በኮፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ኢትዮጵያዊው ወላይታ ድቻ ሃያሉን የግብፅ ክለብ ዛማሌክን ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 2-1 ማሸነፉ ብዙዎችን የአፍሪካ እግርኳስ ተከታታዮች አስደንቋል፡፡ የሶዶው ክለብ እሁድ ከዛማሌክ ጋር የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ካይሮ ሐሙስ ምሽት አቅንቷል፡፡
በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ለአራት ክለቦች መጫወት የቻለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ ወላይታ ድቻ ጫናን መቋቋም ከቻለ ወደ ቀጣዩ ዙር የአምስት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑን ጥሎ ማለፍ የማይችልበት ምክንያት እንደሌለ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡
“ዛማሌኮች በሜዳቸው የሚያደርጉት ጨዋታ ስለሆነ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ፈፅሞ መደናገጥ እና መፍራት የለባቸውም፡፡ የሰሜን አፍሪካ ክለቦች በሚታወቁበት ጫና ፈጥረው የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች መጫወት ይችላሉ፤ ስለዚህም ድቻ በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ከተቻለ 16.50 ላይ አለማድረስ ነው፡፡ ፈጣን እና ተስጥኦ ያላቸው የመስመር ተጫዋቾች፤ ለምሳሌ አንደ ፋቲህ እና መሃመድ አብደልአዚዝ ያሉ ተጫዋቾች ሰው እየቀነሱ በመሄድ በጣም ጥሩ ስለሆኑ የተለየ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ በግብ ክልሉ አቅራቢያ ልክ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የለመድነውን አይነት ጥፋት መስራት ዋጋ ያስከፍላል፤ እዚህ ላይም ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ ሌላው የአየር ላይ ኳስ፤ በተለይም የማዕዘን እና የቆሙ ኳሶች ማስቆጠር የሚችሉ ተጫዋቾች አሏቸው፡፡ ወላይታ ድቻ ሀዋሳ ላይ ያሳየውን እንቅስቃሴ ካይሮ ላይ ከደገመ ያልፋል፡፡ እንደ ቡድን መንቀሳቀስ ከተቻለ ዛማሌክን መጣል ይቻላል፡፡ ኤሃብ ጋላል በተፈጥሮ የሚሰራው ቡድን ከኳስ ጋርም ሆነ ያለኳስ ጫና ይፈጥራል፡፡ ጫና መቋቋም ነው ከድቻ የሚያስፈልገው፤ ለዚህም የሚያዋጣ አጨዋወት መተግበር አለባቸው፡፡”
የሊግ ዋንጫን ለተቀናቃኛቸው አል አህሊ አሁንም አሳልፎ የሰጡት ዛማሌኮች ዋንጫ የማሸነፍ እድላቸው እየቀነሰ በመሆኑ ለጨዋታው ትኩረት መስጠታቸውን ኡመድ ይጠቁማል፡፡
“ዛማሌክ ያለው እድል በኮንፌድሬሽን ዋንጫው እና የግብፅ ዋንጫ ማሸነፍ ነው፡፡ አንድ ድረ-ገፅ ላይ እንዳነበብኩት ጨዋታው አስቀድሞ ስዌዝ ላይ ነበር ሊካሄድ የታቀደዉ፤ አሁን ግን ወደ ካይሮ መልሰውታል፡፡ ፕሬዝደንቱ (ሞርታዳ መንሱር) ናቸው ክለባቸው ጫና ውስጥ ስለሚገኝ ጨዋታው እንዲዛወር ያደረጉት፤ ይህም ክለቡ ለማለፍ ያለውን ብርቱ ፍላጎት ያሳያል፡፡ አንዳንድ የዛማሌክ ደጋፊዎች በመጀመሪያው ጨዋታ ውጤት ተበሳጭተዋል፡፡ ‘እንዴት ድቻ በሊጉ 9ኛ የሆነ ቡድን ዛማሌክን ያሸንፋል?’ ያሉኝ አሉ፡፡ እግርኳስ መሆኑን ለብዙዎች ተናግሬያለሁ፡፡”
ኡመድ ሲያክል የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች በደጋፊዎች የድጋፍ ድምፅ ሳይሸበሩ ጨዋታቸውን ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል፡፡
“ብዙ ደጋፊ ሊገባ ይችላል፡፡ በዚህም የድቻ ተጫዋቾች ፈፅሞ መረበሽ የለባቸውም፡፡ ለፍርሃት ቦታ መስጠት አይገባም፡፡ በኢትዮጵያ በተደረገው ጨዋታ ግሩም ነበሩ፤ አሁንም ይህንኑ መድገም ነው የሚያስፈልገው፡፡ ሌላው በብዛት ግብፅ ውስጥ ጨዋታዎች ከመደረጋቸው በፊት ሳሩ ውሃ ይጠጣል፤ ይህም ኳሱ እንዲፈጥን ያደርጋል፡፡ በዚህ ላይ ታክቲካል ዲሲፕሊን ሊኖር ይገባል፡፡ ሜዳው ኢትዮጵያ ከለመድነው የሰፋ ስለሆነ ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ መሆን ያስፈልጋል፡፡ እኔ እዚህ ግብፅ ውስጥ ስለምጫወት ለምጄዋለሁ፤ ሆኖም ለሌላ ሃገር ክለብ ያስቸግራል፡፡ ታክቲክ እኛ ሃገር ከስር ስለማንማር ይዘን የመጣነው ነገር አይደለም፡፡ እዚህ ደግሞ ታክቲክ በልምምድ ወቅት አፅኖት ተሰጥቶት ስለሚሰጥ ተጫዋቾቻው ታክቲክ ላይ ጥሩ ናቸው፡፡ ድቻዎች በዚህ ረገድ ትኩረት ከሰጡ ማለፍ ይችላሉ፡፡”
ለስሞሃ በአጥቂነት በመጫወት ላይ የሚገኘው ኡመድ ዛማሌክ ያለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎችን ቢያሸንፍም በእንቅስቃሴ ረገድ አሳማኝ እንዳልሆነ በመናገር አስተያየቱን ቋጭቷል፡፡
የዛማሌክ እና ወላይታ ድቻ የመልስ ጨዋታ እሁድ ምሽት ካይሮ በሚገኘው አል ሰላም ስታዲየም ይደረጋል፡፡