በ2019 በኒጀር አዘጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ የመጀመርያ ዙር የማጣርያ ጨዋታውን ከብሩንዲ ጋር መጋቢት 23 ላይ የሚያደርገው የኢትዮዽያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የተጨዋቾች ምርጫ እና ዝግጅቱን ማድረግ ከጀመረ አስረኛ ቀኑ ላይ የደረሰ ቢሆንም እስካሁን ለጨዋታው የሚያስፈልጉ 25 ተጨዋቾችን መርጦ በመጨረስ ለፌዴሬሽኑ ለማሳወቅ እንደተቸገረ ለማወቅ ችለናል።
ለምርጫው በሚፈለገው መልኩ አለመከናወን እንደ ምክንያት እየቀረበ ያለው የተጫዋቾች የእድሜ ተገቢነት ( MRI ምርመራ) ሲሆን ለብሔራዊ ቡድኑ የመጀመርያ ምርጫ በመሆን ያስፈልጋሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጫዋቾች እድሜያቸው ከ20 አመት በላይ ሆኖ በመገኘቱ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ክለቦች ለብሔራዊ ቡድኑ እንዲጫወቱ ጥሪ የቀረበላቸው ተጨዋቾችን በፍጥነት ለመላክ ዳተኝነት በማሳየታቸው እንደሆነ ሰምተናል።
አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ እስካሁን ከ50 በላይ ወጣቶችን በማምጣት የሙከራ እድል በመስጠት 25 ተጨዋቾችን ለመለየት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ቢታወቅም በየቀኑ የሚመጡትን አዳዲስ ተጨዋቾችን ሳይጨምር ከመጀመርያው ጥሪ አንስቶ እስካሁን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር አብረው እየሰሩ የሚገኙ 25 ተጫዋቾች ብቻ ይገኛሉ ። ሆኖም ያለው ስብስብ በቂ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ እና ያሉትም ተጫዋቾች የዕድሜ ምርመራውን በበቂ ሁኔታ ማለፍ ካልቻሉ በሚል ስጋት አሠልጣኙ በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ ተጨማሪ ተጫዋቾችን በመጥራት ለመመልከት እንዳሰቡ እና በሚቀጥለው አራት እና አምስት ቀናት ውስጥ 25 ተጫዋቾቻቸውን ለይተው ለፌዴሬሽኑ በማሳወቅ ተጨዋቾቹን በተለያዩ የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማቀናጀት ፈታኝ ስራ እንደሚጠብቃቸው ተረድተናል ።
ከኢትዮዽያ ውጭ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የመጫወት አቅሙ ያላቸው ትውልደ ኢትዮዽያውያን በሙሉ መጥተው መሳተፍ እንደሚችሉ መገለፁን ተከትሎ በሉቲኒያ ለስታምብራስ በመጫወት ላይ የሚገኘው እና ከዚህ ቀደም በድረ-ገፃችን ያስተዋወቅናችሁ ሶፎንያስ መኮንን ቡድኑን ተቀላቅሎ ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት የቻለ ሲሆን በቀሩት ቀናት እና እስከ መልሱ ጨዋታ መዳረሻ ድረስ የሚመጡ ካሉ የሚስተናገዱ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል ።
በቀድሞው የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ በሚሰለጥነው የሉቲንያው ስተምብራስ የሚጫወተው ሶፎንያስ
በየጊዜው በሚመጡት አዳዲስ ተጨዋቾች ምክንያት አሁን በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ያሉትን ተጫዋቾች ስም ዝርዝር ይፋ ለማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም በቀጣዮቹ ቀናት ምርጫው ተጠናቆ የተመረጡ 25 ተጫዋቾች እንደደረሰን የምናሳውቅ መሆናችንን እንገልፃለን ።
መጋቢት 23 የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ከብሩንዲ አቻው ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ከተጫወተ በኋላ በሳምንቱ የመልሱን ጨዋታ የሚያደረገው የኢትዮዽያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ጨዋታ የብሩንዲ አቻውን መርታት ከቻለ በቀጣይ የመጨረሻ ማጣርያ ጨዋታውን ከሱዳን ከ20 አመት በታች ቡድን ጋር የሚያርግ ይሆናል።