በታንዛንያ አዘጋጅነት በ2019 ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ለመሳተፍ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ከቡሩንዲ ጋር የሚያደርገው የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ይሆን ዘንድ ፌዴሬሽኑ በቅርቡ በይፋ የሾመው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከወዲሁ ስራውን የጀመረ ሲሆን ከእርሱ ጋር አብረው በመሆን የሚያግዙት የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ትላንት ለፌዴሬሽኑ አሳውቋል ።
በተመስገን በረዳት አሰልጣኝነት የተመረጠው ሙሉጌታ አይቸው ይባላል። ቤተ እስራኤላዊ የሆነው ሙሉጌታ የዩኢኤፍኤ የአሰልጣኝነት ላይሰንስ እንዳለው የተገለፀ ሲሆን ያለፉትን አመታት በሀገረ እስራኤል የተለያዩ የታዳጊ ቡድኖችን በማሰልጠን ልምድ እንዳለው ተነግሯል። ወደ ኢትዮዽያ ከመጣበት ከቅርብ ጊዚያት ወዲህም ታዳጊዎች ላይ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል ።
በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት የተመረጠው በለጠ ወዳጆ ነው። አሰልጣኝ በለጠ ወዳጆ በኢትዮዽያ እግርኳስ ስማቸው ጎልተው ከሚጠቀሱ ግብ ጠባቂዎች አንዱ የሆነው በለጠ በመብራት ሀይል ፣ በምድር ጦር ፣ ሙገር ሲሚንቶ ፣ ኢትዮዽያ ቡና እና ኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን በአጠቃላይ ለ20 አመታት ማገልገል የቻለ ግብጠባቂ ነበር ። በ1998 ጎንቱን ከሰቀለ በኋላ በአሰልጣኝነት መከላከያ ፣ ሰበታ ከተማ ፣ ወልድያን ያሰለጠነ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በኢትዮዽያ መድን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን እየሰራ ይገኛል ።
በህክምና ባለሙያነት የተመደበው ደግሞ አትክልት ሲሆን በቅርቡ ለተጨዋቾች ጥሪ በማድረግ ስራቸውን በይፈ እንደሚጀምሩ ታውቋል። በፍጥነት ተጨዋቾችን በመመርጥ ወደ ቅንጅት ስራ ለመግባት እንደሚያስቡም አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታ ተጋጣሚ የትኛዋ ሀገር እንደሆነች ካፍ እስካሁን ያላሳወቀ ቢሆንም በቅርቡ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል ።