ድሬዳዋ ከተማ በዝውውር መስኮቱ ሁለተኛ ተጫዋች በማስፈረም ከወር በፊት ከመቐለ ከተማ ጋር የተለያየው ዮሴፍ ደንገቶን የግሉ አድርጓል።
በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ለረጅም ጊዜያት የቆየበት ወላይታ ድቻን ለቆ ወደ መቐለ ከተማ ያመራው የመሀል ስፍራ ተጫዋቹ ዮሴፍ ድንገቶ በመቐለ ከተማ የተጠበቀውን ያህል ክለቡን ማገልገል ባለመቻሉ ምክንያት ከክለቡ ጋር በስምምነት በመለያየት ወደ ጅማ አባጅፋር አቅንቶ ወደ አንድ ወር የሙከራ ጊዜን ቢያሳልፍም አመርቂ የሆነ እንቅስቃሴን ማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት በክለቡ ሳይፈርም ቀርቶ ነው ወደ ምስራቁ ክፍል ድሬዳዋ ያመራው። በድሬዳዋ ከተማ የአንድ አመት ውል የፈረመው ዮሴፍ ክለቡ ያለበትን ከፍተኛ የአማካይ ተጫዋች ክፍተት ይደፍናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዝውውር ገበያው በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ጥረት እያደረገ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ አስቀድሞ አጥቂው በረከት ይስሀቅን ከኢትዮጵያ ቡና ያስፈረመ ሲሆን ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እንደተቃረቡም አሰልጣኝ ስምዖን አባይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡