በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የኢትዮጵያው ክለብ ወላይታ ድቻ ከግብፅ ዛማሌክ ጋር ዛሬ ምሽት 1፡00 ላይ በካይሮ አል ሰላም ስታዲየም የመልስ ጨዋታቸው ያደርጋሉ፡፡ ድቻ በመጀመሪያው ጨዋታ ሀዋሳ ላይ 2-1 ዛማሌክን መርታት ችሏል፡፡ ዛማሌክ የኢትዮጵያ ክለቦች ላይ ያለው የበላይነት ለማስቀጠል እንዲሁም ወላይታ ድቻ ደግሞ አዲስ ታሪክ ለማስመዝገብ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ጨዋታው በግብፅ የስፖርት ቴሌቭዢን ቻናል ኦን ስፖርትስ የቀጥታ ስርጭት ያገኛል፡፡
ከጨዋታው አስቀድሞ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዲሁም የዛማሌኩ ኤሃብ ጋላል ለግብፅ ሚዲያዎች የሰጡትን አስተያየት አንዲህ አቅርበናል፡፡
“በመከላከል ላይ ያተኮረ ጨዋታ በኔ በኩል ዋጋ የለውም” ዘነበ ፍስሃ
“ለመልሱ ጨዋታ እንዲረዳን ባለፉት ቀናት ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ተመርኩዤ ነበር ዝግጅት ስናደርግ የነበርነው፡፡ ባለፈው የነሱን አጨዋወት ተረድቼ እንደተቆጣጠርናቸው ሁሉ አሁንም ለማስቀጠል በሚረዳኝ ስራ ላይ ትኩረት አድርጌ ሰርቻለሁ፡፡ እዚህ ያደረግነው ለመድገም ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፡፡ አጥቅተን ተጫውተን አሸንፈን ለመውጣት ነው ያሰብነው ፡፡ በእርግጥ ባለፈውሞ የነሱ ጠንካራ ጎን ላይ አሁንም ይበልጡኑ ሰርተን ያለንንም ነገር ጠብቀን በጠንካራ አጨዋወት ፤ ይበልጡኑ ግን ግብ ለማስቆጠር ነው ጥረት የምናደርገው፡፡ በዚህ ላይ ባሉን ቀናት በሚገባ ስንዘጋጅ ቆይተናል፡፡”
“እኔ በፍፁም ለመከላከል ወደ ሜዳ አልገባም፡፡ በመከላከል ላይ ያተኮረ ጨዋታ በኔ በኩል ዋጋ የለውም፡፡ ግብፅ ላይ ብቻ ሳይሆን የትም ቢሆን ራሴን ማስከበር እና በማጥቃት ተጫውቶ ማሸነፍ ነው አላማዬ፡፡ ለመከላከል ከሆነ ግን መጀመርያውኑም ከዚህ ባንሄድ ይሻላል፡፡”
“እርግጠኛ ነኝ በሜዳችን እንደምናሸነፍ” ኤሃብ ጋላል
“ሁኔታዎችን ስናይ የመጀመሪያ ዙር የጨዋታ ውጤት ለእኛ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ እኛ ጥሩ ነበርን እናም እድሎችን አምክነናል፡፡ ድቻ አንድ እድል አግኝቶ የማሸነፊያ ግቡን ሊያስቆጥርብን ችሏል፡፡”
“በተበላሸ ሜዳ ላይ ስትጫወት እና ሃይለኛ ዝናብ ሲደመርበት ስህተቶችን ለመስራት ቅርብ ትሆናለህ፡፡ ድቻ በጣም ሃይለኛ የሆነ ድጋፍም ከስታዲየሙ ታዳሚ ያገኙ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ተጫዋቾች በአህጉሪቱ የክለብ ውድድር ሲጫወቱ ይህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡”
“ሀዋሳ ላይ የተጫወትነው ለማሸነፍ ነበር፡፡ ሆኖም አልተሳካም፡፡ አሁን እርግጠኛ ነኝ በሜዳችን እንደምናሸነፍ እና ዘመቻችን እንደምንቀጥል፡፡ አምናለው የተሻለ እድል እንዳለን፡፡ ለማሸነፍ የሚያስፈልገንን ጨምረን ይዘናል፡፡”