጠራው የደጋፊዎች የመቀመጫ ስፍራ ውጪ በክቡር ትሪቡን፣ በቀኝ እና ግራ ጥላ ፎቅ አካባቢ በነበሩ የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ሞቅ ያለ የድጋፍ አሰጣጥ ነበረ የተደረገው። በአካላዊ ጉሽሚያዎች እና ጥፋቶች ሲቆራረጥ በነበረው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ባህርዳር ከተማዎች ኳስን በመቆጣጠር እና ወደ ጎል በመድረስ ከተጋጣሚያቸው ተሽለው የነበረ ሲሆን በአንፃሩ አውስኮዶች በመከላከልም ሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴ ምንም አዎንታዊ ነገር ሳያሳዩ ቀርተዋል።
በ14ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የተገኘውን ኳስ እንዳለ ከበደ ሞክሮት የአውስኮድ ተከላካዮች አውጥተውት ጨዋታው በማዕዘን ምት ሲቀጥል ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ወሰኑ ዓሊ በግንባሩ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ባህርዳርን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከአስር ደቂቃዎች በኃላ በተመሳሳይ በመልሶ ማጥቃት አንቅስቃሴ ባህር ዳር ከተማዎች ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተው ኳሷ የአውስኮድን ግብ ጠባቂ ከፍያለው ሃይሉን አልፋ ከመረብ ጋር ተገናኘች ተብሎ ሲጠበቅ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተዋት ግብ ሳትሆን ቀርታለች። ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ባለ ሜዳዎቹ ከፍተኛ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በተለይ ወሰኑ አሊ ለተጋጣሚ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቾች የራስ ምታት ሆኖ አምሽቷል። የባህርዳሮች ጥረት ቀጥሎ በ38ኛው ደቂቃ ፍቅረሚካኤል አለሙ ሁለተኛ ጎል በግንባሩ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በሰዓቱ አውስኮዶች ያሳዩት የመከላከል ድክመት ለጎሏ መቆጠር ዋነኛ ምክንያት እንደነበር ተስተውሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ተረጋግተው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን በተቃራኒው አውስኮዶች ጎሎችን አስቆጥሮ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረቶችን ቢያደርጉም ወደ ጎል በመድረስ ረገድ ግን አጥጋቢ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ቀርተዋል። አውስኮዶች የጨዋታው የመጀመሪያ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ የፈጠሩት በ62ኛው ደቂቃ ሲሆን በረጅሙ ከግብ ጠባቂው የተመታውን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሰለሞን ጌድዮን በሚገባ ተቆጣጥሮት ወደ ግብ ቢሞክረውም ኳሷ ወደ ውጪ ወጥታለች። 73ኛው ደቂቃ አካባቢ በተጨዋቾች መካከል በተፈጠረ ግብ ግብ ጨዋታው ለ5 ደቂቃዎች ተቋርጦ የነበር ሲሆን ጨዋታው የከበዳቸው የሚመስሉት የመሃል ዳኛው ከረን እንዳለ ተጨዋቾችን በማረጋጋት ጨዋታውን አስቀጥለዋል። ሙሉ ክፍለ ጊዜ ቅ ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት አውስኮዶች በዜሮ ከመሸነፍ የሚያድናቸውን የግብ ማግባት እድል አግኝተው ምንተስኖት አድኖባቸዋል።
በድሉ ተጠቅሞ ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 28 በማድረስ ከተከታዩ ያለውን ልዩነት ወደ 4 ከፍ አድርጎ መሪነቱን ሲያጠናክር አውስኮድ በ17 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ተቀምጧል።
መድን ሜዳ ላይ በተደረገው የኢትዮጵያ መድን እና ነቀምት ከተማ ጨዋታ ባለሜዳው መድን በትሁት ኑር ጎል ወደ እረፍት ቢያመራም ነቀምቶች ከእረፍት እንደተመለሱ አቻ መሆን ችለው ነበር። ሆኖም አንጋፋው ተከላካይ ሳምሶን ሙሉጌታ ባስቆጠረው ጎል መድኖች ሙሉ ሶስት ነጥብ ከጨዋታው መሰብሰብ ችለዋል።
በውጤቱ መሰረት መድን በ17 ነጥቦች ደረጃውን ወደ 8ኛ ሲያሻሽል ነቀምት ከተማ በ5 ነጥቦች አሁንም በሰንጠረዡ ግርጌ ተቀምጧል።