በአመቱ ደካማ አጀማመርን ያሳየው እና በውጤት መጥፋት ምክንያት በርካታ ለውጦችን ያደረገው የደቡቡ ክለብ በሁለተኛው ዙር በተሻለ ተፎካካሪነት ለመቅረብ ዝውውሮችን እየፈፀመ ይገኛል፡፡
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሀላባ ከተማ የከፍተኛ ሊግ ቆይታው ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ማጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ያመራው ዘካሪያስ ፍቅሬ አንደኛው የክለቡ አዲስ ፈራሚ ሆኗል። አጥቂው በድሬደዋ የተፈለገውን ያህል እንቅስቃሴን ባለማድረጉ ምክንያት ቀሪ የአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ኮንትራት እያለው ከምስራቁ ክለብ ጋር ተለያይቶ ነው በአንድ ዓመት ውል ለአርባምንጭ ለመጫወት ስምምነት ላይ የደረሰው።
ሌላኛው አርባምንጭ ከተማን የተቀላቀለው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ፍቃዱ መኮንን ነው። ፍቃዱ የአንደኛ ሊግ ክለብ በሆነው ጋሞ ጨንቻ ውስጥ ያለፉትን ሁለት አመታት ተሰልፎ በመጫወት በተከታታይ አመታት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል። ተጫዋቹ በአርባምንጭ ለ25 ቀናት የቆየ የሙከራ ጊዜን ካሳለፈ በኃላ በአሰልጣኝ እዮብ ማለ እምነት ተጥሎበት በአንድ አመት የውል ስምምነት የአዞዎቹ ስብስብ አካል ሆኗል።
በተያያዘ ዜና አርባምንጭ ከተማ ሶስት ተጫዋቾችን ከታችኛው ቡድን ሲያሳድግ አሁንም ከጋሞ ጨንቻ ክለብ ሁለት ተጫዋቾች ሙከራ ላይ መሆናቸውን እና በተቃራኒው ወደ አራት የሚጠጉ ተጫዋቾች ደግሞ ከክለቡ ለመቀነስ ከጫፍ መድረሳቸውን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጨመሳ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡