ኮንፌድሬሽን ዋንጫ | ወላይታ ድቻ ምሽቱን ግብፅ ይጓዛል

በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር የግብፁ ዛማሌክን ከሳምንት በፊት በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም 2-1 በሆነ ውጤት ያሸነፈው ወላይታ ድቻ የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ዛሬ ምሽት 3፡30 ላይ 21 ተጫዋቾች እና 6 የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ጨምሮ አመራሮች እና ጋዜጠኞች ያካተተ 42 የልዑካን አባላትን እንዲሁም ጥቂት ደጋፊዎችን ይዞ ወደ ካይሮ ያመራል፡፡

አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ወደ ግብፅ ይዘዋቸው ከሚሄዷቸው ተጫዋቾች መካከል በዚማሞቶው እና የመጀመርያው የዛማሌክ ጨዋታ ያልተጠቀሙባቸው ሶስት አዳዲስ ተጫዋቾች ተካተውበታል፡፡ ተከላካዩ ሲሳይ ማሞ፣ አማካዮ እዮብ አለማየሁ እና ከክለቡ እንደተለያየ ተገልፆ የነበረውን ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ፌቮን በስብስባቸው የተካተቱ ሲሆን በዚማሞቶው ጨዋታ ላይ ጉዳት ገጥሞት የወጣው አጥቂው ዳግም በቀለ ከስብስቡ ውጪ መሆኑ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም ፀጋዬ ብርሀኑ እና እርቅይሁን ተስፋዬ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው አሁንም በማጣሪያው ክለቡን አያገለግሉም፡፡ በተቃራኒው በሊጉ ወልዲያን አስተናግደው ሁለት ለምንም ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ የትከሻ ህመም ገጥሟቸው የነበሩት በዛብህ መለዮ እና ኃይማኖት ወርቁ ከህመማቸው አገግመው እንደሚያቀኑ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ቡድኑ ካይሮ ሲደርስ በግብፅ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ኢትዮጵያውያን አቀባበል እንደሚያደርጉለት የተገለፀ ሲሆን በግብፅ እየተጫወተ የሚገኘው ሽመልስ በቀለ ለቡድኑ ሆቴል ለማመቻቸት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ዕሁድ 10፡00 ላይ ካይሮ ላይ በሚደረገው ጨዋታ ቡድናቸው በሀዋሳ ያደረገውን በካይሮም ለመድገም እንደሚጓዝ አሰልጣን ዘነበ ፍስሃ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ “ለመልሱ ጨዋታ እንዲረዳን ባለፉት ቀናት ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ተመርኩዤ ነበር ዝግጅት ስናደርግ የነበርነው፡፡ ባለፈው የነሱን አጨዋወት ተረድቼ እንደተቆጣጠርናቸው ሁሉ አሁንም ለማስቀጠል በሚረዳኝ ስራ ላይ ትኩረት አድርጌ ሰርቻለሁ፡፡ እዚህ ያደረግነው ለመድገም ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፡፡ አጥቅተን ተጫውተን አሸንፈን ለመውጣት ነው ያሰብነው ፡፡ በእርግጥ ባለፈውሞ የነሱ ጠንካራ ጎን ላይ አሁንም ይበልጡኑ ሰርተን ያለንንም ነገር ጠብቀን በጠንካራ አጨዋወት ፤ ይበልጡኑ ግን ግብ ለማስቆጠር ነው ጥረት የምናደርገው፡፡ በዚህ ላይ ባሉን ቀናት በሚገባ ስንዘጋጅ ቆይተናል፡፡

 

አሰልጣኝ ዘነበ አክለውም የመጀመርያው ጨዋታ ውጤትን ለማስጠበቅ አፍፍጎ መጫወትን እንደማይመርጡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ እኔ በፍፁም ለመከላከል ወደ ሜዳ አልገባም፡፡ በመከላከል ላይ ያተኮረ ጨዋታ በኔ በኩል ዋጋ የለውም፡፡ ግብፅ ላይ ብቻ ሳይሆን የትም ቢሆን ራሴን ማስከበር እና በማጥቃት ተጫውቶ ማሸነፍ ነው አላማዬ፡፡ ለመከላከል ከሆነ ግን መጀመርያውኑም ከዚህ ባንሄድ ይሻላል፡፡ ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

ወደ ግብፅ የሚጓዙ 21 ተጫዋቾች

 

ግብ ጠባቂዎች

ወንድወሰን ገረመው ፣ ኢማኑኤል ፌቮ ፣ መሳይ ቦጋለ

ተከላካዮች

ሙባረክ ሽኩር ፣ ውብሸት አለማየሁ ፣ ተክሉ ታፈሰ ፣ እሸቱ መና ፣ ተስፉ ኤልያስ ፣ ሲሳይ ማሞ ፣ ውብሸት ክፍሌ

አማካዮች

ኃይማኖት ወርቁ ፣ በዛብህ መለዮ፣ አብዱልሰመድ አሊ ፣  ቸርነት ጉግሳ ፣ ያሬድ ዳዊት ፣ አምረላህ ደልታታ ፣ በረከት ወልዴ ፣  እዮብ አለማየሁ

አጥቂዎች

ዘላለም እያሱ ፣ ጃኮ አራፋት ፣ተመስገን ዱባ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *