በሀላባ ከተማ ፣ ሙገር ሲሚንቶ እና መከላከያ የውድድር ጊዜያትን ማሳለፉን ተከትሎ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ጥሪ አማካኝነት ለኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው የግራ መስመር ተከላካዩ ነጂብ ሳኒ ከ23 ወራት ጉዳት በኋላ ለአንድ ወር ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ልምምድ እየሰራ ቆይቶ በመጨረሻም በክለቡ የአንድ አመት ውል በመፈራረም ወደ እግርኳስ ለመመለስ በቅቷል።
ነጂብ ሳኒ ሚያዝያ ወር 2008 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር መከላከያ ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ሲጫወት ነበር የጉልበት ጉዳት ያገጠመው። ተጨዋቹ ከዛ ጉዳት በኋላ ወደ ሜዳ ያልተመለሰ ሲሆን እጅግ አስቸጋሪ ጊዜ ማሳለፉን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡ “ያለፈውን ከአንድ አመት በላይ የሚሆን ጊዜ ያጋጠመኝን ጉዳት ተከትሎ እጅግ ፈታኝ የሆነ አስቸጋሪ ወቅትን አሳልፌበታለው። በፈጣሪ እርዳታ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር አብሬ ልምምድ እየሰራው ቆይቻለው። በጣም ጥሩ ልጆች ያሉበት ስብስብ ነው። አሁን በሁለተኛ ደረጀ ላይ ይገኛል ። በቀጣይ አብረውኝ ካሉት ተጨዋቾች ጋር በመሆን ለዋንጫ እንጫወታለን ብዬ አስባለው። ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር መከላከያ አብሬው ሰርቻለው። አሁንም ከእርሱ ጋር የመስራት እድል በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። አሰልጣኝ ገብረመድህንን በዚህ አጋጣሚ ዳግም ወደ እግርኳስ እንድመለስ ስለረዳኝ እጅግ አድርጌ ላመሰግን እፈልጋለው” ብሏል።
በተያያዘ ዜና ከመቐለ ከተማ ጋር በስምምነት የተለያየው የቀድሞ የወላይታ ድቻ አማካይ ዮሴፍ ደንገቶ በጅማ የነበረው የሙከራ ጊዜ ባለመሳካቱ ከክለቡ ጋር የተለያየ ሲሆን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከፈረመ በኃላ በጉዳት ምክንያት ለጅማ አባ ጅፋር ምንም አይነት ጨዋታ ሳያደርግ የቀረው አሸናፊ ሽብሩ እና ሌላኛው ከባድ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ተጨዋች ዝናቡ ባፋአም ከአባ ጅፋር መለያየታቸው እርግጥ ሆኗል።