ከፍተኛ ሊግ | ዲላ ከተማ ወደ መሪነት የተመለሰበትን ድል አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 14ኛ ሳምንት የምድብ ለ ጨዋታዎች መሪው ደቡብ ፖሊስ በሜዳው ሲሸነፍ ዲላ ከተማ ወደ መሪነት የሚመልሰውን ድል አስመዝግቧል፡፡ ጅማ አባ ቡናም ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ሶስት ነጥቦች አሳክቷል፡፡


ዲላ ከተማ 1-0 ካፋ ቡና

(በአምሃ ተስፋዬ)

ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሃ ግብሮች አንዱ በነበረው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች እንግዳው ቡድን ካፋ ቡና የኳስ የበላይነት ወስዶ ነበር፡፡ በ9ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ሙከራ በአሸናፊ በልቻ አማካይነት  ያደረጉት ካፋዎች በ14ኛው ደቂቃ በረከት ጌቱ ከርቀት የመታው ኳስ የዲላ ግብ ጠባቂ ቢመልሰውም ከዕጁ በማለፋ ወደ ግብነት ተለወጠ ሲባል ተከላካዩ ሙና በቀለ እንደምንም ብሎ ደርሶ አድኖበታል፡፡ የመጀመርያ እንቅስቃሴያቸውን በቀጣዮቹ 30 ደቂቃዎች መድገም ያልቻሉት ካፋዎች በሚገኙት አጋጣሚዎች የዲላን የተከላካይ ክፍል በተደጋሚ ቢፈትሹም ስኬታማ መሆን አልቻሉም፡፡

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ እንቅስቃሴው የገቡት ዲላዎች በ16ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ የተሻገረውን ኳስ ምትኩ ማመጫ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የካፋ ቡና ግብ ጠባቂ ቀድሞ ሲያወጣው ሙና በቀለ የተመለሰውን ኳስ ወደ ግብ አክርሮ መቶ በግቡ አናት ላይ ሲወጣበት ነበር የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት፡፡ በ18ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከዋለው ኤልያስ መንግስቴ የተሻገረትን ኳስ ቢንያም በቀለ ያባከነው እንዲሁም በተመሳሳይ የግብ ዕድል ምትኩ ማመጫ ሳይጠቀምበት የቀረበት አጋጣሚዎችም ተጠቃሽ ነበሩ።

ከእረፍት መልስ ባለሜዳዋቹ ዲላ ከተማዎች የተሻለ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡ በ49ኛው ደቂቃ ላይ ኩምሴ ሞጨራ ከርቀት የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ታኮ ሲወጣበት 50ኛው ደቂቃ ላይም የመታው ሌላ ኳስ በግብ ጠባቂው ብቃት ወደግብነት ሳይለወጥ ቀርቷል። በዚህ መልኩ ጫናቸውን ያጠናከሩት ዲላዎች በ58ኛው ደቂቃ የተገኘውን ቅጣት ምት ዝናው ዘላለም በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ጎል መሪ መሆን ችለዋል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኃላ እብዛም ወደ ካፋ ቡና መጠጋት ያልቻሉት ዲላዎች ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ቡድናቸው ቅርፅ ሲያጣ ተስተውሏል። በተቀራኒው ካፋ ቡናዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫና መፍጠር ችለዋል፡፡ በተለይም በ79ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተሻማውን ኳስ ዘካርያስ ወልዴ በግንባሩ ገጭቶ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የወጣበት ኳስ ከፋ ቡናን አቻ ለማድረግ የተቃረበ ሙከራ ነበር። ጨዋታው በዲላ ከተማ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ዲላ ከተማ በ24 ነጥቦች ለሁለት ሳምንታት የተነጠቀውን መሪነት አስመልሷል፡፡


ደቡብ ፖሊስ 1-2 ሀምበሪቾ

(ቴዎድሮስ ታከለ)

በሜዳው አይበገሬነቱን ያሳየው ደቡብ ፖሊስ ሀምበሪቾን አስተናግዶ 2-1 በመሸነፍ መሪነቱን ለዲላ ከተማ አስረክቧል፡፡ ደቡብ ፖሊሶች ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባሳዩበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሀምበሪቾዎች በተደጋጋሚ ወደ ባለሜዳው የግብ ክልል በመድረስ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። ለሀምበሪቾዎች የማጥቃት ሀይል የደቡብ ፓሊስ ተከላካዮች የሚፈጥሩት ተደጋጋሚ የሜዳ ላይ ስህተቶች ተጠቃሽ ነበሩ። በተለይ 19ኛው ደቂቃ ላይ መስቀሌ ለቴቦ በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ፓሊስ የግብ ክልል ገብቶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ፊት መስመር ላይ ተሰልፎ ሲጫወት የነበረው የቀድሞው የዳሽን ቢራ አጥቂ ፍፁም ደስይበለው የሚያደርገው አስጨናቂ የመረበሽ አጨዋወት ለስህተት ለተጋለጡት የፓሊስ ተከላካዮች ፈተና ሲሆንም አስተውለናል። 20ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታደሰ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ፍፁም ደስ ይበለው አግኝቷት ግብ ሳያደርጋት በፊት የደቡብ ፓሊሱ ግብ ጠባቂ ሀብቴ ከድር ይዞበታል። በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ሀምበሪቾ የግብ ክልል የደረሱት ደቡብ ፓሊሶች 24ኛው ደቂቃ ላይ አበባየሁ ዮሀንስ ከቢኒያም አድማሱ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብለው በመጨረሻም ለበሀይሉ ወገኔ አሾልከውለት በሀይሉ ከግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ጋር ተገናኝቶ ፓሊስን ቀዳሚ ሊያደረግ የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀም ቀርቷል። ኳስ ይዘው መጫወትን አማራጭ አድርገው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሀምበርቾዎች በፈጠሩት ሌላ ዕድል 28ኛው ደቂቃ ላይ መስቀሌ ለቴቦ ከቀኝ የግብ መስመር በቀጥታ የላካትን ኳስ አጥቂው ፍፁም ደስይበለው ወደ ግብ በቀጥታ ሞክሮ ተከላካዮቹ ተረባርበው አውጥተውበታል። ከደቡብ ፓሊሶች መልሶ ማጥቃትም 34ተኛ ደቂቃ ላይ ሚካኤል ለማ ለአጥቂው ያሳለፈለትን በሀይሉ ግብ ጠባቂውን አልፎ ወደ ግብ ሲልካት ተከላካዩ እንዳለ ዮሀንስ  ከግቡ ጠርዝ ላይ ተንሸራቶ ያወጣት ሙከራ ተጠቃሽ ነበረች። ሆኖም ሀምበርቾዎች 41ኛው ደቂቃ ላይ በመስመር በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ምኞት ማርቆስ ወደ ውስጥ ገብቶ መሬት ለመሬት ከላካት ኳስ ፍፁም ደስይበለው አስቆጥሮ ቀዳሚ ሆነዋል። የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ፍፁም ደስይበለው የአብዮት ወንድይፍራው የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ያገኛትን ግልፅ ዕድል ቢጠቀም ኖሮ ደግሞ መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ባለ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ደቡብ ፓሊሶች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ሀምበሪቾዎች መሪነታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት በመልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ ታይቷል። ሀምበሪቾ በተደጋጋሚ በሜዳ ላይ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት በሚመስል መልኩ ሆን ብላችሁ ነው የምትወድቁት በማለት የእለቱ ዳኛ ወደ 8 ቢጫ ካርዶችን መዘውባቸዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ፖሊሶች በበሀይሉ ወገኔ አማካኝነት የጠራ የግብ ዕድል ቢፈጥሩም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ግን አልተቻላቸውም ነበር። ነገር ግን 70ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል የተገኘችን አጨቃጫቂ የቅጣት ምት ሚካኤል ለማ በረጅሙ ወደ ግብ ሲልካት ተጨራርፋ ተቀይሮ ለገባው ሙዲን አብደላ ስትደርሰው ከመረብ አሳርፎ ፖሊስን አቻ አድርጓል። ቅጣት ምቷ ተገቢ አይደለችመሸ በሚል ግብ ከሆነች በኃላ የሀምበሪቾ ተጫዋቾች ዳኛውን በመክባቸው ምክንያትም ጨዋታው ለ10 ደቂቃ ያህል ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ክስ ካስመዘገቡ በኃላ ቀጥሏል።  ሆኖም የሀምበሪቾው አጥቂ ፍፁም ደስይበለው ከዳኛው ጋር በሚያደርገው እላፊ ጭቅጭቅ እና ለፀብ መጋበዝ በቢጫ ካርድ መታለፉ በርካታ ተቃውሞን አስነስቶም ነበር ፡፡ ከውዝግቡ በኃላ ጨዋታው ቀጥሎ ደቡብ ፓሊሶች ወደፊት ተስበው በማጥቃት ላይ ሳሉ በመልሶ ማጥቃት የመጡት ሀምበሪቾዎች 83ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዮናስ ታዬ ለሌላኛው ተቀያሪ አላዛር ዮሀንስ አመቻችቶ ሲሰጠው አላዛር አጋጣሚውን ግብ አድርጎት ሀምበሪቾ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዞ ሲወጣ ፓሊስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡


ሻሸመኔ ከተማ 0-1 ጅማ አባ ቡና

(ቴዲ ታደሰ)

 

ወደ ሻሸመኔ ያቀናው ጅማ አባ ቡና ሻሸመኔ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ ይበልጥ መቅረብ ችሏል፡፡ በዕለቱ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በመኖሩ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ እቅስቃሴ ባለሜዳዎቹ የመጀመርያዎቹን 15 ደቂቃዎች ተጭነው ተጫውተዋል፡፡ በነዚህ ደቂቃዎች ውስጥም ከቆመ ኳስ (ከቅጣት እና ከመዓዘን ምት) ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብነት አለመቀየራቸው የሚያስቆጭ ነበር፡፡ ከ15ኛው ደቂቃ በኃላ የማጥቃት እቅስቃሴ በይበልጥ አጠናክረው የቀጠሉት ሻሸመኔዎች 30ኛው ደቂቃ ይላ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የአባ ቡና ተከላካዮች ኳስን በእጅ በመንካታቸው የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት እስራኤል ታደሰ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ከፍፁም ቅጣት ምቱ መሳት በኃላ ሻሸመኔዎች የተነሳሽነት መንፈሳቸው ተቀዛቅዞ ታይቷል፡፡ በዚህ መልኩ የመጀመሪያውን አጋማሽ ያለግብ አጠናቀዋል፡፡

ከእረፍት መልስ አባቡናዎች ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ እድል በመፍርም ተሽለው ቀርበዋል፡፡ በዚህም በተደጋጋሚ የሻሸመኔ ተከላካዮችን ማስጨነቅ ችለው የነበሩ ሲሆን በ80 ደቂቃ ከቴዎድሮስ ታደሰ የተሻገረችለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ኪዳኔ አሰፋ ከሜዳቸው ውጭ 3 ነጥብ ያስገኘላቸውን ግብ በማቆጠር ቡድኑ አሸንፎ እዲወጣ ማድረግ ችሏል።


ሌሎች ጨዋታዎች

(አምሃ ተስፋዬ)

አቢዮ አርበሳሞ ስታድየም ላይ ሀዲያ ሆሳዕና በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል ናሽናል ሴሜንትን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ የሆሳዕናን ወሳኝ የድል በ88ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው በረከት ወልደዮሐንስ ነበር፡፡ ልላሌ በኩል ግርጌ ላይ የሚገኘው ነገሌ ከተማ ወደ መቂ አቅንቶ መቂ ከተማን 2-1 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ከዕረፍት በፊት መቂዎች በግብ አዳኛቸው በላይ ያደሳ ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችልም ከዕረፍት መልስ ነገሌ ከተማዎች መቆያ አታላይ እና ኃይለየሱስ ኃይሌ አማካይነት ባስቆጠሯቸው ግቦች ማሸነፍ ችለዋል።

 

ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከስልጤ ወራቤ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 በበሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል እንግዳውቹ ስልጤ ወራቤዎች በ41ኛው ደቂቃ በፈድሉ ሀምዛ ጎል ቀዳሚ ቢሆኑም ኤፍሬም ቶማስ ቡታጅራን አቻ አድርጓል፡፡ በመቀጠል ወንድወሰን ዮሐንስ በ61ኛው ደቂቃ ላይ ቡታጅራን ወደ መሪነት ማሸጋገር ቢችልም በ76ኛው ደቂቃ ፈቱላሂም ሴቾ በ76ኛው ደቂቃ ለወራቤ የአቻነቷን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ሚዛን አማን ላይ ቤንች ማጂ ቡና ከ ሀላባ ከተማ ተጫውተው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ወልቂጤ ከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ሚያዝያ 8 ተሸጋግሯል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *