የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለብ የሆነው መከላከያ ደካማ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ መሆኑን ተከትሎ አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬን አሰናብቶ ስዩም ከበደን የክለቡ አዲሱ አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል፡፡ አሰልጣኝ ስዩም በሰበታ የነበራቸውን ውል በስምምነት አፍርሰው የ11 ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ መከላከያን የተረከቡ ሲሆን በዛሬው እለትም ስራቸውን ጀምረዋል፡፡
15 ነጥቦች ብቻ ሰብስበ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ የራቀው መከላከያን ከስጋት ነፃ የማድረግ ኃላፊነትን የተረከቡት አስልጣኝ ስዩም ኃላፊነታቸውን ለመወታት እንደሚሰሩ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ ከክለቡ ጋር ተነጋግሬ ስመጣ የክለቡ ስጋትም ይሄ ነው። ክለቡ ያለበት ደረጃ ታች ነው። ከፍተኛ ፈተና ይጠብቀኛል፡፡ እንደውል ዘመን የተፈራረምነው እስከ 2011 ድረስ ነው። እኔም ከፊታችን የሚጠብቀውን 15 ጨዋታ አጠቃላይ የራሴንም የምችለውን ነገር አድርጌ ከተጨዋቾች ጋር ደግሞ ይህን ትኩረት አድርገን ይህን ትልቅ ክለብ ካለበት ለማውጣት ነው የምታገለው። በዚህም የተሸለ ቦታ ላይ እንደርሳለን ብዬ አስባለው።›› ብለዋል፡፡
በ2008 ከየመን ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ አዲስ አበባ ከተማን ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አሳድገው ለ6 ወራት በሊጉ ቡድኑን ቢመሩም በስምምነት በመለያየት ሌላው የከፍተኛ ሊግ ክለብ ሰባታ ከተማን ተረክበው ያለፉትን 6 ወራት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ 1994 እና 1995 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሱት አሰልጣኝ ስዩም በቅርብ አመታት በፕሪምየር ሊግ ክለቦች እምብዛም አለመታየታቸው ተጽእኖ እንደማይፈጥርባቸው እና ልምዳቸውን ተጠቅመው ቡድኑን ማሻሻል እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡
‹‹ በመሰረቱ በፕሪምየር ሊግ ማሰልጠን ለእኔ አዲሴ አይደለም ። በሀገሪቱ ትልቅ ክለብ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስን ከአንዴም ሁለት ጊዜ አሰልጥኜ የጥሎ ማለፍ እና የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ማድረግ ችያለው ። ከዛም አልፎ ኮከብ አሰልጣኝም ሆኜ መመረጥ ችያለው። ከሀገሬም ከወጣው በኃላ በየመን የሀገሪቱን የሊግ ቻምፒዮን እንዲሆን አስችያለው፡፡ የአሰልጣኝነት ህይወት ደግሞ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን ያሉበት ነው። ትላንት ዋንጫ ማንሳት የቻለ አሰልጣኝ ዛሬ ሌላ ሊሆን ይችላል። አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆን ምሳሌ ማድረግ ይቻላል ። ስለዚህ ከአአ ከተማ ጋር ከፍተኛ ሊግ እያለን ጥሩ ነገር አድርገን ወጥተናል፡፡ ፕሪምየር ሊግ ከገባን በኋላ ደግሞ ማድረግ የሚገባንን ነገር ባለሟሟላታችን ፣ አንዳንድ ክፍተቶችን ባለማስተካከላችን እንጂ እንደ ቡድን ቅርፅ እኔ እስከነበርኩበት ድረስ ጥሩ ነበር ብዬ ነው የማስበው። ስለዚህ ወደዚህ ስመጣ የካበተ ልምዴን ተጠቅሜ ቡድኑን ጠንካራ ለማድረግ ነው ጥረቴ። ››